Tuesday, August 9, 2016

ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ዕዉን ለማድረግ የኦዲግ አበረታች ጅምሮች

lencho letaበዘዉዴ ጉደታ ሙለታ
እንደመግቢያ

ይህ ጽሑፍ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) በዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ከተጋበዙ ዕዉቅ ኢትዮጵያዉያን ጋር አድርጎት በነበረዉ ሰፊ፣ ግልፅና ልባዊ ዉይይት ላይ እንደመግቢያ የቀረበ ሲሆን በአብዛኛዎቹ የዉይይቱ ተሣታፊዎች ጥያቄ መሠረት በተለያዩ ድህረ-ገጾች አማካይነት ለኢትዮጵያዉያን አንባቢዎች እንዲቀርብ ተደርጎ የተዘጋጀ ነዉ፡፡ በጽሁፉ ዉስጥ የሚነሱት ሃሳቦች ግን የአቅራቢዉ ግለሰብ አመለካከት መሆናቸዉ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ ይህም ማለት የተጋነኑ ወይም ስህተት የሆኑ ነጥቦች ቢኖሩ የጽሑፉ አቅራቢ ግለሰብ ችግር እንጂ የድርጅቱ አቋም ተደርገዉ መወሰድ የለባቸዉም፡፡

Read Full Story in PDFዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ዕዉን ለማድረግ የኦዲግ አበረታች ጅምሮች በዘዉዴ ጉደታ ሙለታ
እንደመግቢያ ይህ ጽሑፍ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) በዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ከተጋበዙ ዕዉቅ ኢትዮጵያዉያን ጋር አድርጎት በነበረዉ ሰፊ፣ ግልፅና ልባዊ ዉይይት ላይ እንደመግቢያ የቀረበ ሲሆን በአብዛኛዎቹ የዉይይቱ ተሣታፊዎች ጥያቄ መሠረት በተለያዩ ድህረ-ገጾች አማካይነት ለኢትዮጵያዉያን አንባቢዎች እንዲቀርብ ተደርጎ የተዘጋጀ ነዉ፡፡ በጽሁፉ ዉስጥ የሚነሱት ሃሳቦች ግን የአቅራቢዉ ግለሰብ አመለካከት መሆናቸዉ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ ይህም ማለት የተጋነኑ ወይም ስህተት የሆኑ ነጥቦች ቢኖሩ የጽሑፉ አቅራቢ ግለሰብ ችግር እንጂ የድርጅቱ አቋም ተደርገዉ መወሰድ የለባቸዉም፡፡ ዉይይቱ የተካሄደዉ በሜይ ወር መጨረሻ አካባቢ ስለነበር በዚያን ወቅትም ሆነ ከዚያ ወዲህ በመላዉ ኦሮሚያ እየተካሄደ ያለዉን ሕዝባዊ አመፅ ጨምሮ በአገራችን የተለያዩ ክልሎች የሚካሄዱት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች እየተጠናከሩ የመጡ ከመሆናቸዉም በላይ የሚቀርቡት ጥያቄዎችና በሕዝቡ የሚሰሙት መፈክሮች የሕዝባችን የአንድነት፣ የወንድማማችነት፣ የመተሣሠርና ግፍና ጥቃትን በጋራ ለመከላከል የመተባበር ስሜት እየተጠናከረ መምጣቱን የሚያረጋግጡ ናቸዉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የገዢዉ ቡድን ከፋፍሎ የመግዛትና ነጣጥሎ የመምታት ፖሊሲዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በአጠቃላይ በወጣቱ ትዉልድ ዘንድ ደግሞ በተለይ ምንም ዓይነት ቦታ የሌላቸዉና የሕዝባችን ንቃተ-ህሊና በጡንቻቸዉ ከሚያስቡት የገዢዉ ቡድን አባላት እጅግ ልቆ መሄዱን በግልፅ ያሣዩ ናቸዉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ዉስጥ የተነሡት ዋና ዋና ነጥቦችም ይህንኑ የሚያጠናክሩ በመሆናቸዉ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንታገል የሚለዉን የአብሮነት ጥያቄ ለሚያነሱ ወገኖች የዉይይት መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል እምነት ቢቀርብም በአዳራሽ ዉስጥ ለተሰበሰቡ ዉስን የዉይይት ተሣታፊዎች በንግግር መልክ የቀረበን ጽሑፍ በስፋት እንዲነበብ አድርጎ ለማቅረብ ሲሞከር አንዳንድ ቦታዎች ላይ አቀራረቡ ለአንባቢ ላይጥም ይችል ይሆናል፡፡ የብዙዎቹን የዉይይቱን ተሣታፊዎች ተደጋጋሚ ጥያቄ ለመመለስ ሲባል ግን በዚህ መልኩ ለማቅረብ ተሞክሯልና አንባቢያን ይህንኑ ከግምት ዉስጥ እንድታስገቡ በትህትና ትጠየቃላችሁ፡፡ ትንሽ ስለዉይይቱ ይህ ጽሑፍ በመግቢያነት የቀረበበት የአንድ ሙሉ ቀን ዉይይት ተሣታፊዎች የተጋበዙት ለእያንዳንዳቸዉ በግል በተፃፈላቸዉ ደብዳቤ አማካይነት ነበር፡፡ የግብዣ ደብዳቤዉ ለአንዳንድ ኢትዮጵያዉያን በአድራሻቸዉ ሲደርስ ግርምታንና ጥሪዉን ያለማመን ስሜት ፈጥሮ እንደነበረ ይህ ስሜት አድሮባቸዉ የነበሩ ተጋባዦች ራሳቸዉ አልሸሸጉም፡፡ ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ዉጭ ለሚደረጉ ኢትዮጵያ ነክ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንደ ዋና ማዕከል ተደርጎ በሚታየዉ የዋሺንግተን ዲሲ ኣካባቢ አንድ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት “በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንወያይ” በሚል ተነሣሽነት ዕዉቅ ኢትዮጵያዉያንን ለዉይይት መጋበዝ ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን ፍፁም የማይታሰብም ስለሚመስል ነዉ፡፡ ነገር ግን የአገራችንን ዉስብስብ ችግሮችና እየመጣብን ያለዉን አገር-አልባ ሊያደርገን የሚችል ወያኔ-ሠራሽ አስከፊ አደጋ ለተረዱና አገር ዉስጥ ያለዉን እዉነታ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት ለሞከሩ ወገኖች ኦሮሞነታቸዉን በኩራት፣ በልበሙሉነትና