Thursday, September 14, 2017

Teddy Afro - Mar eske Twauf (ማር እስከ ጧፍ) | New Official Video - 2010/2017

(Surafel Real Habesha)
⇩⇩⇩
በአምለሰት ሙጬ ተዘጋጅቶ በማያ ፊልም ፕሮዳክሽን
የቀረበ የፍቅር እስከ መቃብር አጭር ታሪክ!!! (የሙዚቃ
ቪዲዮ ከምል ይልቅ አጭር ፊልም ብለው ስራውን
በደምብ ይገልፃል)
☞ ገና ቪዲዮ ሲጀምር "ማር እስከ ጧፍ" ተብሎ
የተፃፈበት መንገድ በራሱ የሙዚቃውን ሀሳብ
ይገልፀዋል። ማር አንድም ይጥማል አንድም ጧፍ ሆኖ
ይነዳል። ይነዳል የሚለው ቃል በራሱ ኹለት ትርጉሞች
ይኖሩታል። አንድም መንደድ/መቃጠል ሲሆን ሌላው
ደግሞ መናደድ ነው። በግጥሙ ላይም እንደተመለከትነው
☞ ማር እስከ ጧፍ ሁኖ ዓለም ቢነዳቸው ☜ ይላል
ሰብለወንጌል ዓለም በቃኝ ብላ መመነኗን እንዲናገር!!!
☞ ቪዲዮ ሲቀጥል አስቀድሞ የተዜመ የግዕዝ ቃል አለ።
"ዝ ጠላ ከመ ወይን ጣዕሙ
እስኩ ድገሙ ድገሙ እስኩ ድገሙ"
ይህ ጠላ እንደ ወይን ይጥማል። ድገሙ እንደማለት ነው።
(የግዕዝ ዕውቀት የለኝም) ☞ ሰብለወንጌል የንጉሥ ዘር
ያለበት ቤተሰብ ውስጥ ነበር የምትኖረው። ስለዚህም
በቤታቸው ጥዑም የሆነ ጠላ እንደ ወይን የሆነ ተትረፍርፎ
እንደሚገኝ ያወሳል። ነገሩ ጠላ ተባለ እንጂ ውስጣዊ
ትርጉሙ ከማር የተሰራ የሚጣፍጥ ጠጅ እንደማለት ነው።
ይህንንም በቪዲዮ ውስጥ ጠጅ ሲጠጡ አስመልክቶናል።
ስለዚህም ሰብለወንጌል ሁሉ ነገር የተትረፈረፈበት የንጉሥ
ቤት ውስጥ እንደምትኖር ያመሰጥራል።
☞ አሁንም ይህ ድንቅ ቪዲዮ ሲቀጥል ሎሬቱ የክቡር
ዶክተር ሐዲስ አለማየሁን ፍቅር እስከ መቃብር እያነበበ
እና የከያኒ ወጋየሁ ንጋቱን ትረካ እየሰማ ያሳየናል።
ትረካውም እንዲህ ይላል " ... የተከደኑ አይኖቹን ገለጥ
አድርጎ ከፊቱ የቆሙትን መነኩሴ አየና "ሰብለ" አለ ጣር
በሚጎትተው ድምፅ ... " ይላል። በዛብህ ሰብልዬን ፍለጋ
ከሀገር ሀገር ሲዞር በአጋጣሚ ሽፎታዎች በደበደቡት ጊዜ
ሰብለወንጌል መንኩሳ ኖሯል ለካ!!! ሰብልዬም በዛ ጊዜ
በዛብህ መሆኑን አላወቀችም ነበር። "ሰብለ" ሲላት ጊዜ
ግን በዛብህ እንደሆነ አወቀች። ልታድነውም ጣረች። ነገር
ግን በጣም ተደብድቦ ነበርና በዛብህ ሊተርፍ አልቻለም።
በዛብህ ከተቀበረበት መሬት አጠገብ ሰብልዬ ለራሷ
ጉድጓድ አስቆፍራ ነበር። (ስትሞት ከአጠገቡ እንድትቀበር
