አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ከትግሉ አውደ ግንባር የጻፉትን ሳነብ ከአንድ ወጣት ታጋይ የቀረበላቸው አንድ አድርጉን የሚለው ጥያቄ ነበር ከሁሉም ቀልቤን የሳበው፡፡ ወያኔ ሀያ አራት አመት ገዝቶን አሁንም ለሌላ ተመሳሳይ አመት ግዞት የሚመኘን ተደጋግፈን መቆም፤ተጋግዘን መራመድ ተባብረን መታገል ባለመቻላችን እንደሆነ አንኳን እኛ ወያኔም የማይክደው ሀቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ሆኖ ማየት ነው አለማችን የሚሉ በሀገር ውስጥም በውጪም ያሉ፤ሰላማዊውንም የጠብ-መንጃውንም መንገድ የተከተሉ ድርጅቶች ሲሆን አንድ መሆን ካልሆነም መተባበርና በጋራ መታገል የማይቻላቸው ሆኖ መኖሩን ማወቄ ነው የወጣቱ ጥያቄ ቀልቤን አንዲስበው ያደረገው፡፡ ፓርቲዎች ወደ አንድነት ከመምጣት ይልቅ አብረው ፓርቲ የመሰረቱ እየተለያዩ ሌላ ፓርቲ በመመስረት ሲባዙ ማየቱ ነውና የተለመደው ለአቶ ኤፍሬም ከባድ ግን ወሳኝ የወጣቱ ጥያቄ ነበር፡፡ ( ታስበው ያልተሳኩት ባይታወቁም ተጀምረው ለውጤት ያልበቁትን ኢ.ዲ.ኃ.ቅ፤አማራጭ ኃይሎች፤ ጋፖመ፤ኢተፖድኅ፣ ትዴኢ፤ ኢሀጉ፣ ኢ.ዴ.ኃ.ኀ ፤ቅንጅት፤ ወዘተ እያልን መጥቀስና ማስታወስ እንችላለን)
የየፓርቲዎቹ አባላት ተለያይታችሁ አታስጠቁን አንድ ሁኑና አንድ አደርጉን የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ኖረዋል፤አሁንም ያቀርባሉ፡፡ደጋፊውም ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ ከማለት አልፎ በሚችለው አቅምና መንገድ ለመሸምገል፤ለማደራደር ብሎም ለማስገደድ ሞክሯል፡፡ግና አንድም ለውጤት የበቃ ተግባር የለም፡፡ በተግባር አንዳየነው የመተባበር ጅምሮች ሲከሽፉም ሆነ የተሰበሰበው ሲበተን የሚቀርቡት ምክንያቶች ለወሬም የሚበቁ አይደሉም፡፡ አይደለም ውህደት ለመፍጠር ለመተባበር የማያስችሉ በቂ ምክንያች በማንም መቼም ቀርበው አያውቁም፡፡ እኛ ለአመታት ታግለን እነርሱ ትናንት መጥተው ማለት፡ እራስን አተልቆ ሌሎችን አሳንሶ ማየት፤ ራስን ሀቀኛ ተቀዋሚ አድርጎ ሌላውን መናቅ፡ የመሪነቱን ቦታ ለራስ የአንበሳውን ድርሻ ለድርጅታቸው መፈለግ ወዘተ እነዚህ ናቸው ሰበብና ምክንያት እየሆኑ ፖለቲከኞቹን አላቀራረብ ሲሉ ለተቀራረቡትም መራራቅና መወነጃጀል ምክንያት ሲሆኑ የታዘብነው፡፡
ትግሉ ገና ዳዴ ማለት ሳይጀምር ስለ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ወንበር የሚያስቡም አሉ፡፡ እነዚህ የሀገር መሪነቱን እስኪያገኙ የፓርቲም ሆነ የግንባር፣ የጥምረትም ሆነ የውህደት መሪ ካልሆኑ በሌሎች የሚቀደሙና የሚያመልጣቸው አድርገው በመስጋት በሚፈጽሙት ተግባር ወንበሩንም ሳያገኙት ትግሉንም ሳይመሩት ይቀራሉ፡፡ ይህ መሰሉ ተግባር ተቀዋሚ እየተባሉ ከመኖርና ለወያኔ እድሜ ማራዘሚያ ከመሆን ያለፈ ሲፈይድ አላየንም፡፡ የሚገርመው ግን ይህ የሚያሳፍርም የሚያሳዝንም አለመሆኑ ነው፡፡
የመተባበርን ጥቅም የተረዱት የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሀኒቱ ፤ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ወዘተ በማለት የረገልጹታል፡፡ የዛሬዎቹ የመተባበር ጥቅሙ ባይጠፋንም ራስ ወዳድነትና የሥልጣን ህልመኝነት ከሁሉ ነገር በላይ ሆኖብን፤ከመደጋገፍ መነቃቀፍ ስራችን ሆኖ፣ መተባበር ዳገት ሆኖብን፤ እየተሰባሰብን ስንበታተን፤ተባበርን እያልን ስንለያይ፣ የመተባበርን ጠቃሚነት እየለፈፍን የመለያየት መርዝ ስንረጭ ለወያኔ እድሜ ማራዘሚያ መድሀኒት ሆነን ከዛሬ ደርሰናል፡፡ ስለዚህም ነበር የአቶ ኤፍሬምን ጽሁፍ ሳነብ ጠያቂው ታጋይ ወጣት መልስ ያገኝ ይሆን? አቶ ኤፍሬምስ ከባልደረባዎቻቸው ጋር ሆነው ለተጠየቁት ጥያቄ መልስ ማስገኘት ይችሉ ይሆን? በማለት ራሴን የጠየኩት፡፡
ከአንጀት ካለቀሱ አንባ አይገድም፡
ሁሉም በየተሰማረበት እንደመረጠው የትግል ስልትና አደረጃጀት የሚታገለው በርግጥ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከሆነ ከአንጀት ካለቀሱ አንባ አይገድም እንዲሉ አይደለም ጥምረት ውህደትም መፈጸም የሚገድ አልነበረም፡፡ ችግሩ በፕሮግራማቸው ከሚጽፉት በየዲስኩራቸው ከሚገልጹት በስተጀርባ ቀዳሚና ዋንኛ ጉዳይ መኖሩ ነው፤ እሱም የሥልጣን ጥም፡፡ ከንድ በላይ ፓርቲዎች በጥምረትም ሆነ በውህደት ወደ አንድ ሲመጡ የሚኖረው ቦታ አንድ ነው፤ሁሉም ደግሞ ያቺን ወንበር ይመኛሉ፡፡ እናም ያቺን ወንበር አንደማያገኙዋት ሲያውቁ አብ አሻፈረኝ ያላሉ፡፡ የሚመሩት ድርጅት አብዛኛው አመራርም ሆነ አባልና ደጋፊ ጥምረቱን ሆነ ውህደቱን ቢደግፍም ወሳኞቹ አነርሱ ናቸውና የሌለ ምክንያት ፈጥረው ያልሆነ አንቅፋት አስቀምጠው የተጀመረውን ያከሽፉታል፤የተወጠነውን ያፈሩስታል፡፡
ይህ ለአመታት ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ እያልን እየጮኽን መልስ ባለማጋኘታችን ሲያቆስለን የኖረ ሂደት ከሽፎ ዛሬ በአዲስ ዓመት ዋዜማ አራት ንቅናቄዎች የጋራ ግንባር መመስረት መቻላቸው እሰየው የሚያሰኝ የአዲስ አመት ብስራት ነው፡፡ ከይር ያሰማችሁ፤ ለድል የብቃችሁ፡፡ ይህ አድራጎታቸው ከምር ለትግሉ ራሳችውን መስጠታቸውንና ከልብ ለነጻነት ለመታገል መቁረጣቸወውን የሚያሳይ ነውና የየድርጅቶቹ አመራሮችና አባሎች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ያበርታችሁ፤ ወደፊት አንጂ ወደ ኋላ አያሳያችሁ ፡፡
መተማመን የሚዳብረው፣ አንድነት የሚጠነክረውና ትግሉም የሚሰምረው ወደ ኋላ የሚጎትቱ ነገሮችን እያስወገዱ ወደ ፊት ማየት ሲቻል ነው፡፡ ስለሆነም የአራቱ ድርጅቶች ህልው ሆኖ መቆየት ወደ ኋላ አንድታዩ የሚያደርጋችሁ በመሆኑ ይህን በቶሎ መልክ አሲያዛችሁ ወደ ፍጹም አንድነት እንደምትመጡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በኋላ አንደመሰረታችሁት ሀገር አድን ንቃናቄ አንጂ አንደ ተናጠል ድርጅቶቻችሁ ማሰብን ቀስ በቀስ ማስቀረት ይገባል፡፡የትናንት ትናናሽ ጎጆአችሁን እየተዋችሁ ትልቁን የጋራ ቤታችሁን ማጠናከር ነው፡፡ስለ ድሉ ስኬት መምከር ከወያኔ በኋላ ሊኖር ስለሚገባው መንግሥት አመሰራረት ማቀድ ወሳኝና ከባድ ስራ አለባችሁ፡ ስለሆነም ለትልቅ ኃላፊነት ትልቅ ሆኖ መገኘት ግድ ነውና አሁን ትልቅነታችሁን አሳይታችኋል፤ይበልጥ ትልቅ መሆን አንጂ ከዚህ በኋላ በአስተሳሰብም ሆነ በድርጊት አንሶ መገኘት አንደ ሀገሬ ሰው አባባል ግምኛ ነው፡፡
የሀገር አድን ንቅናቄው አባል ለመሆን ያልቻሉት ቀሪዎቹ ድርጅቶችም ያሳለፉትን የባከነ ግዜ በማሰብ በርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ አገዛዝ ተላቆ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አንዲበቃ ከሆነ አላማቸው በቶሎ መላ መላ ብለው የግለሰብም ይሁን የድርጅት ጉዳያቸውን መልክ አስይዘው ሀገር የማዳን ትግሉ አካል ሊሆኑ ይገባል፡፡
የወቅቱ ጥያቄ የብሄረሰብ፤ የኃይማኖት፤የፍህ ወይን የሰብአዊነት ሳይሆን የነጻነት ጥያቄ ነው፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ነጻነት የለም ብሎ የሚያምንና የሚታገለውም ራሱን ለሥልጣን ለማብቃት ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ ከሆነ የነጻነት ትግሉን በጋራ ለማካሄድ የሚገደው አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ ሞክረን ባቃተን የምናላዝን አስበን ባላተሳካልን የምናዝን፣ ባለፈ ታክ የምንወነጃጀል ሳንሆን በአዲስ ሀሳብ እየተመራን ያልተሄደበትን መንገድ እየፈለግን እየተመካከርንና እየተደጋገፈን ለጥቂቶች አሸናፊነት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ድል ወደፊት ! አንበል፡፡
መጪውን አመት የፍቅር የሰላምና የድል ያድርግልን
No comments:
Post a Comment