Friday, August 28, 2015

የማኅበረ ቅዱሳን ንዋያተ ቅድሳት ማምረቻ ክፍል ቃጠሎ ደረሰበት

ማህበረ ቅዱሳን በድረገጹ እንደዘገበው:- በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር የንዋያተ ቅድሳት ማምረቻ ክፍል ነሐሴ 18 ቀን 2007 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ቃጠሎ እንደደረሰበት የልማት ተቋማት አስተዳደር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ፍስሐ ገለጹ፡፡ መረጃው ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እንደደረሳቸው የገለጹት አቶ ኃይሉ በማምረቻ ክፍሉ ተከስቶ የነበረውን ቃጠሎ በአካባቢው ሕዝብና በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ወረዳ የእሳት አደጋ ማጥፊያና መቆጣጠሪያ ክፍል አባላት ርብርብ ወደ ሌሎች ክፍሎች ሳይዛመት በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በቃጠሎው 12 የልብስ ስፌት ማሽኖች፤ 2 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ካውያዎች፤ 1 መዘምዘሚያ ማሽን፤ 1 ቁልፍ መትከያ ማሽን፤ በዝግጅት ላይ የነበሩና ያልተጠናቀቁ፤ ለስፌት የሚያገለግሉ የግሪክ ጨርቆች፤ የካህናት፤ የዘማርያንና የሰባኪያን አልባሳት፤ ለአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተዘጋጁ አልባሳት፤ የግሪክ ጣቃ ጨርቆች፤ የማምረቻ ክፍሉ በሮች፤ መስኮቶችና ኮርኒስን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡ ግምታቸውንም ለጊዜው ማወቅ እንዳልተቻለ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ ቀኑን ሙሉ መብራት ጠፍቶ ስለነበር ምንም ዓይነት ሥራ አገልጋዮቹ እንዳለከናወኑ የገለጹት ዳይሬክተሩ ቃጠሎው የተከሰተው አገልጋዮቹ ከወጡ በኋላ በመሆኑ የአደጋው መንስኤ እሰካሁን አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡ አደጋው የተከሰተበት ምክንያት ፖሊስ የቴክኒክ ምርመራ በማካሔድ ላይ ስለሚገኝ ምርመራው እንደተተናቀቀ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል፡፡ ወደፊት ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ኃይሉ ከኢንሹራንሽ ጋር በተያያዘም ወደፊት የሚሠሩ ሥራዎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡ በቃጠሎው ከፍተኛ ጉዳት ሳይደርስ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ላደረጉ አካላት ለአራዳ ክፍለ ከተማ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መቆጣጠሪያ ጣቢያ፣ ለአካባቢው ምእመናንና ፖሊስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በንዋያተ ቅዱሳት ማምረቻ ውስጥ የአልባሳት፤ የመባ /ዕጣን፤ ጧፍ፤ ዘቢብ/ ዝግጅት፤ የተማሪዎች አልባሳት፤ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉና በእንጨት የሚዘጋጁ ንዋያተ ቅድሳት እንዲሁም የብረታ ብረት ሥራዎች ይመረታሉ፡፡ - See more at: http://wkidusanww.zehabesha.com/amharic/archives/46245#sthash.Y6HFeE9j.dpuf

No comments:

Post a Comment