በድፍረት በየመድረኩ በማንፀባረቅ በሚታወቁ ሰዎች “ስለኢትዮጵያ ጉዳይ እንወያይ” ተብሎ መጠየቅ ግር የሚያሰኝ ሳይሆን የዉይይቱን አዘጋጆች የሚያስመሰግን ሆኖ ነዉ የተወሰደዉ፡፡ በተለይም በደፈናዉ “የኢትዮጵያ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት” ከማለት ይልቅ “ምን ዓይነት አንድነት? ምን ዓይነት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እሴቶች?” ብለዉ ለመጠየቅና ለመወያየት ፈቃደኛ የሆኑ አስተዋይና አርቆ አሣቢ ኢትዮጵያዉያን ወገኖች የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግን) የመሰለ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅት ከመመሥረት አልፈዉ በበላይነት በመምራት ይታወቁ በነበሩ የኦሮሞ ታጋዮች የተመሠረተ የፖለቲካ ድርጅት “በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንወያይ” የሚል ጥሪ ሲያቀርብ ከመገረምና ከመደነቅ አልፈዉ “የተደበቀ አጀንዳ” ፍለጋ ርቀዉ ሳይሄዱ “እስቲ የሚሉትን እንስማ፤ የምንፈልገዉም ይህንን ነበር” በማለት ጥሪዉን በደስታ ተቀብለዉ መምጣታቸዉና በዉይይቱም ላይ እጅግ የሚደነቅ ተሣትፎ ማድረጋቸዉ የሚያበረታታ ነዉ፡፡ በየትኛዉም መድረክ የኦሮሞና የኢትዮጵያ ጉዳይ በተነሣ ቁጥር መረሣት የማይገባዉ ነጥብ በሁለት የተራራቁ ጫፎች የቆሙ ፅንፈኛ ወገኖች የመኖራቸዉን ያህል “ትናንት እኮ ዛሬ አይደለም፣ ይህ ትልቅ ሕዝብ ለግማሽ ምዕተ-ዓመት ሲያካሄደዉ የነበረዉ ትግል በሌሎችም ዘንድ በቂ ግንዛቤ እያገኘ ነዉ፣ ጥቂቶች እንደሚሉትም የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ አገርን ለማፍረስ የቀረበ ጥያቄ አይደለም” የሚል በሳል አመለካከት የመኖሩ እዉነታ ነዉ፡፡ እዉነትም የኦሮሞ ሕዝብ ትናንት የነፃነት፣ የእኩልነትና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎቹን በተማሩ ልጆቹና ንቃት ባላቸዉ መሪዎቹ አነሣሽነት ሀ ብሎ ሲጀምር ከነበረበት ቦታ ብዙ በጣም ብዙ ርቆ ሄዷል፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ በክልሉ ካለማንም ጣልቃ ገብነት ራሱን በራሱ የማስተዳደር ዲሞክራሲያዊ መብቱ እንዲከበርለት፣ በሃብቱ ላይ ራሱ ማዘዝ እንዲችል አበክሮ ከሚጠይቅበትና ከራሱም አልፎ ሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወገኖቹም ተመሣሣይ መብት እንዲኖራቸዉ ከሚጠይቅበት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወገኖቹ ጋር ሆኖ እዉነተኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት በአገሪቱ እንዲሰፍን ከሚታገልበት አኩሪ የሆነ የፖለቲካ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በሌላዉም ወገን ቢሆን የኦሮሞ ሕዝብ በዚያች አገር ዉስጥ እንደትልቅነቱ መያዝ የሚገባዉን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሥፍራ ተነፍጎ እንደቆየ፣ ይልቁንም አሁን ሥልጣን ላይ ያለዉን የጥቂቶች ገዢ ቡድን ጨምሮ ተከታታይ የአገሪቱ ገዢ ቡድኖች የኦሮሞን ሀብት በስግብግብነትና በራስ ወዳድነት ከመበዝበዝ ዉጭ ለሕዝቡ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መከበር ደንታ ቢሶች እንደነበሩና እንደሆኑ፣ ሌላዉ ቢቀር የአገሪቱን ግማሽ የሚያክል ቁጥር ያለዉ ሕዝብ የሚጠቀምበትን የኦሮምኛ ቋንቋ እንኳ የብሔራዊ መግባቢያ ቋንቋነት ደረጃ እንዲኖረዉ አለመደረጉ ትክክል እንዳልነበረ በቁጭት የሚናገሩ በደም ኦሮሞ ያልሆኑ አርቆ አሳቢ ኢትዮጵያዉያን በብዛት እየታዩ ነዉ፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ችግር ከመሠረቱ እንዲፈታና የምንመኘዉ የአገር አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲገነባ የምንፈልግ ከሆነ የአሁኑ ትግላችን ዘመናትን ያስቆጠሩትና ተገቢዉን መልስ ባለማግኘታቸዉ ዛሬም ድረስ የቀጠሉት በህዝቦችና በመንግሥት መሀል ያሉ ግንኙነቶችን በአዲስ መሠረት ላይ የመገንባት፣ የነፃነት፣ የዲሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የፍትሕ፣ የእኩልነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች የማያዳግም መልስ አግኝተዉ የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ተገቢዉን ሚና ሊጫወት የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር መሪዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥያቄዎች የማያዳግም መልስ ማግኘት ይቻል ዘንድ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወገኖቻቸዉ ጋር እጅና ጓንት ሆነዉ ለመሥራት ቆርጠዉ የተነሡ፣ ይህን ለማድረግ ደግሞ የማንንም በጎ ፈቃድ የማይጠይቁ ኦሮሞዎች ናቸዉ፤ ኦሮሞነትን በሚያከብር ኢትዮጵያዊነት የሚኮሩ የኢትዮጵያ ዜጎችም ናቸዉ፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪካዊ አሻራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሌለበት የዚያች አገር ክልልና