Thursday, August 4, 2016

ባንድራዬን አየኋት! (ኤፍሬም ማዴቦ – ከአርበኞች መንደር) August 4, 2016


አዎ! ሰንደቅ አላማዬን አየኋት። ያቺን በልጅነቴ ጧት “ደሙን አፈሰሰ” ብዬ የሰቀልኳትንና ማታ “ተጣማጅ አርበኛ” ብዬ ያወረድኳትን አረንጓዴ፥ ብጫና ቀይ ሰንደቅ አላማዬን ጎንደር መስቀል አደባባይ ዉስጥ ስትዉለበለብ አየኋት። አየኋት . . . አየኋት ያቺን አለፍላጎቴ የለወጡብኝንና እኔን ሳይጠይቁ ባዕድ አካል የሸነቆሩባትን ባንድራዬን ጎንደር ዉስጥ አየኋት። ያቺ ከአባቶቼ ጋር አድዋና ማይጮ የዘመተችዉን፥ ወድቀን ስንሰበር አብራን የወደቀችዉንና ተነስታ ስትዉለበለብ ከወደቅንበት አቅፋ ያነሳችንን አረንጓዴ፥ ብጫና ቀይ ሰንደቅ አላማዬን ጎንደር ዉስጥ አየኋት። እሁድ ጁላይ 25 ቀን ጎንደር ያሳየችኝ ሰንደቅ አላማዬን ብቻ አይደለም። ጎንደር አልገዛም ባይነትን፥ ጽናትን፥ ቆራጥነትንና ጀግንነትን ሁሉንም አንድ ላይ አሳየችኝ። ጎንደር ህወሓት አጠፋሁት ያለዉን “ኢትዮጵያዊነት” አልጠፋም አለ አለችኝ፥ የቴዎድሮስንና የገብርዬን ጀግንነት አሳየችኝ። ጎንደር የነጻነቴ ቀን መቃረቡን፥ የፍትህ ጎህ መቅደዱንና የግድያ፥ የአፈናና የዝርፊያ ዘመን እያከተመ መሆኑን ነገረችኝ። አዎ! ጎንደር አደርገዋለሁ ያለችዉን ቃሏን አከበረች፥ ከህወሓት ነብሰ ገዳዮች ጋር ተናነቀች፥ የነጻነት አዋጅ አወጀች።

እሁድ ጁላይ 25 ቀን የጎንደር ህዝብ ለኢትዮጵያዉያን ወንድሞቹና እህቶቹ ህወሓት በተባበሩ ኢትዮጵያዉያን ፊት ገለባ መሆኑን ብቻ አይደለም ያስተማረዉ። ጡንቻ ራሶች ስለሆኑ አይገባቸዉም እንጂጎንደር ለህወሓት መሪዎችም “ሰላማዊ ሰልፍ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሀ . . .ሁ እየቆጠረች አስተምራቸዋለች። በተለይ “ሽብርተኞች ናቸዉ” እያሉ ሰላማዊ ሰልፈኞችን በየመንገዱና በየአደባባዩ ለሚጨፈጭፉት ነብሰ ገዳዮቹ የህወሓት መሪዎች ሽብርተኞቹ እነሱ እራሳቸዉ እንጂ ህዝብ አለመሆኑን ጎንደር በተግባር አሳይታቸዋለች። ህወሓት ሰላማዊ ሰልፈኞችን የሚጨፈጭፈዉ ሽብርተኛ ስለሆነ ነዉ። ባለፈዉ እሁድ ጎንደር ዉስጥ በተካሄደዉ ሰላማዊ ሰልፍ ህወሓት ወደ ሰላማዊ ሰልፈኛዉ ያልተኮሰዉ ለጎንደር ህዝብ አዝኖ አይደለም . . . እዛም ቤት አሳት እንዳለ ስላወቀ ነዉ። ወያኔን በሚገባዉ ቋንቋ ማናገር አለብን የምንለዉም ለዚሁ ነዉ . . . . ጡንቻ ራስ የሚገባዉ ጡንቻ ብቻ ስለሆነ!!!!
ጎንደር “ሰላማዊ ትግል” ከጠላት ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ እንጂ ልመና አለመሆኑን በተግባር አሳየች። በቃ! በቃ አለች ጎንደር ቆርጣ ተነሳች ለእኩልነቷ....እምቢ አለች ጎንደር ለክብሯ ለመብቷ፥እምቢ ...እምቢ...እምቢአለችጎንደርለነጻነቷእምቢአለች ጎንደር ለኢትዮጵያ ክብር ለአንድነቷ። ጎንደር ተቆጣች አገሬን ካልተዋችሁ አልተዋችሁም አለች። ጎንደር አኮራችኝ ፥ተነስ ብላ አነሳሳችኝ ፥ ቤቴ መጥታ እንሂድ አለችኝ. . . እንታገል ብላ በስሜ ጠራችኝ፥ እጄን ይዛ መስቀል አደባባይ ወሰደችኝ። ልቤን ማረከችዉ ጎንደር ጀግንነቴን ቀሰቀሰችዉ፥ ስጠፋባት ፈለገችኝ፥ ስደክምባት አጽናናችኝ፥ መላ ሲጠፋኝ መከረችኝ . . . . ጎንደር አለሁልህ አለችኝ። ሰላማዊ ትግል “ሰላም” እንጂ ሽብር አለመሆኑን አሳየችኝ። ጎንደሮች አትሰለፉም ሲባሉ እምቢ ብለዉ ተሰለፉ፥ የታጠረዉን በር ሰባብረዉ አለፉ አደባባይ ገብተዉ ነጻነት ለፈፉ። ጎንደር የልጆቿን ጥሪ ሰማች፥ ለወገን አደራ አደረች፥ መሃላዋን አከበረች ወልቃይትን መልሱልኝ. . . . ጠገዴን መልሱልኝ፥ ጸለምትን መልሱልኝ . . . . መልሱልኝ . . . . መልሱልኝ አለች!