ዘንድ) ይህንን ታሪክ ሊያስቃኘን ወደደና ይህን ትረካ
አስገባው ሎሬቱ!!!
☞ ከዚህ ለጥቆ ሎሬቱ ማንበቡን ገታ አድርጎ ሃሳብ
ውስጥ ሲገባ ዋናው የሙዚቃ ቪዲዮ ይጀምራል
የ ማር እስከ ጧፍ ግጥምም ዋና ሀሳቡ ከላይ
እንደተገለፀው ☞ በዛብህ የሰብልዬን ምንኩስና
በተመለከተ ጊዜ ምን ይናገር ነበር? የሚለው ነው።
ይህንንም በቪዲዮ ውስጥ ባማረ ሁኔታ ተመልክተነዋል።
☞ የሙዚቃ ቪዲዮ ባማረ ሁኔታ (በጥሩ ሁኔታ ከተሰራ
ፊልም ጋር በሚመሳሰል መልኩ) እስከመጨረሻው
ይዘልቃል። በተለይም የሰብልዬ እና የፊትአውራሪ መሸሻ
ገፀባህርያት ትወና የሚደንቅ ነበር።
በዚህ ድንቅ ሥራ መሀል የተካተቱትን ኹለት ቦታዎች
ብቻ ጠቀስ ላድርግ
① ጉዱ ካሳ ሰብለወንጌል ከመነኮሰች በኋላ ከሷ ዘንድ
ሲሄድ እና
② ፊትአውራሪ መሸሻ ፈረስ እየጋለቡ ሳለ ፈረሱ ከገደል
ጥሏቸው ሲሞቱ (እዚህ ጋር እንኳን ሰው ፈረስም
ይተውናል የሚያስብል ነው) ፊትአውራሪ ሲሞቱ ሰብልዬ
ላይ የነበረው ሀዘን የአምለሰትን የትወና ብቃት
ይመሰክራል።
☞ ሙዚቃው ከተገባደደ በኋላ ሎሬቱ በድጋሚ የፍቅር
እስከ መቃብርን መፅሐፍ እያነበበ (የሚያነበው መፅሐፍ
ያረጀ ነው። የፍቅር እስከ መቃብርን ታላቅነት በእርጅናው
አሳይቶናል) የከያኒ ወጋየሁ ንጋቱ ትረካ ይንቆረቆራል።
(የመተረኪያው ራዲዮም በድሮ ጊዜ የነበረ መሆኑ
የትረካውን ዕድሜ ያሳያል) ①* " ... ጉዱ ካሳ እና ሰብለ
በተገናኙ በአስራ አምስተኛው ቀን ሰብለ የልብ በሽታዋ
ተነሳ እና እንደልማዷ ወደቀች። ነገር ግን ዳግም
አልተነሳችም!!! " ከዚህም በኋላ ሰብልዬ አስቀድማ
ባዘጋጀችው መቃብር ከበዛብህ አጠገብ ተቀብራ
# ፍቅር_እስከ_መቃብር ሆነ። ጉዱ ካሳም አብሮአቸው
ተቀበረ።
☞ በስተመጨረሻም ይህን ሥራ ለክቡር ዶክተር ሐዲስ
አለማየሁ እና ለከያኒ ወጋየሁ ንጋቱ አበርክቷል። እዚህም
ጋር ለፊተኞቹ የሚገባቸውን ክብር በሚገባቸው ሥራ
ሰጥቷል። ብዙ ሰዎችን ካመሰገነ በኋላ በልዩ ምስጋና ላይ
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በቅድሚያ አመስግኗል። ይህም
የሙዚቃው ቪዲዮ ሲሰራ ታሪክ ሳያዛባ በጥበብ እና
በጥንቃቄ እንደሰራው ያሳየናል።
# እናመሰግናለን_ቴዲያችን
ፍቅር ያሸንፋል!!
https://m.youtube.com/watch?feature=youtu.be&v=u2inQ1WeaFs

No comments:

Post a Comment