Wednesday, November 4, 2015

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ) በጎንደር-አዘዞ፣ ጠዳ፣ ማክሰኝት፣ ቆላ ድባ፣ ደልጊ፣ ጭልጋና ሌሎች የወረዳ ከተሞች ላይ የመጠጥ ውሃና መብራት አግልግሎት በመቋረጡ ነዋሪዎች ችግር ላይ ናቸው፡፡ ====================================================


የህወሓት አገዛዝ በተለየ ሁኔታ በመሰረተ ልማት ሆነ ብሎ እያዳከማቸው ከሚገኙት የኢትዮጵያ ከተሞች ጎንደር አንዷ እና ዋነኛዋ ናት፡፡ ህወሓት ጎንደር እድገት እንዳታሳይ ብቻ ሳይሆን ባሏት የቆዩ ታሪካዊ እሴቶቿና ውበቷ ከዘመን ዘመን እየቆረቆዘች እንድትመጣ ተቆጥረው የማያልቁ ሸፍጦችን ፈፅሟል፡፡ በደርግ ዘመን ጎሃ ተራራ ላይ የተተከለውን ከተማዋን በበቂ ሁኔታ ሊያዳርስ የሚችል ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለውን ግዙፍ ጀነሬተር በጉልበቱ ነቅሎ ወደ ትግራይ በማስጫን ሃውዜን ላይ መትከሉን ሁሉም የጎንደር ነዋሪ በከፍተኛ ፀፀትና ቁጭት የሚገልፀው የሀወሓት ዓይን ያወጣ የዘረፋ ተግባር ነው፡፡
በተጨማሪም በአለፋ ጣቁሳ-ደልጊ እና ደምቢያ-ቆላ ድባ ይገኙ የነበሩ ሁለት ታላላቅ የተግባረ ዕድ ትምህርት ቤቶችን ቁሳቁሶች ሙልጭ አድርጎ በመዝረፍ ወደ ትግራይ ጭኗቸዋል፡፡ ከዕደ ጥበብ መማሪያ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ወድ ውድ ቁሳቁሶች በተጨማሪ አቢያተ መፅሐፍትም አብረው ተዘርፈው የማንበቢያ አዳራሾች መቀመጫ ወንበሮችን ብቻ ታቅፈው ኦና ሆነው ቀርተዋል፡፡ 
በጎንደር ከተማም ሆነ በቆላ ድባና በደልጊ የተፈፀመውን ከበቀል የመነጨ የህወሓት የማራቆት ነውረኛ ተግባር ህዝቡ ዝም ብሎ በፍርሃት እጆቹን አጣጥፎ አልተመለከተውም ነበር፤ ነገር ግን ጎጠኛው የህወሓት ቡድን ታንክ አሰልፎና መትረየስ ጠምዶ ያቃተውን ንጥቂያ አሳቻ ሰዓት ጠብቆና አዘናግቶ በደረቅ ሌሊት ህዝቡ በእንቅልፍ ላይ ሆኖ ባልሰማበትና ባላየበት ሊያከናውነው ችሏል፡፡

ሁለት ታላላቅ ጅረቶች አንደኛው ከሁለት ሰንጥቋት ሌላኛው አካሏት የሚያልፉባት ጥንታዊቷ የጎንደር ከተማ በመጠጥ ውሃ ችጋር ፍዳዋን እያየች በጨለማ ውስጥ እንድትኖር ህወሓት የተባለው የባንዳ ልጆች ቡድን ፈርዶባታል፡፡ በተለይም ደግሞ በወረዳ ከተሞቿ ችግሩ እጅግ በጣም የከፋና አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡
በጣና ሐይቅ አፍንጫ ላይ የሚገኙት ደልጊ፣ ማክሰኝትና ቆላ ድባ እንዲሁም ጭልጋና ሌሎች የወረዳ ከተሞች የሚጠጣ ጠብታ ውሃ አሮባቸው ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ በድቅድቅ ጨለማ ተውጠው ይገኛሉ፡፡
በእነዚሀ ጎስቋላ የጎንደር ወረዳዎች በተለይም ደግሞ በማክሰኝት ከተማ የውሃ ልማትና የመብራት ኃይል ቅርንጫፍ መ/ቤቶች የህወሓት ሎሌ የሆኑ የወረዳው ሹሞች መኖሪያ ቤቶች በሚገኙባቸው ሰፈሮች ብቻ እየለዩ ውሃ በገፍ በመልቀቅና መብራት በማብራት ድሃውን ህዝብ ዘወትር ያስጠሙታል፤ በጨለማ ያሳድሩታል፡፡

በተጨማሪም የጎንደር ዙሪያ ወረዳ /ማክሰኝት ከተማ/ የህወሓት አገልጋይ ካቢኔዎች ሲያሻቸው ጠዳ አሊያም ጎንደር እንዲሁም እስከ ባህር ዳር ድረስ ተጉዘው ውሃ በመቃረም የህዝቡ ንብረት በሆኑት የመስሪያ ቤት ተሽከርካሪዎች በበርሜል ጭነው እያጓጓዙ በመጠቀም ድሃውን ህብረተሰብ እንቁልልጭ ይሉታል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በእንፍራንዝ ከተማም ነዋሪዎች የሚጠጡት ውሃ የላቸውም፡፡ የከተማዋ የህወሓት አሻንጉሊት የብአዴን አባላት የሆኑ ሹሞች የመጠጥ ውሃውን ችግር ለመፍታት በሚል ህብረተሰቡን ገንዘብ እንዲያዋጣ ካስገደዱት በኋላ በብዙህ ሺህ የሚቆጠረውን ብር ወደየግል ኪሳቸው አስገብተውት በህዝቡና በሹሞች መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቶ ነበር፡፡
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ)

No comments:

Post a Comment