እጄ መጻፍ አቅቶት ኩርሲ ላይ ቁጭ ብዬ ኢሳትን ስመለከት አንድ ጉድ ሰማሁና ለነጻነቴ፥ ለመብቴና ለእናት አገሬ አንድነት ለመታገል በረሃ ከመግባቴ ከጥቂት አመታት በፊት የህወሓቱ ተላላኪ አቶ ሃይለ ማሪያም ደሳለኝ ከአንድ አትላንታ ዉስጥ ከሚገኝ የአሉባልታ ሬዲዮ ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ትዝ አለኝ። ያ የተናገረዉም የሰማዉም ትዝ የማይለዉ “ማንትስ” የሚባለዉ ጠያቂያቸዉ ለጠየቃቸዉ ጥያቄ እንዲህ ብለዉ ነበር የመለሱት። ወላጅ አባቴ የኢህአፓ አባል ነበሩ። እኔ ያኔ ትንሽ ልጅ ብሆንም አንዳንዴ በኢህአፓ ጉዳይ ለአባቴ እላላክ ነበር። ወይ ጉድ! አልኩኝ ድፍረታቸዉም ቅሌታቸዉም ገረመኝና። ያ “ማንትስ” ያልኳችሁ ጠያቂያቸዉ ምግብ ስለሚወድ ሌላዉ ሰዉነቱ ነዉ ትልቅ እንጂ ጭንቅላቱ ትንሽ ነዉና እንዴት ብሎ አልጠየቃቸዉም። ዉሸት ደስ ስለሚለዉ ዉሸታቸዉን ደስ ብሎት ተቀበለ። ዬኔ አባት እንደ አቶ ሃይለ ማሪያም አባት የኢህአፓ አባል አልነበረም። እኔ ልጁ ግን ነበርኩ። የኢህአፓን እንደ ብረት የጠነከረ ዲሲፕሊን በሚገባ አዉቃለሁና አቶ ሃይለ ማሪያም በኢህአፓ ጉዳይ ለአባቴ እላላክ ነበር ሲሉ ነጭ ዉሸታቸዉ ወድያዉ ነዉ የታየኝ። ግን እኚህ የእምነት ሰዉ ነኝ የሚሉ ሰዉ የሰማይ ስባሪ የሚያክል ዉሸት መዋሸታቸዉ አይደለም የገረመኝ። እኔን የገረመኝ አቶ ሃይለ ማሪያም አሁንም ያኔም ዕድሜ ልካቸዉን ተላላኪ መሆናቸዉ ነዉ።
ይህንን የአቶ ሃይለ ማሪያምን እንደ ሪፓብሊካኑ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪ እንደ ዶናልድ ትራምፕ በየቀኑ የሚሰማ ቅሌት ያመጣሁላችሁ ወድጄ አይደለም። ይህንን ጽሁፍ ስጽፍ . . . ኢሳት ቴሌቪን ላይ አቶ ሃይለ ማሪያም “የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ የተመለሰዉ ከሃያ አምስት አመታት በፊት ነዉ” ብለዉ ሲቀልዱ ስለሰማሁ ነዉ። እኚህ ተላላኪ ሰዉ እንደሚሉት የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ከሃያ አምስት አመታት በፊት ተመልሶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ እሳቸዉም ተላላኪ አይሆኑም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉያንም በሰላምና በእኩልነት ይኖሩ ነበር።
ሐሙስ ጁላይ 22 ቀን ከኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉ የጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጆች ሁሉ “ይህ ሰልፍ ህወሓት ፈቀደም አልፈቀደ መካሄዱ አይቀርም” ብለዉ በልበ ሙሉነት ነበር የተናገሩት። ልበ ሙሉነታቸዉንና ቁርጠኝነታቸዉን ወደድኩት። ግን እነዚህ ጀግኖች ወገኖቼ ፊት ለፊት የሚጋፈጡት ፍጹም አረመኔ ከሆነ ጠላት ጋር ነዉና ሳሳሁላቸዉ። ሆኖም ደም ሳይፈስ ስርየት የለምና እሁድ ደርሶ ሰልፉን ለማየት ልቤ ተንጠለጠለ። “ሐሙስ... ልቤን አለዉ ደስ ደስ” ....በጣም ከምወዳቸዉ የአስቴር አወቀ ዘፈኖች አንዱ ነዉ። ሐሙስ የቀን ቅዱስ ነዉ። ዕድለኛዉ እኔ ልሁን ዉዷ እናቴ አላዉቅም . . . . እኔም የተወለድኩት ሐሙስ ቀን ነዉ። ሐሙስን እወደዋለሁ . . . . ሐሙስ ጁላይ 22 ግን እንደ ገመድ ረዘመብኝና ጠላሁት። አርብና ቅዳሜማ . . .ምነዉ ከሰባቱ ቀናት በተቀነሱ አሰኘኝ። እሁድ መጥቶ ጎንደርና መስቀል አደባባይ ሲገጥሙ ለማየት ጓጓሁ።
ቅዳሜ ጁላይ 24 ቀን “የማይነጋ ሌሊት” ተብሎ የተዘፈነለት ረጂም ሌሊት ነበር። ግን ዕድሜ ለኢሳት! . . . . ከዋሺንግተን ዲሲ መሳይን መኮንንን ከአመስተርዳም አፈወርቅ አግደዉን እየቀያየረልኝ ረጂሙን ሌሊት አሳጠረልኝ። በተለይ እንቅልፍ ሲያጃጅለኝማ አፈወርቅ አግደዉ ነበር መድሀኒቴ። የጎንደር ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ መሰለፍ የህወሓት ስጦታ ሳይሆን ህገ መንግስታዊ መብቴ ነዉና መሰለፍ አለብኝ ብሎ በድፍረት ሲነሳ የኔም ልብ ደፈረ። ደፋሩ ልቤ ብቻ ሳይሆን ይህንን ደፋር ልብ የተሸከመዉ ደካማዉ ሰዉነቴም ድፍረት አገኘና ጎንደር ገብቼ ካላደርኩ አለ። አዎ! ልቤ፥ አይኔ፥ እግሬና ሀሳቤ ጎንደር ገብተን ካላደርን አሉ። ለግዜዉ በአካል ባልችልም በምናቤ ጎንደር ገባሁና “ብታስሩኝ እታሰራለሁ ብትገድሉኝም ገድያችሁ እሞታለሁ እንጂ አንገቴን አጎንብሼ አልገዛም” ብሎ ቆርጦ የተነሳዉ የጎንደር ህዝብ መስቀል አደባባይን ሲሞላዉ ታየኝ። ቀና ብዬ ሰዐቴን ሳየዉ ዶሮ ሊጮህ ትንሽ ነዉ የቀረዉ። ሳላስበዉ እንቅልፍ ይዞኝ ጭልጥ አለ።
“ሰላማዊ ሰልፍ ክልክል ነዉ” የሚለዉን የጌቶቻቸውን ትዕዛዝ ለማስከበር ነብሰ ገዳዮቹ የአግዓዚ ወታደሮች ጎንደርን እንደ ጉም ከብበዋታል። ሁሉም የጎንደር በሮች ከቅዳሜ ማታ ጀምሮ በህወሓት ወታደሮች ተዘግተዋል። መስቀል አደባባይ እንኳን ሰዉ ወፍም ሾልኮ የሚገባበት ቀዳዳ የለዉም። ጎንደር ታጥራለች፥ ጎንደር ተዘግታለች፥ ጎንደር ተቆልፋለች። የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ አልቆለታል የሚሉት ህወሓቶችና “አገሬን ለሰዉ አልሰጥም ” እያለ የሚዘምረዉ የጎንደር ህዝብ ፊት ለፊት ተፋጥጠዋል። ዕብሪተኛዉ ወያኔ መሳሪያዉን ተማምኖ ቆራጡ ጎንደሬ ደግሞ በአላማዉና በወገኖቹ ተማምኖ አትሰለፍም . . . እሰለፋለሁ እየተባባሉ የቃላት ጦርነት ዉስጥ ገብተዋል።
“ሙሽራ ነሽ ጎንደር ይሰፋል ልብስሺ” እየተባለ ሲዘፈን እየሰማሁ ነዉ ያደኩት። ዛሬ ጎንደር ሙሽርነቱ ቀርቶብኝ ከልጆቼ ከወልቃይት፥ ከጠገዴና ከጸለምት ጋር ቆሜ በቀረሁ እያለች ነዉ። አዎ! ጎንደር እንኳን አዲስ ልብስ ሊሰፋላት “ዕድሜ ለህወሓት” አሮጌዉ ልብሷም ተገፍፎ እርቃኗን ቀርታለች። ዛሬ የጎንደር ምኞት አዲስ ልብስ መልበስ አይደለም ̧. . . . የድሮዉ ልብሷ እንዲመለስላት ነዉ። ጎንደር አለፍላጎቷ በመሳሪያ አስገድዶ ካገባት የሃያ አምስት አመት ባሏ ጋር መፋታት ነዉ እንጂ ሙሽርነት አትፈልግም።