ሕዝብ ስለሌለ ደግሞ ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት፣ እኩልነት፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መረጋገጥ ብሎም ለቋንቋዉ፣ ለባህሉና ለታሪኩ መከበር የሚታገሉትን ያህል ለሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያልተሸራረፈ መብትም ለመታገል ቆርጠዉ የተነሡ መሆናቸዉንም ሳያሠምሩበት አያልፉም፡፡ ስለሆነም ከኢትዮጵያዉያን ጋር የጋራ ዉይይት ከማድረግም አልፎ ወሳኝ የጋራ እርምጃዎችን የመዉሰዱ ጅምር ሰፋ ባለ መልኩ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የዉይይቱ ዓላማ እንግዲህ በእዉነተኛ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የምትተዳደር፣ ልጆቿን ሁሉ በእኩል ዓይን የምታይ፣ ሁላችንም ጎልተን የምንታይባት፣ አንዳችን ልጅ - ሌላችን ደግሞ የእንጀራ ልጅ የማንደረግባት፣ እንደ አፍቃሪ እናት የምትይዘንና እኛም የምንወዳት ኢትዮጵያን በጋራ ትግላችን በአዲስ መሠረት ላይ ለመገንባት እንዴት እጅ ለእጅ ተያይዘን አብረን በመታገል የምንፈልገዉን ዉጤት እናገኛለን? ለሚለዉና እስከዛሬ መልስ ላልተገኘለት ወይም በመልሱ ላይ ላልተስማማነዉ ትልቅ ጥያቄ የጋራ መልስ እንፈልግ የሚል ነዉ፡፡ ከላይ የተጠቀሰዉ የኦሮሞዎች ኢትዮጵያዊነትም ከእነዚህ የዜግነት መገለጫዎች የሚመነጭ ስለሚሆን እነዚህን ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ መመለስ የግድ ነዉ፡፡ ለእነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች የጋራ መልስ ፍለጋ ያመች ዘንድ ኦሮሞ ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊም ሆኖ ኦሮሞነት የሚቃረኑ ማንነቶች አይደሉም ብሎ ስለተነሣዉ ድርጅት አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) እንዴት ተመሠረተ? አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶችን መመሥረት ወይም ከነበሩበት ድርጅት ወጥቶ በተመሣሣይ ወይም በተቀራራቢ ስም ሌላ ድርጅት ይዞ ብቅ ማለት ባለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ሥልጣን የያዘዉን ገዢ ቡድን በመቃወም በተደረጉና አሁንም እየተደረጉ ባሉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ዉስጥ እጅግ ጎልቶ የታየ ተግባር ነበር፡፡ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር የኦነግ መስራቾችና ከፍተኛ የአመራረር አባላት የነበሩ ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎችን እንዲሁም ሌሎች የኦሮሞ ታጋዮችን አቅፎ ሲመሠረትም በሌሎች የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ዉስጥ ከታዩት ከአንዱ ድርጅት ወጥቶ ሌላ ድርጅት የመመሥረት አሰልቺ ሁኔታዎች የተለየ ላይመስል ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር የተመሠረተበት መንገድና ለመመሥረቱም ምክንያት የሆኑት እዉነታዎች በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ዉስጥ ከታዩት ወይም ከተሰሙት ሁኔታዎች በጣም የተለዩ ናቸዉ፡፡ ኦዲግ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲና የነፃነት ኃይሎች መካከል ያለዉን እጅግ የተራራቀ የአመለካከት ልዩነት ማስወገድ ካልሆነም በጣም ማሣነስ ይቻላል የሚል ጠንካራ እምነት ይዞና ይህን እምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ የፖለቲካ ሂደቶች ዉስጥ ግንባር ቀደም ሚና ለመጫወት ወስኖ የተነሣ ድርጅት ነዉ፡፡ የኦዲግ የትግል ስልትና የፖለቲካ ግቦችም የኢትዮጵያን ሕዝቦች የዲሞክራሲ፣ የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎች በማያዳግም ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴዎችን መሠረት የሚያደርጉ ናቸዉ፡፡ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት በጊዜያዊ አለመግባባት ወይም በቀላሉ ሊፈቱ ይችሉ የነበሩ የአመለካከት ልዩነቶችን በእርጋታና በአርቆ አስተዋይነት ለመፍታት ካለመቻል የተፈጠረ ድርጅት አይደለም፡፡ አንዳንዶች ለማስመሰል እንደሚሞክሩትም በጥቂት የኦሮሞ ፖለቲከኞች ስሜታዊነትና በዉጭ ኃይሎች ግፊት የተመሠረተ ድርጅት አለመሆኑንም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ለኦዲግ መመሥረት እንደጠንካራ መነሻ ተደርጎ የተወሰደዉ የፖለቲካ አመለካከት የጊዜዉን ዓለም-አቀፍ ሁኔታ በጥልቀት የመረመረ፣ የአፍሪካን ቀንድና የኢትዮጵያን ሁኔታ ያገናዘበና የኢትዮጵያን ሕዝቦች የጋራ ትግል የዳሰሰ ዓመታትን የፈጀ ጥልቅ ጥናትና ምርምር የተደረገበት ጠንካራ አመለካከት ነዉ፡፡ በመጨረሻም ወደ ኦዲግ ምሥረታ ካመራዉ ትልቅ ዉሳኔ ላይ የተደረሰዉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚኖሩ በርካታ የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት ጋር በአፋን ኦሮሞ - Waltajjii Marii Oromoo፣ በአማርኛ - የኦሮሞ የምክክር መድረክ፣ በእንግሊዝኛ ደግሞ - Oromo Dialogue Forum በሚል ጥላ ሥር ለሁለት ዓመት ያህል ተከታታይ ዉይይቶች፣ ጠንካራ ክርክሮችና ልባዊ ምክክሮች ከተደረጉ በኋላ መሆኑን መግለፅ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከእነዚህ ዉይይቶች በመነሣት የተደረሰበት ድምዳሜ ለኦሮሞም ሆነ ለሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚበጅ ሰፊ አጀንዳ ቀርፆ የነፃነት ትግሉን ወደፊት መግፋት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አንገብጋቢም ነዉ የሚል ስለነበር የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) ከሦስት ዓመታት በፊት ሊመሠረት ቻለ፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር ኦዲግ - በአርቆ አሳቢነት፣ በአስተዋይነት፣ በፖለቲካ ብስለት፣ ከምንም በላይ ደግሞ በግማሽ ምዕተ-ዓመት የፖለቲካ ትግል ልምድና ተሞክሮ ላይ በመመሥረት በኢትዮጵያ ሕዝቦች የነፃነትና የዲሞክራሲ ትግል ዉስጥ ያሉ ችግሮችን በጋራ ትግል ማስወገድ ይቻላል ብሎ የተነሣ የፖለቲካ ድርጅት ነዉ፡፡ የኦዲግ መሥራቾች የኦሮሞ ሕዝብና የኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ ዋልታ መሆናቸዉን መረዳት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች በብዙ መልኩ የተሣሠረ ሕይወት ያላቸዉ መሆናቸዉን የሚያምኑና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ችግሮች ተፈትተዉ ስቃይና መከራቸዉ ወደሚያበቃበት የመጨረሻ ግብ በሚያደርሰዉ ትግል ዉስጥ የበኩላቸዉን ሚና ለመጫወትና የሚፈለግባቸዉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ቆርጠዉ የተነሡ መሆናቸዉን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ኦዲግ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል በአጠቃላይ የተቃዋሚዎችን የፖለቲካ አሠራር ደግሞ በተለይ ከመሠረቱ መቀየር ያስፈልጋል፤ ከልብ ከታሰበበትና በጥንካሬና በድፍረት ተባብረን ከሠራን ደግሞ ይቻላል የሚል ጠንካራ እምነት ይዞ የተነሣ ድርጅት ነዉ፡፡ የፖለቲካ ባህላችንን የመለወጥ አስፈላጊነት ኦዲግ ከኢትዮጵያዉያን ግለሶቦችና በኢትዮጵያ ስም ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር የሚያደርጋቸዉ እንቅስቃሴዎች ድርጅቱ ለወደፊቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ መድረኮች ላይ እንዲኖር ለሚፈልገዉና ለተግባራዊነቱም ጠንክሮ ለሚሠራዉ የግልፅነት፣ የመተማመን፣ የመከባበር፣ የመተሣሰብ፣ የመቀራረብና የመፈቃቀር ባህል ለመነሻነት የሚጠቅሙ ናቸዉ፡፡ በአለፉት የወያኔ/ኢህዴግ የአገዛዝ ዘመናትም ሆነ ከዚያ በፊት የተደረጉትን የኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በጥልቀትና በጥሞና ስንመረምር በግልፅ የምንገነዘበዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአብዛኛዉ የሚታወቀዉ በተንኮል፣ በመጠላለፍ፣ በድብቅነት፣ በሸር፣ በምቀኝነት፣ አንዱ ሌላዉን ጥሎና በሌላዉ ላይ ተረማምዶ የበላይ መስሎ በመታየት፣ ባልሠሩት ሥራ ለመሞገስና ለመኮፈስ በመሞከር፣ ከሚያዉቁት በላይ ራስን አዋቂ አስመስሎ በማቅረብ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል ግትር አቋም፣ ከ”እኛ” “የእኛ” እና “ለእኛ” ይልቅ -- “እኔ” “የእኔ” እና “ለእኔ” የሚሉትን ራስ ወዳድ አመለካከቶች በማስቀደም ነዉ ቢባል “የለም ስህተት ነዉ” የሚል ቢኖር የአገራችንን የፖለቲካ ሂደትና የብዙዎቹን የፖለቲካ ድርጅቶቻችንን የገመድ ጉተታ ዓይነት አካሄድ በጥሞና ያልተከተታለ ወገን ብቻ ነዉ፡፡ ይህ የፖለቲካ ባህል ደግሞ መጠፋፋትንና እንዲለወጥ ከሚፈለገዉ የአገዘዝ ሥርዓት መዳፍ ዉስጥ በቀላሉ መዉደቅን ከማስከተል ዉጭ በአገሪቱ እንዲሰፍን የሚፈለገዉን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማምጣት እንዳላስቻለ፤ በአጠቃላይ ለሕዝቦቻችንና ለአገራችን ይጠቅማል ብለን ከምናምነዉ ግብ እንዳላደረሰንና እንደማያደርሰን የተቃዉሞ እንቅስቃሴያችን ባለበት መርገጥ ብቻም ሳይሆን ያለፉትና የዛሬዎቹ የአገራችን ችግሮችና የደሃዉ ሕዝባችን ከመኖር በታች ከመሞት በላይ የሆነ የስቃይ ኑሮ በቂ ምስክሮች ናቸዉ፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን “እኔ ያልኩት ካልሆነ” የሚል ግትር አቋም የትም አያደርሰንም፡፡ ብዙዎቹን ችግሮቻችንን በማያዳግም ሁኔታ ልንፈታ የምንችለዉ ካለምንም ማስመሰል በግልፅነትና በቅንነት መነጋገር ስንችል ነዉ፡፡ ዛሬ በጣም ጎልተዉ ለሚታዩት የሕዝባችንና የአገራችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ችግሮች የማያዳግም መፍትሔ ለማግኘት አርቆ አሳቢነት፣ ግልፅነት፣ ቅን አመለካከትና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሕዝባችንና ለሀገራችን አንገብጋቢ ችግሮች ቅድሚያ መስጠት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ አማካይነት የቀረቡ ሃሳቦችና ምናልባትም