Wednesday, July 13, 2016

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ) በወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ሳቢያ በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉ ታወቀ፡፡



የህወሓት አገዛዝ የዜጎችን መብት አፍኖና እረግጦ ለመግዛት ያለ የሌለ ሃይሉን አሟጦ ለመጠቀም ቢሞክርም ከየ አቅጣጫው የተነሳበትን ህዝባዊ ተቃውሞ መቋቋም ተስኖትና ግራ ተጋብቶ ባለበት ወቅት በወልቃይት ህዝብ ማንነት ጥያቄ ሳቢያ ሰሞኑን በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት ዛሬም ተባብሶ ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ከቦታው የሚገኘው የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ ምንጫችን ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
የወልቃይት ህዝብ ያነሳውን የማንነት ጥያቄ ተከትሎ የህወሓት አገዛዝ የታጠቁ ሃይሎችን በስፍራው በማሰማራት ዝም ለማሰኘትና ወደ ክልል አንድ ተጠቃሎ ያለፍላጎቱ በግድ እንዲገዛ ለማድረግ ያደረገው ሙከራ አልሳካ ሲለው ለአገዛዙ የራስ ምታት ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን የወልቃይት ህዝብ የወከላቸውን ግለሰቦች አፍኖ ለመውሰድ ጥረት ቢያደርግም በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ሲከሽፍበት የክልል አንድን የፌደራልና ልዩ ሃይል አጓጉዞ በማምጣት ዛሬ ረቡእ ሐምሌ 6 ቀን 2006 ዓ.ም በተደረገው ተኩስ ልውውጥ ሞርተርና ዲሽቃ የተጠቀመ ሲሆን ከህዝብ በኩል ብዙ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ሠጠኝ ባብል እና ሲሳይ ተክሌ የተባሉ የአርማጭሆ ነዋሪዎች ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም አንድ የ5 ዓመት ህፃን በወያኔ ጥይት ተመትቶ መሞቱ ተረጋግጧል፡፡ በተያያዘ ዜና ማክሰኞ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም በመኖሪያ ቤቱ እንዳለ በወያኔ የታጠቁ ሃይሎች ተከቦ የነበረው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ በህዝብ ድጋፍ ከታፈነበት ወጥቶ ከህዝብ ጋር ተቀላቅሎ እየተዋጋ መሆኑን ምንጫችን ከስፍራው የላከልን መረጃ ያስረዳል፡፡ በዛሬው ዕለት በተደረገው የተኩስ ልውውጥ 13 የወያኔው የታጠቁ ሃይሎች ሲገደሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች መቁሰላቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪ የአገዛዙን ታርጋ የለጠፉ መኪናዎችን ጨምሮ ሁለት ሰላም ባስና 4 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በህዝቡ መቃጠላቸው የታወቀ ሲሆን ከትግራይ ክልል በመጡ የወያኔ ፌደራልና የደህንነት አባላት ድርጊት ህዝቡ በመበሳጨት ንብረትነታቸው የህወሃት አገልጋይ ግለሰቦች የሆኑ ሆቴሎችን ቡቲኮችንና ሱቆችን ያቃጠሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል ፍሎሪዳ ሆቴልና አፄ በካፋ ሆቴል ይገኙበታል ፡፡

No comments:

Post a Comment