የሀወሓት መሪዎች ፊትና ኋላ አይለዩም። በዛሬና በትናንትና፥ በዘንድሮና በአምና መካከል ያለዉ ልዩነትም በፍጹም አይገባቸዉም። ባለፈዉ አመት አሸንፈዉ ከሆነ ዘንድሮም የሚያሸንፉ ይመስላቸዋል። ትናንት እንዳሰኛቸዉ ገድለዉ ከሆነ ዛሬም የሚደግሙ ይመስላቸዋል። ወደፊት ሄደዉም አስበዉም አያዉቁም። ጉዟቸዉ፥ ዕቅዳቸዉ፥ ሀሳባቸዉና ህልማቸዉ ሁሉ ወደ ኋላ ብቻ ነዉ። አገራችን ኢትዮጵያንም አየወሰዱ ያሉት ወደኋላ ነዉ። ለዚህ ነዉ “ወያኔ ነዉ ከጫካዉ የወጣዉ እንጂ ጫካዉ ከወያኔ ዉስጥ አልወጣም” የሚባለዉ። አሁንም ጫካ ዉስጥ ስላሉ ነዉ ኦሮሚያ ዉስጥ መንፈቅ የዘለለዉን ህዝባዊ እምቢተኝነት በጽንፈኞች የተቀነባበረ ጸረ ልማት ሴራ ነዉ የሚሉት። አርባ ምንጭ ዉስጥ ህዝቡ በቃችሁን ብሎ ሲታገላቸዉ አስመራ ሽብርተኞች ላከችብን አሉ። ድፍን ጎንደር ወልቃይትን መልሱልኝ ድንበሬ ተከዜ ነዉ ብሎ ሲነሳ የ”ሻዕቢያ ተላላኪ” ብለዉ ሰደቡት። የኦሮሞ ህዝብ በጽንፈኞች የሚመራ ከሆነ፥ ደቡብ ኢትዮጵያ ጉዳዩ ከአስመራ ጋር ከሆነና የጎንደር ህዝብ የሻዕቢያ ተላላኪ ከሆነ ለመሆኑ ህወሓት እመራለሁ የሚለዉ የትኛዋን ኢትዮጵያ ነዉ? . . . 100% ተመረጥኩ የሚለዉስ በየትኛዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ነዉ?

በህይወቴ ደስ ብሎኝ የዘለልኩባቸዉ ብዙ ቀኖች አሉ። አዝኜ አንገቴን የደፋሁባቸዉ ቀኖችም አሉ። እሁድ ጁላይ 25 ቀን ጎንደር ሁለቱንም አንድ ላይ ይዛብኝ መጣች- ደስታዉንም ሀዘኑንም። ጎንደር የተመሰከረላት የጀግኖች አገር መሆኗን አዉቃለሁ። በእርግጥም ጎንደር ጀግና የምታበቅል ምድር ናት። ሆኖም በዛሬዋ ሆዳምና ከሀዲ አንገቱን ቀና አድርጎ በሚሄድባት ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አትችሉም ሲባል “መሰለፍ መብታችን ነዉ” ብሎ መሰለፍና “ህወሓት ይዉደም” እያሉ አደባባይ ላይ መጮህ ግን – ጀግንነት ብቻ ሳይሆን የዛሬ አንድ መቶ ስልሳ አመት አጼ ቴዎድሮስ ያሳዩን ጀግንነት ነዉ። ቴዎድሮስ የነጭ እጅ ሰዉነቴን ከሚነካዉ ጥይት ይንካኝ ብሎ ኢትዮጵያዊ መስዋዕትነትን አስተምሮን ያለፈ ጀግና ነዉ። ዛሬም በነዚያ ቴዎድሮስ በተመላለሰባቸዉ አደባባዮች ዉስጥ “ተላላኪዉ ህወሓት ይወደም” ብሎ የሚጮህ ህዝብ ማየት እኔን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚያኮራ ገድል ነዉ። አጼ ተዎድሮስን አላየኋቸዉም ወይም አለመታደል ሆኖ በሳቸዉ ዘመን አልኖርኩም። የማዉቃቸዉ ፍጹም ኢትዮጵያዊ በሆነዉ የጀግንነት ታሪካቸዉ ነዉ። የእኚህን ጀግና ሰዉ የመጨረሻ ቦታ መቅደላን ሳስብ ኢትዮጵያዊ አልበገር ባይነት ይታየኛል፥ ፍትህ ይታየኛል፥ ነጻነት ይታየኛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በኛ በልጆቿ የምትመሰረተዉ አዲስቷ ኢትዮጵያ ትታየኛለች። ይህ ኢትዮጵያዊ አልበገር ባይነትና አልገዛምማለትዛሬምጎንደርዉስጥአለ።ኦሮሚያዉስጥአለ።ደቡብኢትዮጵያዉስጥአለ..... ኢትዮጵያዉስጥአለ።በዚህ የማይደሰትና በዚህ ተስፋዉ የማይለመልም ካለ እሱ ህወሓት ብቻ ነዉ።
