በኢትዮጵያ ውስጥ ለተንሰራፋው የህዝቡ የከፋ ድህነትና ስራ አጥነት መንስኤ የሆነው የህወሓት አምባገነናዊ አገዛዝ ድህነታቸውን ተጠቅሞ ዕልፍ አዕላፍ ወጣቶችን በአገር መከላከያ ስም በመመልመል በየጠረፉ በሚደረጉ የሽምቅ ውጊያዎች ውስጥ በመጨመር ያለቀባሪ በየበረሃው ወዳድቀው እንዲቀሩ በማድረግ በደምና አጥንታቸው የስልጣን ዘመኑን ለመቀጠል ሲፍጨረጨር መቆየቱ በግልፅ የሚታወቅ እውነታ ነው፡፡
በስልጣንና የንዋይ ፍቅር የነሆለለው ዘረኛው የህወሓት ቡድን ምስኪን ኢትዮጵያዊ እናቶች ኩበትና እንጨት ለቅመው ሽጠው፣ ለባለፀጋ ተገርደው በችጋር አለንጋ እየተገረፉ ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን ወደ ሶማሊያ ምድር በማስገባት በጥይት እያስጨፈጨፈ ሬሳቸው ሳይቀር በሞቃዲሹና በሌሎች ከተሞች ጎዳናዎች ላይ ልክ እንደውሻ በድን በገመድ ታስሮ እንዲጎተት እያደረገ በምስኪኖች ሞት እሱ ረብጣ ዶላር እያፈሰ ይገኛል፡፡
አሁንም ቢሆን ህወሓት ያንን የደም ቁማሩን በድሃ ልጅ ላይ መቆመሩን ቀጥሏል፡፡ እሱ ራሱ በሚፈፅመው ማባሪያ የሌለው ግፍና በደል ምክንያት በመላ አገሪቱ ተቃውሞ ተነስቶበት ህዝቡ ልቡ በረሃ ገብቶ በመሸፈቱና የአርበኝነት ትግል እያፋፋሙ የሚገኙ የነፃነት ድርጅቶች እንድ እየሆኑ ወታደራዊ ተክለ ቁመናቸው እየገዘፈ በመምጣቱ እንዲሁም በተጨማሪ በየጊዜው እያሰለጠነ ሲያከማቸው ለዓመታት በኖረው መከላያ ሰራዊቱ ላይም አንዳች እምነት በማጣቱ ምክንያት ስራ አጥ የሆኑ የድሃው ህዝብ ልጆችን በአገር መከላከያ ስም መልምሎ ለስልጣኑና ለጥቅሙ ሲል ብቻ እሳት ውስጥ ለመክተት በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
የህወሓት አገዛዝ ወጣቱን በዲስኩራቸው የሚያሳምኑ ካድሬዎችን አሰልጥኖ በየመንደሩ አሰራጭቶ በሶስት የማታለያ መንገዶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊ ጦር መልምሎ የማሰልጠን ስውር ዕቅዱን ለማስፈፀም ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛል፡፡
የህወሓት አገዛዝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊ ጦር መልምሎ የማሰልጠን ህልሙን ዕውን ለማድረግ ወጣቱን ያማልላሉ ብሎ ያወጣቸው ሦስቱ የማስመሰያ ቅጥር የሙያ መስኮች ለመከላከያ ኢንጅነርኢንግ ኮሌጅ ትምህርት፣ ለአየር ኃይል አብራሪነት እና ለልዩ ኮማንዶና አየር ወለድ የሚሉ ናቸው፡፡
በመሆኑም ለመከላከያ ኢንጅነርኢንግ ኮሌጅ ከፍተኛ ትምህርት በሚል ሰበብ ቴክኒክና ሞያ ት/ቤት ተመርቀው ስራ ማግኘት ያልቻሉትን በእግረኛ ተዋጊ ሰራዊትነት ለመመልመል ከፍተኛ ጉትጎታ ላይ ነው፡፡
ለአየር ኃይል አብራሪነት ደግሞ ከከዚህ ቀደሙ የመመልመያ መስፈርት በተለየ ሁኔታ በፊዚክስ፣ ሂሳብ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ "C" በቂ ነው የሚል አዲስ የቅጥር መስፈርት አውጥቷል፡፡
በየመንደሩ የተሰገሰጉት መልማይ ዲስኩራም ካድሬዎችም "ዳርፉር ሄዳችሁ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ብር ዝቃችሁ ትመለሳላችሁ..." በማለት ወጣቱን የእርጎ ባህር እያሳዩ ወላጆችን ደግሞ "ልጆቻችሁ በመንግስት ተምረው ኢንጅነርና ፓይለት እንዲሆኑላችሁ እና ከችጋር እንዲያወጧችሁ መምከርና በገሰፅ አለባችሁ..." እያሉ የድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ልጅ ደም በከንቱ እንደ ጅረት መፍሰሱን እንዲቀጥልና በአገራችን ላይ የተጫነው የባርነት አገዛዝ ዘመን እንዲራዘም ቀን ከሌሊት እየተጉ ነው፡፡
ህወሓት ከዚህ ቀደምም በ1980ዎቹ ዓ.ም መጨረሻ በመላ አገሪቱ የሚገኙ 12ኛ ክፍልን አጠናቀው ዩኒቨርሲቲ መግባት ያልቻሉ ወጣቶችን ለኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ስልጠና በሚል አታሎ በገፍ መልምሎ በሙያ ዘርፉ ከተመረቁ በኋላ የሚያገለግሉት "በአገር መከላከያ ልዩ ልዩ ክፍሎች ውስጥ እንደሆነና በመጀመሪያ ወታደራዊ ስልጠና መውሰድ ግዴታቸው እንደሆነ አሳምኖ ወደየ የእግረኛ ተዋጊ ማሰልጠኛ ማዕከሎች ካስገባና አሰልጥኖ ካወጣቸው በኋላ ቆይቶ በፈነዳው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ማግዶ ሁሉንም አስጨርሷቸዋል፡፡
የሀወሓት አገዛዝ ከማማለያው ጎን ለጎን የድሃው ህዝብ ልጅ የሆኑ ወጣቶችን አስገድዶ የመመልመል ሙከራም እያደረገ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ "በደቡብ ክልል" በጎፋ ሳውላና በቁጫ የሚኖር እያንዳንዱ ወላጅ ቢያንስ አንድ አንድ ልጅ እንዲያዋጣ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡
ሆኖም የህወሓት አገዛዝ የቱንም ያክል ማማለያና መደለያ ቢያቀርብ እንዲሁም በጉልበት ቢያስገድድ እስካሁን ድረስ ተታሎ አንድም የተመዘገበ ወጣት እንደሌለ እንዴውም በተቃራኒው ወጣቱ የሚደርስበት ጭቆና አንገሽግሾት እየተደራጀ ጫካ በመግባት ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
No comments:
Post a Comment