Friday, May 11, 2018

አቶ አባይ ጸሃዬን ጨምሮ አራት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተባረሩ (ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 3/2010)አቶ አባይ ጸሃዬን ጨምሮ አራት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተባረሩ። ለኢሳት በደረሰው የስንብት ደብዳቤ ላይ እንደተመለከተው አቶ አባይ ጸሀይን ጨምሮ አራቱ ባለስልጣናት ከስልጣናቸው የተነሱት ሚያዚያ 11 እና 12/ 2010 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ ነው። በሁለት ተከታታይ ቀናት የስንበት ደብዳቤ የደረሳቸው ባለስልጣናት ከአቶ አባይ ጸሐዬ በተጨማሪ ጠቅላይ ዐቃቢ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ፣ የመለስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ቴድሮስ ሐጎስ፣ እንዲሁም የኢንሳ ምክትል ዳይሬክተር ኮሎኔል ታዜር ገብረ እግዚአብሔር ናቸው። ለአቶ አባይ ጸሐዬ ሚያዚያ 12/ 2010 ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የተጻፈው ድብዳቤ ከመጋቢት 09/2006 ጀምሮ በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማግልግል ላይ መሆናቸውን ያስታውሳል። ላበረከቱትም አስተዋጽኦ ምስጋና በማስቀደም ከሚያዚያ 12/2010 ጀምሮ ከሃላፊነት የተነሱ መሆናቸውን ይገልጻል። ለሌላው የሕወሃት አመራር ለአቶ ቴድሮስ ሃጎስ በተመሳሳይ ቀን የተጻፈው የስንብት ደብዳቤ አቶ ቴድሮስ ሃጎስ ከህዳር 15/2008 ጀምሮ የመለስ ዜናዎ ስራ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገል ላይ መሆናቸውን ይገልጻል። ከምስጋና ጋርም ከሚያዚያ 12/2010 ጀምሮ ከሃላፊነት የተነሱ መሆናቸውን ደብዳቤው ያመለክታል። የሃገሪቱ የሳይበር የስለላ ተቋም ማለትም ኢንሳ ምክትል ዳይሬክተር ለሆኑት ለኮለኔል ታዜር ገብረእግዚአብሔር በርሔ የተጻፈውም የስንብት ደብዳቤ ከየካቲት 14/2006 ጀምሮ በዚሁ ሃላፊነት ላይ እንደነበሩ በመዘርዘር ከሚያዚያ 12/2010 ጀምሮ ከሃለፊነታቸው መነሳታቸውን ከምስጋና ጋር ይገልጻል። ከሶስቱ የህወሃት ሰዎች በተጨማሪ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ለብአዴኑ አቶ ጌታቸው አምባዬ የተጻፈው የስንብት ደብዳቤም ከመስከረም 25/2010 ጀምሮ በጠቅላይ አቃቤ ሕግነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን በማስታወስ ከሚያዚያ 11/2010 ጀምሮ ከምስጋና ጋር ከሃላፊነት መነሳታቸውን ያመለክታል። እነዚህ ከሃላፊነት ተነሱ ከተባሉት ግለሰቦች ሶስቱ ዛሬ የትና በምን ሃላፊነት ላይ እንዳሉ የሚታወቅ ነገር የለም። የስንብት ደብዳቤ የደረሳቸውና የኢንሳ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ኮለኔል ታዜር ገብረእግዚአብሔር ግን ትላንት በተሰጠው ሹመት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው መሾማቸው ተሰምቷል። ሆኖም ከስኳር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ በቢሊየን ብር ስርቆት ጉዳይ የሚነሱት አቶ አባይ ጸሃዬ እንዴት በሕግ አይጠየቁም የሚሉ ድምጾች በመሰማት ላይ ናቸው። የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ እና የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ክንፈ ዳኘው በሌሎች ሰዎች መተካታቸው ይታወሳል። ሁለቱም የህወሃት ታጋዮች ናቸው።