እሁድ ጁላይ ሃያ አምስት ቀን ጎንደር “ኢትዮጵያዊነት” በህወሓት የሚጠፋ የዋዛ ነገር ሳይሆን የህወሓት መጥፊያ ቁም ነገር እንደሆነ ለወዳጅም ለጠላትም አሳይታለች። በእርግጥም ባለፈዉ እሁድ መሳሪያ በታጠቁ የወያኔ ወታደሮች ዙሪያዉን የታጠረዉን መስቀል አደባባይ ሰብረዉ የገቡትን ጀግኖች ወንድሞቼንና እህቶቼን ሳይ ኢትዮጵያዊነት ሲገፉት ጠንክሮ የሚቆመዉ፥ ሲያጠፉት የሚለመልመዉ ሲያፈርሱት የሚገነባዉ ለምን እንደሆነ ታወቀኝ። እነዚህ ወገኖቼ መሳሪያ ከታጠቁ ነብሰ ገዳዮች ጋር የተጋፈጡት ባዶ እጃቸዉን መሆኑን ሳይ ደግሞ ጎንደርና ኦሮሚያ የሌሎች ኢትዮጵያዉያንን ሙሉ ድጋፍ ካገኙ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ከሚቀጥለዉ የጌታችን ትንሳኤ ሊቀድም መቻሉ ታየኝና ደስ አለኝ። ለምን ደስ አይበለኝ . . . . ህወሓት ጠፋ ማለትኮ አገሬን ኢትዮጵያን 25 አመት ሙሉ ቀስፎ የያዛት ነቀርሳ ተነቀለ ማለት ነዉኮ!
“ነጻነት ወይም ሞት” ብሎ የተነሳዉ የጎንደር ህዝብ ለተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ወገኑ ግልጽ የሆነ መልዕክት አስተላልፏል። ይህ ትግል የሱ ብቻ ወይም ለሱ ብቻ እንዳልሆነ መስቀል አደባባይ ላይ ባስተጋባቸዉ የተለያዩ መፈክሮች በግልጽ ተናግሯል። “ድምጻችን ይሰማ” ብሎ በመጮህ ይህ ትግል የእስልምና እምነት ተከታዮችና ክርስትያኖች በጋራ ማካሄድ ያለባቸዉ ትግል መሆኑን ተናግሯል። “ኦሮሚያ ዉስጥ የወገኖቻችንን ደም በግፍ ማፍሰስ ይቁም” በማለት የአማራንና የኦሮሞን ህዝብ የትግል አንድነት አረጋግጧል። “የህወሓት ዘመን ይብቃ” ብሎ በመዘመር የኢትዮጵያ ህዝብ ዘረኝነትን፥ ግድያን፥ ኢፍትሀዊነትንና አይን ያወጣ ዝርፊያን በህዝባዊ ትግል ደምስሶ ፍትህና እኩልነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ እንዲገነባ ጥሪ አድርጓል። ጎንደር ላይ የታየዉ አመጽና እምቢተኝነት የኢትዮጵያ ህዝብ የህወሓትን ስርዐት እንዴት መታገል እንደሚገባዉ አስተምሮ አልፏል። ህወሓትን አፍርሶ አዲስ ስርዐት መገንባት የሚቻለዉ የህወሓትን ህግ በማክበር ሳይሆን “እምቢ” በማለት ብቻ መሆኑን ጎንደር ላይ አይተናል። ጎንደር ህዝባዊ እምቢተኝነትና ህዝባዊ አመጽ ሲቀናጁ የኢትዮጵያን ህዝብ እንኳን ግዜዉ ያለፈበት ወያኔ ማንም እንደማይበግረዉ በተግባር አሳይቷል።በአይነቱም በጸባዩም በህወሓት ዘመን ከተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች ሁሉ ልዩ የሆነዉ የጎንደሩ ሰልፍ ከተካሄደ በኋላ አንዳንድ የገዢዉ ፓርቲ አሽከሮች ያንን የለመዱትን የጭቃ ጅራፋቸዉን ሲያጮሁ ተደምጠዋል። የጎንደር ህዝብ ግን ከምንም አልቆጠራቸዉም። “ከወደቁ በኋላ መንፈራገጥ ለመላላጥ” ብሏቸዉ ትግሉን ቀጥሏል። ሬዲዮ ፋና የጎንደር ህዝብ ይዞት የወጣዉን ሰንደቅ አላማ ህገወጥ ሰንደቅ አላማ ብሎታል። ለመሆኑ አረንጓዴ፥ ብጫና ቀዩ ባንዲራ የማን ባንዲራ ነዉ? የህወሓት? የሬዲዮ ፋና ወይስ የኢትዮጵያ ህዝብ? የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ላይ ህወሓት ባዕድ አካል ሲጭንበት የኢትዮጵያ ህዝብ ገና ከጧቱ አልተቀበለዉም። ምክንያቱም የኢትዮጵያንሰንደቅ አላማ የሚለዉጠዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እራሱ ነዉ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች አይደሉም። ለመሆኑ እንዴት ብንታይና ምን ያክል ብንናቅ ነዉ የሚመራትን አገር ኢትዮጵያን “አገሬ ኢትዮጵያ” ብሎ መጥራት የሚጠይፍና ባንዲራችንን ጨርቅ ብሎ ከለበሰዉ ልብስ ያሳነሳት መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያን ባንዲራ የሚለዉጠዉ? ሬዲዮ ፋና የጎንደርን ሰላማዊ ሰልፈኞች “የኢትዮጵያን አንድነት የሚሸረሽሩ” ጸረ ህዝብ ሀይሎች ናቸዉ ብሏል። እርግጠኛ ነኝ ሬዲዮ ፋናን ያበሳጨዉ የጎንደር ሰልፈኞች የኢትዮጵያን አንድነት የሚሸረሽሩ መሆናቸዉ አይደለም። ሬዴዮ ፋናን ያበሳጨዉ የጌታዉ የህወሓት ኢትዮጵያን የማፈራረስ የረጂም ግዜ ዕቅድ በጎንደር ጀግኖች መክሸፉ ነዉ። ወልቃይት ጠገዴ ከጎንደር ተቆርጦ ትግራይ ላይ ሲቀጠል የጎንደር ህዝብ ተቃዉሞዉን አሰምቷል፥ ግን በወቅቱ ኢትዮጵያን የተቆጣጠረዉ ሀይልና ወልቃይትን ቆርጦ ትግራይ ላይ የቀጠለዉ ሀይል አንድ በመሆናቸዉ ጎንደር አፉን ዘግቶ የቤት ስራዉን መስራት ጀመረ እንጂ የጎንደር ህዝብ የወልቃይትን ትግራይነት ለአንድም ደቂቃ ተቀብሎ አያዉቅም። የሰንደቅ አላማችንም ጉዳይ እንደዚሁ ነዉ። ህወሓት ህግ አዉጥቶ ከዚያ በህዝብ ከተጠላዉ ሰንደቅ አላማ ዉጭ ሌላ ሰንደቅ አላማ የሚይዝ ዜጋ በህግ ይጠየቃል ብሎ ህዝብን እስኪያስፈራራ ድረስ የህወሓትን ሰንደቅ አላማ የሚይዝ ቀርቶ የሚያየዉም አልነበረም። ፋና ሬዲዮ እንደ ጌታው እንደ ሀወሓት ወደ ኋላ ብቻ የሚያስብ ግዑዝ ዕቃ ስለሆነ ነዉ እንጂ ጎንደር ላይ የተሰማዉ ጩኸትኮ ባንዲራዉም ወልቃይትም የኛ ናቸዉና የነሱን ነገር ለኛ ተውልን የሚል ህዝባዊ ጩኸት ነው። “ህወሓት ይወገድ”፥ “ድምጻችን ይሰማ”፥ የኦሮሞ ወንድሞቻችንን ደም ማፍሰስ ይብቃ” እነዚህ መፈክሮች ኢትዮጵያ ዉስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ የሚስተጋቡ መፈክሮች ናቸዉ። ታዲያ እነዚህ መፈክሮች ጎንደር ዉስጥ በመሰማታቸዉ እንዴት ሆና ነዉ ኢትዮጵያ የምትሸረሸረዉ? ትጠነክራለች እንጂ! ደግሞስ የኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በህወሓት ጥይት እንደ ቅጠል ሲረግፉ አፉን ያልከፈተዉ ፋና ሬዲዮ ለምን ይሆን “የኦሮሞ ወንድሞቻችንን ደም ማፍሰስ ይብቃ” ሲባል እንደ ሞኝ ዘፋኝ ብቻዉን የሚንጫጫዉ? ለመሆኑ ምን ነበር ሬዲዮ ፋና የፈለገዉ? ደም እንዲፈስ ወይስ ደም እንዳይፈስ? መልሱን አልፈልግም . . . . አዉቀዋለኋ!!

የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት በታሪኩ አይቶትም ሰምቶትም የማያዉቀዉን ጥላቻ፥ ዕብሪትና ንቀት ሳይወድ በግዱ አስተናግዷል። ልጆቹን በነብሰ ገዳዮች ጥይት ተቀምቷል፥ ንብረቱን በአልጠግብ ባዮች ተዘርፏል፥ ማንነቱ በዘረኝነት አለንጋ ተገርፏል። አገሩን የሚወደዉ ኢትዮጵያዊ ያገሩ ለም መሬት ለባዕዳን ሲሸጥ ጥርሱን እየነከሰ አፉን ዘግቶ ተመልክቷል። አባቶቹ ደማቸዉን አፍስሰዉ ያቆዩለት ያገሩ ዳር ድንበር ለባዕዳን ገጸ በረከት ሆኖ ሲቀርብ አቅም ስላጣ ብቻ ዝም ብሎ ተመልክቷል። ዕብሪተኞቹ የህወሓት መሪዎች ግን ይህ ዝምታና ትዕግስት ግድ የለሽነትና ፍርሃት እየመሰላቸዉ የተናገራቸዉን ማሰርና መደብደብ፥ በቃችሁን ያላቸዉን ደግሞ በጅምላ መግደላቸዉን ተያያዙት። ዛሬ ይህንን ቅጣ ያጣ ዕብሪትና ማን አለብኝነት የኦሮሞ ህዝብ በቃ ብሎ ልጆቹ ፍትህ፥ ሰላምና እኩልነት በነገሰባት ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዲኖሩ እሱ በየቀኑ እየሞተ ነዉ። በነመለስ ዜናዊና ስብሐት ነጋ ማኒፌስቶ እንዲጠፋ የተፈረደበት የአማራ ህዝብ ላለመሞት እየሞተ ነዉ። ጀግናዉ የጎንደር ህዝብ የአግዓዚን ነብሰ ገዳዮች “እኔም ቤት እሳት አለ” እያላቸዉ ነዉ። በፌዴራሊዝም ስም አንድ ሙቀጫ ዉስጥ የተወቀጠዉ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ህወሓቶችን ከነሙቀጭችሁ ጥፉልኝ እያለ ነዉ። በየቀኑ ቦምብ የሚወርድባቸዉ የሶማሌ ወግኖቻችን ነጻነት፥ ፍትህና ዲሞክራሲ ወይም ሞት ብለዉ ከህወሓት ነብሰ ገዳዮች ጋር እየተዋደቁ ነዉ። በስኳርና በልማት ስም ከመሬታቸዉ የተፈናቀሉ የአፋር፡ የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ጀግኖች መሳሪያ አንስተዉ “ዱር ቤቴ” ካሉ ሰነበቱ።
የህወሃት መሪዎች ወደዱም ጠሉ ሰሞኑን በግልጽም በስውርም እንደነገሩን “ሳይቃጠል በቅጠል” ብለዉ ለሰላማዊ ሽግግር መንገድ ካልጠረጉ “ልክ እናስገባቸዋለን” ተብሎ የተዘበተበት የኦሮሞ ህዝብ ባቀጣጠለዉ የህዝባዊ እምቢተኝነት እሳት ተጠራርገዉ የመጥፋታቸዉ ጉዳይ የቀኖች ጉዳይ ነዉ። እስከዛሬ አማራ ኦሮሞ እያሉ ከፋፍለዉ ገዝተዉናል። ዛሬ አማራዉ “የኦሮሞ ወገኖቼን ደም በግፍ አታፍስሱ” እያለ ነዉ። የኦሮሞ ህዝብም “የጎንደር ህዝብ ትግል የኔም ትግል ነዉ” ብሎ ከአማራ ህዝብ ጋር ያለዉን የትግል አንድነት በየቀኑ እያረጋገጠ ነዉ። ህወሓት ሃያ አምስት አመት ሙሉ በየቦታዉ የለኮሰዉ የልዩነት እሳት እሱን እራሱን እያቃጠለዉ ነዉ። ህወሓት ተቃጥሎ አመድ እስኪሆን ድረስ ጎንደርና ኦሮሚያ ዉስጥ የተቀጣጠለዉ ህዝባዊ እሳት ኢትዮጵያ ዉስጥ በየቤቱ፥ በየቀበሌዉ፥ በየከተማዉ፥ በየወረዳዉና በየክልሉ መንደድ አለበት።
ባለፈዉ እሁድ ጎንደር መስቀል አደባባይ ዉስጥ የታየዉና ህወሓትን ያንቀጠቀጠዉ ህዝባዊ እምቢተኝነት አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ዉስጥ ከ1997ቱ ሱናሚ እጅግ በጣም በልጦ መደገም አለበት። ጎንደርና አዲስ አበባ ሁለቱም የደም ከተማዎች ናቸዉ፥ ሁለቱም ዉስጥ ደም ፈስሷል፥ ሁለቱም ዉስጥ ዜጎች የት እንደገቡ እንኳን ሳይታወቅ እንደ ሻማ ቀልጠዉ ቀርተዋል። የጎንደር መስቀል አደባባይ ይህንን በደልና ግፍ በቃኝ ብላ ህወሓትን ስታንቀጠቅጥ የአዲስ አበባዉ መስቀል አደባባይ ግፍና በደል ተሸክሞ ዝምታን የመረጠበት ምክንያት ምንድነዉ? መስቀል ጎንደርም አዲስ አበባም መስቀል ነዉ። ጎንደር ዉስጥ አገር እያዳነ አዲስ አበባ ዉስጥ ግድግዳ ላይ ተንጠልጥሎ የሚዝግበት ምንም ምክንያት የለም። ምነዉ አዲስ አበባዎች? እናንተ እንዳትሞቱ ነዉኮ ነቢዩ በልጅነቱ የተደፋዉ! የወገኖቼን ነገር አደራ ብላ እየጮኸች ነዉኮ ሽብሬ አንገቷን ለአግዓዚ ጥይት የሰጠችዉ! እስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌ፥ በቀለ ገርባና ኡስታዝ አቡበከር ቃሊቲን የመረጡት የእስር ቤት ኑሮ ናፍቋቸዉ አይደለም። እናንተ እንዳትታሰሩ ነዉኮ እነሱ የታሰሩት። