
ዛሬ የሃይማኖተኛ ህዝብ ሃገር በሆነችው ኢትዮጵያ የእምነት ነፃነት ጥያቄ በመጠየቃቸው በጥይት ተደብድበዋል፣ዜጎች በአደጉበት ባህል፣ ቋንቋ፣ስነ-ልቦናና ለማንነታቸው መሰረት የሆነውን ወግና ባህል ጠብቀው አስተዳደራቸውን ለመመስረት በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ በማቅረባቸው የመጨረሻ ውድ የሆነውን የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በ2008 ዓ.ም ማቅ ለብሳለች፡፡በሃዘን ተውጣለች፣መጨረሻውን ለመተንበይ በሚያስፈራ ሁኔታ ገዥዎቻችን በእብሪት ተወጥረው በሰላማዊ ህዝባችን ላይ የጥፋት ሰይፋቸውን እያሳረፉ ነው፡፡እጅግ የሚያሳዝነውና ልብ የሚሰብረው ነገር ይህንን ሁሉ በደልና ግፍ የሚፈፅሙት በፈጠሩት ብልሹ አስተዳደር ምክንያት 25 % የኢትዮጵያ ህዝብ በርሃብ አለንጋ እየተገረፈ ባለበት ጊዜ ነው፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ በአሳለፍነው ዓመት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በጉልበት ከተጫነበት አገዛዝ ተላቆ ህዝባዊ አስተዳደር ለመትከል በቆራጥነት ተነስቷል፡፡ለአዕምሮ የሚከብድ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡የታሪክ ቁርሾዎች ሳያግዱት ለመብቱና ለነፃነቱ በአንድነት ቆሟል፡፡ይህ ያሳየው አንድነት አሁን ባለው ትውልድና ለመጭው ትውልድ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡የኢትዮጵያን መዳከም የሚመኙ የሩቅና የቅርብ ጠላቶችን አንገት አስደፍቷል፡፡
ሃገራችሁን በመውደዳችሁና ለእውነት በመቆማችሁ ደማችሁ ለፈሰሰ፣አጥንታችሁ ለተከሰከሰ ዜጎች ሁሉ ኢትዮጵያ በክብር ታሪክ ስታስታውሳችሁ ትኖራለች፡፡በእናንተ አጥንትና ደም ተለውሳ በምትፈጠረው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የወደፊት ትውልዶች የመማሪያ መፅሃፍት ላይ ፎቶዎቻችሁን የምናይበት ዘመን እሩቅ አይሆንም፡፡
በመጨረሻም በ2008 ዓ.ም የታየው ቆራጥነትና አንድነት ተጠናክሮ 2009 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ህዝብ የድል ዘመን እንደሚሆን በፅኑ አምናለሁ፡፡አሁን ለተያያዝነው የነፃነትና የእኩልነት ትግልም ሰማያዊ ፓርቲ ከህዝብ ጎን በመሆን በሙሉ አቅሙ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ መወሰኑን በፓርቲያችን ስም እገልፃለሁ፡፡
መልካም አዲስ ዓመት ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
ጳግሜ 5 ቀን 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment