Wednesday, October 7, 2015



Fasil Yenealem
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሹመት
የሚኒስትሮችን ሹመት አስመልክቶ ብዙ አስተያየቶች ቀርበው አንብቤአለሁ። ሚኒስትር "ሀ" በ ሚኒስትር "ለ" መተካቱን በመግለጽ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብለው በተስፋ የተሞሉ አስተያየቶችን የሚሰጡ ሰዎች አንድ ያልተረዱት ነገር ያለ ይመስለኛል። ኢህአዴግ የሚመራው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና ነው ( አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባል የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ፍልስፍና አለ ወይ የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ)፤ መሰረታዊ የፖለቲካ መርሁም፣ ዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት (democratic-centralism) ነው። ዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ሌኒናዊ አስተሳሰብ ነው፣ የፓርቲው አባላት "ተወያይተውበት" በመሪው የጸደቀ ህግ፣ ሳይቀነስ ሳይጨመር ተግባራዊ ይደረጋል።
የኢህአዴግ ሚኒስትሮች ፈጻሚዎች ናቸው። ፖሊሲ የማርቀቅ ስልጣን ቢኖራቸውም፣ የሚረቀቀው ፖሊሲ ፓርቲው ከሚመራበት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና ውጭ ሊወጣ አይችልም፤ ፖሊሲው ህዝብን የሚጠቅም ሆኖ ነገር ግን ፓርቲው ፖለቲካውን ያበላሸዋል ብሎ ካመነ ውድቅ ይደረጋል፤ የፓርቲው ጥቅም ከህዝብ ጥቅም ቅድሚያ ይሰጠዋል:: Party interest takes precedence over people's interest. የፕሬስ ነጻነትን ማየት ይችላል። የፕሬስ ነጻነት ለህዝብ እጅግ ጠቃሚ ነገር ቢሆንም በፓርቲው ህልውና ላይ የሚያመጣው ስጋት መኖሩ ሳይታለም የተፈታ ነው። የፕሬስ ነጻነት ካለ ፓርቲው እንደፈለገ የሚገድልበት፣ የሚዘርፍበት፣ የሚጠረንፍበት... እድሉ እየጠበበ ይሄዳል። የፕሬስ ነጻነት የህዝብን መብት አስፍቶ የፓርቲን መብት ያጠባል። የአገራችን ፕሬስ ለህዝብ ቢጠቅምም፣ ለኢህአዴግ የህልውና ስጋት ስለፈጠረ በአብዮታዊ ጁዶ ተመታ። አብዮታዊ ዲሞክራሲ በአጭር አገላለጽ የጥርነፋ እና ዜጎችን መፈናፈኛ አሳጥቶ የመግዛት ፍልስፍና ነው። በአገራችን የመጠርነፊያው ዋና ስልት ደግሞ አንድ ለአምስት የሚሉት አደረጃጀት ነው። በአለም ላይ በዚህ መጠን ሰዎችን የጠረነፉ አገሮች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ሂትለር ዜጎቹን በአንድ ለ2 ሺ ሰው ነበር የጠረነፈው፣ የቀድሞው የምስራቅ ጀርመን ኮሚኒስት መሪ ኤሪክ ሆኒከር "አሻሽሎት" ዜጎቹን በ አንድ ለ69 ሰው ጠረነፋቸው፤ የኛዎቹ ደግሞ "እጅግ አሻሽለውት" በአንድ ለአምስት ይጠረንፋሉ። ሰሜን ኮሪያ በዜጓቿ ጭንቅላት ውስጥ በሰራቸው ከ70 አመታት በላይ በቆየ ስራ አንድ-ለአንድ መጠርነፍ ችላለች።
አሁን የተሾሙት ሚኒስትሮች ፣ የብቃት ደረጃቸው እንዳለ ሆኖ፣ እውነተኛ ስልጣኑን የያዘው ጥቂቱ ክፍል ከሚወስነው ውጭ ምንም ለማድረግ የማይችሉ " ስመ-ሚኒስትሮች" ናቸው። እንኳን ሚኒስትሮች የእነሱ ጠቅላይ የተባለው ሰው እንኳን ምንም ለማድረግ የማይችል " ስመ-ጠቅላይ ሚኒስትር" ነው። የሃይለማርያ ካቢኔ ከመለስ ካቢኔ የሚለይበት ባህሪም ይህ የመስለኛል፤ በመለስ ዘመን "ስመ-ሚኒስትሮች" በ ጠ/ሚኒስትር ይመሩ ነበር፤ በሃይለማርያም ዘመን ግን "ስመ-ሚኒስትሮቹ" የሚመሩት ከእነሱ ብዙም የተለየ ስልጣን በሌለው "ስመ-ጠ/ሚኒስትር" ነው። ሚኒስትሮቹም ሆነ ጠቅላያቸው የሚሾሙትና የሚሻሩት ለህዝብ በሰሩት ስራ ልክ ሳይሆን ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ ባላቸው ታማኝነትና አረዳድ ልክ ነው። ሿሚዎች ደግሞ ከጀርባ የማይታዩት " እነ እንትና" ናቸው። በምዕራብ አገራት የሃይል ሚኒስትሩ ለአንድ ሳምንት መብራት ቢያጠፋ፣ ስልጣኑን ሊለቅ ይችላል ምክንያቱም ሚኒስትሩ መብራት እንዳይቋረጥ የሚያደርግ ሙሉ ስልጣን ከሃላፊነት ጋር ተሰጥቶታልና። በአብዮታዊ መርህ ግን ይህ አይሰራም፤ ካጠፋህ አትጠየቅም፣ ምናልባት የሰራሃው ስራ የፓርቲውን ገጽታ የሚያበላሽ መስሎ ከታየም፣ ህዝብን ለማረጋጋት ሲባል፣ ቦታህ እንዲቀየር ተደርጎ ሌላ ስልጣን ይሰጥሃል።
በአብዮታዊ መርህ ግለሰቦች ከድርጅት በታች ናቸው፤ ድርጅት የሚባለው ደግሞ ሙሉ ስልጣን የያዘ አንድ ግለሰብ ( እንደ መለስ ዜናዊ) ወይም አሁን ስልጣኑን የያዙት ጥቂት ግለሰቦች ሊሆኑ ይችላሉ። የኢህአዴግን ሹመት በዚህ መነጽር ካየነው፣ የስመ-ሚኒስትሮች ቦታ መቀያየር፣ እንኳንስ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብሎ ተስፋ ማድረቅ ቀርቶ ለውይይት እንኳ ጊዜያችንን የምናባክንበት አጀንዳ አይመስለኝም።

No comments:

Post a Comment