
በሃገር ውስጥ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከወራት በፊት የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ተክትሎ ኢትዮጵያን በመስቀለኛ መንገድ ውስጥ እንድትገባ ማድረጉን ለቱርኩ የዜና ወኪል በሰጡት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ከ500 የሚበልጡ ሰላማዊ ሰዎች በዚሁ ተቃውሞ መሞታቸውን የዘገበው የዜና አውታሩ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ውጥረቱ አሁንም ድረስ ዕልባት ሳያገኝ መቀጠሉን አመልክቷል።
የመንግስት ባለስልጣናት ህዝባዊ ተቃውሞው እልባት እንዳገኘ በተደጋጋሚ ቢገልጹም በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ጸረ-መንግስት የስራ ማቆም አድማና ተቃውሞ መቀጠሉ ታውቋል።
በሃገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳንዛ ድላሚኒ ዙማ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ካለው እርምጃ እንዲቆጠብ ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የቱርኩ የዜና አናዱላ በዘገባው አመልክቷል።
የአሜሪካ መንግስትን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ነው ያሉትን የሃይል እርምጃ በአስቸኳይ በማቆም ለህዝባዊ ጥያቄው ሰላማዊ ምላሽ እንዲሰጥ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
14 አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋር ጥያቄን በማቅረብ በመንግስት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ሃሙስ ይፋዊ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።
በተያዘው ሳምንት የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ይፈጸማል ያለውን ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማውገዝ ለሃገሪቱ የሚሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እንዲቋረጥ ያደረገ ሲሆን፣ ከሳምንት በኋላ የተባበሩትን መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ወደ ኢትዮጵያ ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
No comments:
Post a Comment