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ህያዉ ሆነዉ ከትውልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፉት አንዱ ኢትዮጵያዊ ለሌላዉ ኢትዮጵያዊ ሲሞትና ሲታሰር ብቻ ነዉ። አዲስ አበባዎች ታዲያ ምነዉ ጎንደር ሲሞት እናንተ ዝም አላችሁ? ኦሮሚያ ዉስጥ አራስ እናትና ጡት የምትጠባ ህጻን አንድ ላይ ሲገደሉ አይቶ ዝም ማለት ከየት የመጣ ኢትዮጵያዊነት ነዉ? እናቷ ሆድ ላይ ተንጋልላ በአፏ የእናቷን ጡት የምትፈልግ ህጻን ጥይት ስትጎርስ አይታችሁ እንዲህ አይነቱን ግፍና ሰብዓዊነት የጎደለዉ ወንጀል ካልተበቀላችሁ ማን ወገን ብሎ ይፈልጋችኋል . . . . ማንስ ኢትዮጵያዊ ብሎ ይጠራችኋል? በተለይ ምስራቅ ኦሮሚያ በዴሳ ዉስጥ በህወሓት ነብሰ ገዳዮች የተገደለዉን ወጣት አስከሬን አቅፋ ኡኡ የምትለዉን ሴት ያየ ኢትዮጵያዊ እንዴት በህወሓት እየተገዛ ይኖራል? ምነዉ አዲስ አበባ? ምነዉ አዋሳ? ምነዉ ደሴ? ምነዉ መቀሌ? ምነዉ ባህርዳር? ይህንን ነዉ ኮሎኔል አብዲሳ ያስተማሩን? በላይ ዘለቀ ፍርሃት ነዉ ያስተማረን? ቴዎድሮስስ ዝምታና ሽሽት ነዉ ያስተማረን?
ህወሓት 17 አመት ጫካ ዉስጥ ሃያ አምስት አመት ደግሞ ስልጣን ይዞ ሊያጠፋዉ ሽንጡን ገትሮ የታገለዉ ኢትዮጵያዊነት አልጠፋ ብሎት አሁንማ ጭራሽ እሱን እራሱን መልሶ እያጠፋዉ መሆኑን ጎንደርና ኦሮሚያ ዉስጥ በግልጽ እያየን ነዉ። የኦሮሞ ህዝብ “ማስተር ፕላኑ” ግፍና መከራዉ ሲበዛብኝ ፈንቅሎ አነሳሳኝ እንጂ ትልቁ ጥያቄዬ ክብሬ፥ ሰብዓዊ መብቴና ነጻነቴ ሙሉ በሙሉ ተከብሮ ማየት ነዉ ብሎ አሁንም እየታገለ ነዉ፥ አሁንም እየሞተ ነዉ። የኦሮሞ ህዝብ የህወሓት ዘመን ካላበቃ ትግሌ አይቆምም ብሎ ቆርጦ ተነስቷል። ጎንደር “የወልቃይት ጎንደርነት” የሚረጋገጠዉ ህወሓት ሲጠፋ ነዉ ብላ ስለምታን ለዚህ እምነቷ ለመሞት ቆርጣ ተነስታለች። ሌሎቻችንስ? ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻዉን ታግሎ ብቻዉን ነጻ የሚወጣ ህዝብ የለም። የነጻነታችን ብቸኛዉ መንገድ አንድነታችንና ህብረታችን ነዉ። ጎንደር ሲያምጽ ጎጃምና ወሎ አብሮ ካላመጸ ጎንደርም፥ ጎጃምም ወሎም ነጻ አይወጡም። ህወሓት መጥፋት ካላበት ከየትኛዉም የኢትዮጵያ ክፍል ተነቅሎ መጥፋት አለበት። ይህ እንዲሆን ደግሞ ህወሓት ኦሮሚያ ዉስጥ ሲዋከብ ደቡብ ኢትዮጵያ ዉስጥም መዋከብ አለበት። የጎንደር ህዝብ እምቢ ብሎ ሲነሳ የአዲስ አበባ ህዝብም እምቢ ማለት አለበት። እኛ ኢትዮጵያዉያን ከተለያየን ያሻንን ያክል መሳሪያ ብንይዝ ወያኔን ማሸነፍ አንችልም። ከተባበርንና እንደ አንድ ሰዉ ከቆምን ግን እንኳን መሳሪያ ብትርም አያስፈልገንም- እምቢ ማለት ብቻ ይበቃናል። ሁላችንም አንገዛም እንበል፥ ሁላችንም እምቢ እንበል . . . . ሁላችንም በቃ እንበል . . . በቃ!
ቸር ይግጠመን- ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር
ebini23@yahoo.com

No comments:

Post a Comment