በሃሳቦቹ ላይ የሚደረጉ የአንባቢያን ዉይይቶች የግል መኖሪያ ቤታችንን ለማደስና የቤታችንን የዉስጥ ጉድለቶች ለማስተካከል እንደምንወስዳቸዉ የየራሳችን እርምጃዎች ተደርገዉ ቢታዩ ጥሩ ይሆናል፡፡ የራሱን መኖሪያ ቤት የሚያድስ ሰዉ “አቶ እከሌ ቤቱን አድሷል” ለመባል ብቻ ጥራት የሌላቸዉን የግንባታ ቁሳቁሶች እንደማይጠቀም ሁሉ እኛም ለጋራ አገራችን ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ብለን የምናቀርባቸዉ ሃሳቦች የተሸፋፈኑ፣ ማስመሰል የበዛባቸዉ፣ ድብቅ አጀንዳዎችን ያካተቱና በማር የተለወሱ መርዞች መሆን የለባቸዉም፡፡ በብዙዎቻችን ዕድሜና ተሞክሮ እንኳን ስናስብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያልተደረገ ጥናት፣ ያልተፃፈ ጽሑፍ፣ ያልተካሄደ ስብሰባ፣ ያልቀረበ የመፍትሔ ሃሳብ በአጠቃላይ ያልተሞከረ ሙከራ ያለ አይመስልም፡፡ ያለመታደል ሆኖ ግን ችግሮቻችን ተፈትተዉ ለማየት አልቻልንም፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ “ለምን?” ብሎ መጠየቅና ቆም ብሎም ማሰብ ይኖርበታል፡፡ ዛሬ የዓለም ሕዝቦች በስልጣኔ ላይ ስልጣኔ፣ በሃብት ላይ ሃብት፣ በምቾት ላይ ምቾት፣ በጥጋብ ላይ ጥጋብ፣ በደስታ ላይ ደስታ ለመጨመር ሌት ተቀን እየሠሩ ባሉበት ሁኔታ በተለያዩ የኢትዮጵያ ገጠሮች የሚኖሩ የብዙዎቻችን አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች እንደ ጥንቱ ሁሉ በበሬ ጉልበት በሚሳብ እጅግ ኋላ ቀር የእርሻ መሣሪያ እያረሱ፣ ሩቅ መንገድ በእግራቸዉ ተጉዘዉ የወንዝ ወይም የኩሬ ዉሃ ቀድተዉ እየጠጡ፣ በአብዛኛዉ ተመንጥሮ ካለቀ ጫካ ለምግብ ማብሰያ የሚሆን የማገዶ እንጨት ለመልቀም እየደከሙ፣ የተቦጫጨቀ ልብስ ለብሰዉ በባዶ እግራቸዉ እየሄዱ ሕይወታቸዉን ለማቆየት ይፍጨረጨራሉ፡፡ ይህም በዝቶባችኋል ተብለዉ ደግሞ ሰዉ በመሆናቸዉ ብቻ ሊኖራቸዉ የሚገባዉን የመብት ጥያቄ በማንሣታቸዉና ይልቁንም እንደ ነፃ ዜጎች በገዛ አገራቸዉና ዕትብታቸዉ በተቀበረበት ቄዬ ያለምንም ስጋት ሠርቶ የመኖር መብት እንዲኖራቸዉ በሰላማዊ መንገድ በመጠየቃቸዉ ብቻ በዛሬዎቹ የአገራችን ገዢዎች የጥይት መልስ እየተሰጣቸዉ ነዉ፡፡ ከዚህ ሁሉ መከራ ይሻል ይሆናል በማለት የስደትን መንገድ የመረጡ ወጣት ኢትዮጵያዉያንም በማያዉቁት አገር ባህርና ዉቅያኖስ ሬሳቸዉን እንኳ ፈልጎ ማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ የዉሃ ሽታ ሲሆኑ እያየንና እየሰማን ነዉ፡፡ ችግር አስገድዷቸዉ በጀመሩት የስደት ጉዞ ምክንያት ዉሃ ዉስጥ ሰምጠዉ ያለቁትንና የአዞ እራት የሆኑትን ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች ስናነሳ ብዙዎቻችን በመገናኛ ብዙሃን ያየነዉንና እስከዛሬም ድረስ ከእያንዳንዳችን አእምሮ ያልጠፋዉን፣ ሊጠፋም የማይችለዉን በአረመኔዎች የጭካኔ ብለዋ እንደ አገራችን የዓመት በዓል በጎች በአደባባይ የታረዱትን ወጣት ኢትዮጵያዉያንም ሣንዘነጋ ነዉ፡፡ በመካከለኛዉ ምሥራቅ ከሚገኙ የተለያዩ የዓረብ አገሮች ስለወጣት ኢትዮጵያዉያን ሴቶች በየጊዜዉ የምንሰማቸዉ እጅግ ዘግናኝ ዜናዎችም ከዚያች አገር በመፈጠራችን እንድናፍር፣ አንገታችንንም እንድንደፋ የሚያደርጉን እንጂ “እኔ እኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ!” ብለን በኩራት እንድንናገር የሚያደርጉን አይደሉም፡፡ ይህ ሁሉ መከራና ስቃይ የደረሰዉና እየደረሰ ያለዉ ደግሞ ብሄር፣ ቋንቋ፣ የትዉልድ ሥፍራና ሃይማኖት እየለየ አይደለም፡፡ ሁላችንም እንደምናዉቀዉ የሀገራችን ተከታታይ አምባገነን ገዢዎች በፈጠሯቸዉ ዉስብስብ ችግሮች ያልተጎዳ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ ይህን ሁሉ እያየንና እየሰማን ግን ከልብ ተቀራርበንና ተነጋግረን “ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ የሆነ ዘላቂ መፍትሔ እንዴት እንፈልግ?” እንደመባባል እዚህ ግባ የማይባሉ ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን የተራራን ያህል አግዝፈን ወደቀ ሲሉን ተሰበረን እየጨመርንበት ልዩነቶቻችንን የባሰ የሚያሰፉ፣ የመቀራረብ ተስፋችንን የሚያጨልሙ፣ ለባለጊዜዎቹ ራስ ወዳድ ገዢዎች ግን በጣም የሚመቹ አሳዛኝ የልዩነትና የመራራቅ መንገዶችን መከተልን የመረጥን እንመስላለን፡፡ በሚያቀራርቡን ሳይሆን የባሰዉኑ በሚያራርቁን ጉዳዮች ላይ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን፣ ዕዉቀታችንንና ገንዘባችንን እናጠፋለን፡፡ በመሆኑም በአካል ባንገናኝ እንኳ የዓለም ሕዝቦች ስንት ትልልቅ ቁም-ነገሮችን በሚሠሩባቸዉ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ዉጤቶች በሆኑ ድህረ- ገፆችና የማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ስንሰዳደብ እንዉላለን፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱት በኢትዮጵያ ሕዝቦች የተባበረ ትግል ብቻ ነዉ፡፡ በተወሰኑ ድርጅቶች ወይንም ቡድኖች ጥረት ወይም ደግሞ በምዕራባዉያን መንግሥታት እገዛና ተፅዕኖ ለዘርፈ-ብዙ ችግሮቻችን መፍትሔ ልናገኝ አንችልም፡፡ ራሳቸዉን “International Community” ብለዉ ከሚጠሩ ወይንም ደግሞ እኛ “የዓለም አቀፉ ማህበረ-ሰብ” ብለን ከምንጠራቸዉ አሜሪካ-መራሽ የምዕራብ ሀገራት ኃያላን መንግሥታት ምንም ዓይነት ድጋፍ መጠበቅ የለብንም፡፡ ለሃያ-አምስት ዓመታት በራቸዉን አንኳኩተንና ደጅ ጠንተናቸዉ ያተረፍነዉ ንቀትን ነዉ፡፡ ምናልባት የእነሱን ትኩረት መሳብና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ድጋፋቸዉን ማግኘት የምንችለዉ በምንግባባቸዉ ነጥቦች ላይ ተባብረን በመሥራት የተወሰኑ እርምጃዎችን ወደፊት ተጉዘን ለወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ጥሩ አማራጭ መሆናችንን በተግባር ማሣየት ስንችል ብቻ ነዉ፡፡ የኢትዮጵያን ዉስብስብ የሆኑ መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ከምንም በላይ በቅንነት፣ በንፁህ ልቦና፣ በአርቆ አሳቢነት፣ ከራስ ጊዜያዊ ጥቅምና ዝና በላይ ለወገን በማሰብ፣ ከምንም በላይ ደግሞ በራሳችን በማመንና እርስ በእርሳችን በመተማመን ተቀራርበን አብረን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በመናናቅ፣ በጥላቻ፣ በመወነጃጀል ብሎም ያለፈዉን ታሪካችንን ገንቢ ባልሆነ መልኩ ደጋግመን በማንሣት ወይም ፈፅሞ እንዳይነሣ በመከልከል ለችግሮቻችን መፍትሔ ማግኘት አንችልም፡፡ ወደድንም ጠላንም ችግሮቻችንን ልንፈታ የምንችለዉ አማካይ መንገድ ላይ ተገናኝተን በግልፅነት በመነጋገርና በመቻቻል አብረን ሥንሠራ ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በየትኛዉም መሥፈርት የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት መሆኑ ከማያጠያይቀዉ የኦሮሞ ሕዝብ አብራክ የወጡ ምሁራንና የፖለቲካ ሰዎች ከሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ተመጣጣኝ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ዕዉን ለማድረግ ደግሞ ቢያንስ የዘመኑ ሥልጣኔ ቁንጮ መሆኑ በማያጠያይቀዉ የምዕራቡ ዓለም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከመጡ የልዩ ልዩ አገራት ዜጎች ጋር አብሮ የመማር፣ የመኖርና የመሥራት ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያዉያን እጅግ በጣም ጠቃሚ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ በባዕድ አገራት ቋንቋቸዉ፣ ባህላቸዉ፣ ሥነ-ምግባራቸዉ፣ እምነታቸዉ ብሎም መልካቸዉ ከኛ በጣም ልዩ ከሆኑ ሰዎች ጋር ተቀራርበንና ተግባብተን ለመኖር ያልተቸገርን ሰዎች ከገዛ አገራችን ከመጣ ሰዉ ጋር የጋራ አገራችንንና ወገናችንን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በቅንነት መቀራረብና በግልፅነት መነጋገር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የረሃብ፣ የችግርና የስደት ምሳሌ ተደርጋ ከምትወሰድ አገር መጥተን ሌላዉ ቢቀር የጋራ ችግሮቻችንን በጋራ ስለመፍታት ማሰብ አለመቻላችን ሊያሣፍረን በተገባ ነበር፡፡ በግለሰብ ደረጃ የሚደረጉ መቀራረቦች ወደ ድርጅቶች አንድነትም ሊያመሩ ስለሚችሉ እስቲ የሚያራርቁንንና የሚያቃቅሩንን ጉዳዮች ትተን ሁላችንንም የሚመለከቱትንና በሚገባ ብናስብባቸዉ መልስ ልናገኝላቸዉ የምንችላቸዉን የጋራ ጥያቄዎች አብረን እናንሣ፡- ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች የዓለም ጭራ የሆነችዉ ለምንድነዉ? በጣም ታዋቂ በሆኑ የምዕራባዉያን ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚያስተምሩና በከፍተኛ ተመራማሪነት የሚታወቁ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ በሳል ምሁራንን ያፈራች አገር ሌላዉ ቀርቶ ዜጎቿን እንኳ መመገብ ያለመቻልዋ ሚስጢር ምንድነዉ? ኢትዮጵያዉያን የሌሎች አገሮች ሕዝቦች ያላቸዉን ዓይነት ለሕዝብ ፍላጎት ተገዢ የሆነ መንግሥት ሊኖረን ያልቻለበትን ምክንያት ማወቅ እንዴት ተሣነን? መቼ ይሆን ለዘመናት መልስ ያላገኙት የፖለቲካ ጥያቄዎቻችን በበቂ ሁኔታ መልስ አግኝተዉና የምንፈልገዉን ዓይነት መንግሥታዊ ሥርዓት መሥርተን ዲሞክራሲ፣ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት በሰፈነበት ሁኔታ የሕዝባችንን የታመቀ ችሎታ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና ማዋል የምንችለዉ? እነዚህና እነዚህን የመሣሰሉት ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ጉዳይ በቀጥታ ይመለከተናል፣ ያቺ አገር የሁላችንም የጋራ አገር ናት በምንል ወገኖች ሁሉ መመለስ የሚገባቸዉ ጥያቄዎች ናቸዉ፡፡ አንዱ ዘመን በሌላዉ፤ አንደኛዉ ገዢም በሌላ ገዢ እየተተካ ቢመጣም የሕዝባችን መከራና ስቃይ ግን እየባሰበት እንጂ እየቀነሰ አልሄደም፡፡ የዛሬዎቹ ገዢዎች ጭካኔና ራሰ-ወዳድነት ደግሞ በዚያች አገር ታሪክ ብቻም ሳይሆን በዓለም ታሪክም ታይቶ የሚታወቅ አይመስልም፡፡ በጥንካሬያቸዉ ሳይሆን በገዛ ድክመቶቻችን ምክንያት ግን ለሩብ ምዕተ-ዓመት ወደር በማይገኝለት ጭካኔ ቀጥቅጠዉ እየገዙን ብቻ ሳይሆን ሀገራችንንም እንደግል ንብረታቸዉ እየተጫወቱባት ይገኛሉ፡፡ ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን እንደአገራቸዉ፣ ሕዝቡንም እንደወገናቸዉ አይተዉ በማያዉቁ ጥቂት ዕብሪተኛና ራስ-ወዳድ ግለሰቦች ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ ተረግጠን የተገዛነዉና አሁንም የምንገዛዉ በወያኔ መሪዎች ጥንካሬ ሳይሆን በራሳችን ድክመት መሆኑን ልንክድ አንችልም፡፡ ትልቁ ድክመታችን ደግሞ በጋራ ቆመን መጠቃትን፣ መገፋትንና ዉርደትን እምቢ! ማለት አለመቻላችን ነዉ፡፡ ስለሆነም ይህን ድክመታችንን በጥልቀት መርምረን፣ የትግል ስልታችንን ለዉጤት ሊያበቃ በሚችል መንገድ በጥንቃቄ ቀይሰንና ለአገራችን ችግሮች መፍትሄ ፈላጊዎቹ እኛዉ ራሳችን መሆናችንን ከልብ አምነን በጋራ ለመታገል ቆርጠን ከተነሣን ከምንፈልግበት ግብ የማንደርስበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን የዛሬዎቹ ገዢዎች ጨቁኖ የመግዛቱን ተራ ለልጆቻቸዉ የማያሳልፉበትና ለሌላ ሩብ ምዕተ ዓመት ለመግዛት የሚያስችላቸዉን ማንኛዉንም ዓይነት ኢሰብዓዊ ድርጊት በሕዝባችን ላይ የማይፈፅሙበት ምክንያት የለም፡፡ በቅርቡ ለተደረገዉና እስከአሁንም ላልበረደዉ የኦሮሞ ሕዝብ ሰላማዊና ፍትሃዊ የመብት ጥያቄ የተሠጠዉ የጥይት መልስ፤ አሁንም የጎንደር ሕዝብ ላነሣቸዉ ተመሣሣይ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች የተሠጠዉና እየተሠጠ ያለዉ የጥይት መልስ የሚያሳየዉም ይህንኑ እዉነታ ነዉና የገዢዎቻችንን ዕብሪት መቋቋም፣ መመከትና ማሸነፍ የሚያስችሉ ስልቶችን የመቀየስ ተግባር ጊዜ ሊሰጠዉ የሚገባ ጉደይ አይደለም፡፡ የሃያ-አንደኛዉ ክፍለ ዘመን የፖለቲካ ሂደታችን እንግዲህ እከአሁን ያየናቸዉን አሣፋሪ ሁኔታዎች ለመቀየር የሚያስችለን መሆን ይኖርበታል፡፡ የትዉልዶች ጉዳይ የዛሬዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ የሀገራችንንና የሕዝባችንን ችግሮች ከራሳቸዉ የሕይወት ልምድና ተሞክሮ አንፃር በማየት የየራሳቸዉን የመፍትሔ አቅጣጫዎች ሊጠቁሙ ወይም ሊከተሉ የሚችሉ የተለያዩ ዘመናት ትዉልዶችን ተሣትፎ የሚጠይቅ ነዉና የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎች የተለያዩ ትዉልዶችን የሚወክሉ እንደሚሆኑ እሙን ነዉ፡፡ በቅድመ-ወያኔ ሥርዓት የጎልማሣነትና የወጣትነት ዘመን ዉስጥ ከነበረዉ ትዉልድ የምትመደቡ ወገኖቻችን ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ከመጡ ጓደኞቻችሁ ጋር ብዙ የሕይወት ተሞክሮዎችን አብራችሁ በማሣለፍ ብቻ ሳይሆን በአብሮ-አደግነት፣ በወንድማማችነትና እህትማማችነት፣ በትምህርት ቤት ጓደኝነት ወይም በሥራ ባልደረባነት ወዘተ የምትተዋወቁ፣ ምናልባትም የጥንቱና የስመ-ጥሩዉ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሣታፊ ትዉልድ አባላት በመሆናችሁ ከልብ ካሰባችሁበት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሊያግባባና ሊያቀራርብ በሚችል ደረጃ ለመነጋገር፣ ለመመካከር፣ ለመስማማት በጣም ከባሰ ደግሞ ላለመስማማትም ቢሆን ለመስማማት በአጠቃላይ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ከማንም በተሻለ መልኩ ተነጋግራችሁ የተራራቁ አመለካከቶችን ማቀራረብ ትችላላችሁ ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ ከዚያ ዉጭ ያለዉ አዲሱ ትዉልድ ደግሞ አብዛኛዉን ዕድሜዉን በዛሬዎቹ ገዢዎች መዳፍ ሥር ያሣለፈ በመሆኑ ታላላቆቹ ያለፉበትን ዓይነት ማህበራዊ ሕይወት እንዲያዉቅ ተደርጎ ያደገ ትዉልድ አይደለም፡፡ በተለያዩ ትዉልዶች መነፅር ሲታይ እንግዲህ አሁን ያለዉ የኢትዮጵያ እዉነታ የሚያሣየዉ ከምንም በላይ ለብሔር ማንነቱ ቅድሚያ የሚሰጥ ትዉልድ የአገር ኃላፊነትን ያህል ከባድ ሸክም ለመዉሰድ ከሚዘጋጅበት ደረጃ ላይ መድረሳችንን ነዉ፡፡ ይህን ኃላፊነት ለመወጣትና ሸክሙንም ለማቅለል የሚቻለዉ የኢትዮጵያዊ ማንነት መገለጫዎችን በአዲስ መሠረት ላይ በመጣል፣ አዲስ ህገ-መንግሥታዊ አርበኝነት ለመገንባት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የሆነ የጋራ ራዕይ መገንባት ስንችል ብቻ እንደሆነ የሚያመላክቱ እዉነታዎችን እየታዘብን ነዉ፡፡ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ካለማቋረጥ የተካሄደዉ የኦሮሞ ሕዝብ አመፅ የወያኔ ተቃዋሚ ነን የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችን ጨምሮ ከሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦች ያገኘዉ መልስ (የአሁኑ የጎንደር ሕዝብ አመፅ እስኪጀመር ድረስ) በጣም ዉስን መሆን የዚህ በብሔር ማንነት ዙሪያ ብቻ የመወሰንና ሌላዉን ወገን በጥርጣሬ የማየት ነፀብራቅ ብቻ ሳይሆን የጎደሉንና መሟላት ያለባቸዉ አዲስ የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች መኖራቸዉን በግልፅ ያመላከተ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ግን ይህ የኦሮሞ ሕዝብ አመፅ ትኩረቱን ሁሉ ያደረገዉ በገዢዉ ሥርዓት ፖሊሲዎችና በሥርዓቱ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ላይ ብቻ መሆኑ ለዚህ ለምናልመዉ ኢትዮጵያዊ አርበኝነት መሠረት ጥሏል ብለን እናስባለን፡፡ ሁላችንም እንደተከታተልነዉ የኦሮሞ ሕዝብ በመቶዎች እየተገደለና በሺዎች እየታሠረ ለወራት የዘለቀዉን ሰላማዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ያደረገዉና ወያኔዎች የሚይዙትንና የሚለቁትን እስኪያጡ ድረስ ያንቀጠቀጠዉ በወንዝ፣ በመንደር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በዕድሜ፣ ወይም በሌሎች ሊከፋፍሉት ይችሉ በነበሩ ጥቃቅን ነገሮች ሳይከፋፈል እንደ አንድ ሰዉ ሆኖ በጋራ በመቆም ነዉ፡፡ በአመፁ ፍሬያማ ዉጤቶች የተገኙ ከመሆኑም በላይ በኦሮሞ ልጆች አኩሪ መስዋዕትነት የሚፈለገዉን ድል ማስገኘት የሚያስችሉ ጠንካራ መሠረቶችም ተጥለዋል፤ እየተጣሉም ነዉ፡፡ እስከአሁን የተገኙት ዉጤቶች ደግሞ ይዋል ይደር እንጂ የወያኔ በሕዝባችን የጋራ ጠንካራ ትግል መዉደቅ አይቀሬ መሆኑን ያሣዩ ናቸዉ፡፡ በቅርቡ የተጀመረዉና ወያኔን ክፉኛ ያስደነገጠዉ የጎንደር ሕዝብ ጀግንነት የተመላበት የመብት ጥያቄ የሚያሳየዉም ይህንኑ የወያኔ በሕዝባችን የተባበረ ጠንካራ ትግል መዉደቅ አይቀሬ የመሆኑን እዉነታ ነዉ፡፡ አሁንም ድረስ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን እስከአፍንጫዉ በታጠቀ ታማኝነቱን ለሕዝብ ሳይሆን ለጥቂት ገዢዎች ባደረገ የወታደር ኃይል ታፍነዉ የተያዙት የኦሮሞና የጎንደር ሕዝብ የአመፅ እንቅስቃሴዎች የሚፈለገዉን ሰፊና አስተማማኝ ድል ለማግኘት እስከአሁን ካየነዉ የበለጠ መስዋዕትነትን ሊጠይቁ መቻላቸዉ እንደተጠበቀ ሆኖ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች እጅግ በጣም ጠቃሚ መልዕክት ማስተላለፍ ችለዋል -- በአንድነት ፀንቶ የመቆምንና ሞትን ያህል ከባድ ነገር ንቆ ላመኑበት ዓላማ ተባብሮ የመታገልን ጥቅም!! ማጠቃለያ ለጋራ ዓላማ በአንድነት የመቆምን የሕዝባችንን አኩሪ ተግባር እንዴት የበለጠ ማጠናከርና የወያኔ ተቃዋሚ የሆኑ የፖለቲካ ኃይሎችንም በአንድ ጥላ ሥር ማሰባሰብ ከሚቻልበት ደረጃ ላይ እንዴት ማድረስ እንደሚቻል በጥሞና የማየቱ ጉዳይ የእያንዳንዱ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ግንባር ቀደም ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡ እየመጣብን ያለዉን አገራዊ አደጋ ተገንዝበን እጅ ለእጅ ተያይዘን የመታገያ መንገዶችን ማመቻቸት ካልቻልን እስከ ዛሬ ያየናቸዉና አሁንም በተለያየ መልኩ እየቀጠሉ ያሉት የወገኖቻችንና የአገራችን ችግሮች ወደባሰ ደረጃ የሚሸጋገሩ ከመሆናቸዉም በላይ የሀገሪቱ ህልዉና ራሱ ጥያቄ ዉስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ኃይሎች ጥያቄ የአገራችን ሁለ-ገብ ችግሮች ወደባሰ ደረጃ እንዳያድጉ፣ አሁን ሥልጣን ላይ ያለዉን ጨቋኝ አገዛዝ ከማስወገድ ባሻገር ለዘለቄታዉ የኢትዮጵያን ሕዝቦች የነፃነት፣ የዲሞክራሲ፣ የፍትሕና የእኩልነት ባለቤቶች ለማድረግ እንዴት በጋራ መታገል እንደሚቻል ለመመካከርና በዚህ የጋራ ትግል አዲስ ኢትዮጵያዊነትን አብሮ ለመገንባት በሚያስችሉ ስልቶች ላይ በግልፅ ተመካክሮ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩል ተጠቃሚ ወደሚያደርግ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር የሚያስችለዉን መንገድ እንዴት በጋራ መጥረግ እንችላለን የሚል መሆን ይኖርበታል፡፡ በሁላችንም የጋራ ትግል እንደ አዲስ መመሥረት አለበት በምንለዉ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዉስጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዲሞክራሲ፣ የነፃነት፣ የፍትህና የሰብዓዊ መብት መከበር ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ያገኛሉ የሚል እምነት ይዘዉ የተነሡትና ለዚህ ደግሞ ሰፋ ያለ የዲሞክራሲና የነፃነት ኃይሎች የጋራ ግንባር ሊመሠረት ይገባል የሚል ጠንካራ አቋም የያዙት የፖለቲካ ኃይሎች አካሄድ የማይዋጥላቸዉ በሁለት የተራራቁ ጫፎች ፅንፈኛ አቋም ይዘዉ የቆሙ ጥቂት ወገኖች በየራሳቸዉ ምክንያት የመሃል መንገድ አካሄድን በጥርጣሬ ዓይን እንደሚመለከቱ ይታወቃል፡፡ ቢሆንም ግን ዲሞክራሲያዊ አመለካከት ያላቸዉን ኃይሎች ሊያቀራርብ የሚችል መካከለኛ መንገድ መከተል በሕዝቦችና በመንግሥት መሀል የነበረዉ የተዛባ ግንኙነት ላስነሳቸዉ ጥያቄዎች ተገቢዉን መልስ ለማስገኘት የሚያስችል ትክክለኛ ብቻ ሳይሆን አማራጭም የሌለዉ ነዉና ፅንፈኛ አመለካከቶችን በደፈናዉ ማዉገዝ ሳይሆን በዲሞክራሲያዊ ሂደት ለማቀራረብ መጣር ያስፈልጋል፡፡ እንደአዲስ የሚገነባዉ እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወንድማማችነትና እዉነተኛ አንድነት በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባ እንዲሆን ስለሚያደርግ በኦዲግ አማካይነት በተጀመረዉ አዲስ መንገድ ዳሩን ወደመሀል በመሳብ ፅንፈኛ አስተሳሰቦችን ማቀራረብ ብሎም ማስታረቅ ይቻላል፡፡ ወደሚፈለገዉ የመጨረሻ ግብ ለመድረስ ግን የአንድ ወገን ጥረት ብቻዉን በቂ ስለማይሆን የሁሉም አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዉያን ኃይሎች ጥረት ሊታከልበት ይገባል፡፡ ያ ደግሞ በተራራቀ ጫፍ የቆሙትን ወገኖች ሁሉ የኦዲግ መሥራቾች እንዳደረጉት ሁሉ ወደመሃል መንገድ ለመሄድ መወሰንና መሄድም የመቻል ብርታትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡

No comments:

Post a Comment