Wednesday, May 24, 2017

የስፓርት ሜዳዎች ለሕዝባዊ ትግል መፋፋም አገልግሎት ይዋሉ!

May 24, 2017
የህወሓት አገዛዝን በመሰለ አፋኝ ሥርዓት የሚገኝ ሕዝብ ለተቃውሞ መግለጫነት የሚያገለግሉ አጋጣሚዎችን ሁሉ መጠቀሙ ብልህነት ነው። ብሔራዊ፣ ባህላዊና የሀይማኖት በዓላት፤ የሙዚቃ ድግሶች፤ የስፓርት ሜዳዎች፤ ትምህርት ቤቶችና ገበያዎች ለተቃውሞ መነሻነት ምቹ ናቸው። እነዚህን ሁሉ በአግባቡ መጠቀም ለሁለገብ ትግል ውጤታማነትና ሕዝብን ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አላቸው።

በተለይ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በርካታ ሕዝብ በጠባብ ቦታ የሚሰበሰብባቸው በመሆኑ፤ አብዛኛው ተመልካችም በእድሜ ወጣትና ንቁ ስለሆነ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ለመቀስቀስ የተመቹ ቦታዎች ናቸው። በአገራችን በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን በእስከ ዛሬ ልምድ የእግር ኳስ ሜዳዎቻችን በዚህ ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽዖ እጅግ አነስተኛ ነው። የእግር ኳስ ሜዳዎቻችን የሕዝብ ብሶት መግለጫ ከመሆን ይልቅ አፋኙ ሥርዓት የሚያሰራጫቸው ዘርና አካባቢን መሠረት ያደረጉ ልዩነቶችን ማራገቢያ ሲሆኑ ይስተዋላል።

በቅርቡ በመቀሌና ባህርዳር ከነማ ቡድኖች መካከል ተደርጎ በነበረው የእግር ኳስ ጨወታ እንደተስተዋለው የእግር ኳስ ሜዳዎቻችን የሕዝብ ሜዳ ከመሆናቸው ይልቅ የህወሓት ሜዳ እየሆኑ ነው። ሜዳዎቻችን አብሮነት የሚወደሰበት፤ ኢትዮጵያዊነት የሚከብርበት፤ ወዳጅነት የሚጎለብትባቸው ቦታዎች ከመሆን ይልቅ የህወሓት የዘር ፓለቲካ ሥር የሚሰድባቸው ቦታዎች እየሆኑ ነው። ይህ ማብቃት አለበት!
እግር ኳስን በስፓርትነት ብቻ ሳይሆን በተቃውሞ መሣሪያነት ጭምር መታየት አለበት። የኳስ ሜዳ መዝሙሮችና ዘፈኖች ወኔ ቀስቃሽ፣ አገራዊና ፀረ-ህወሓት አገዛዝ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። የእግር ኳስ ሜዳዎቻችን ልዩ ልዩ የአካል፣ የድምጽ፣ የምስል የተቃውሞ ምልክቶች ማስተዋወቂያና መሞከሪያ መድረኮች መደረግ አለባቸው።
እርግጥ ነው የአገዛዙ ሥርዓት አገልጋዮችም ይህንን የሚያውቁ በመሆኑ ተቃውሞዎችን ለማፈን ከፍተኛ የፓሊስና የወታደር ኃይል ይጠቀማሉ። በዚህም የተነሳ ከፍ ያለ ዓላማ ያነገቡ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ወደ ዘርና የቡድን ግጭቶች እንዲወርዱ በማድረግ የህወሓት ከፋፍለህ ግዛ መሠሪ ፓሊሲ ማስፈፀሚያዎች እንዲሆን የተቻላቸውን ሁሉ ሊያደርጉ እንደሚችል  ይጠበቃል። እኛ ግን ይህ እንዲሆን በፍጹም መፍቀድ አይኖርብንም።
ግንቦት 5 ቀን 2009 ዓ. ም. የመቀሌ ከነማ እና የባህርዳር ከነማ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ስቴዲዮም ባደረጉት  የእግር ኳስ ግጥሚያ የተከሰተው ግጭት ህወሓት የእግር ኳስ ሜዳዎችን እንዴት ለዓላማው ማሳኪያነት እንደሚጠቀም አንድ የቅርብ ጊዜ ማሳያ ነው። ይህ መደገም የለበትም። የኳስ ሜዳዎችን ድባብ በኢትዮጵያዊ አርበኝነት ስሜት መሸፈን ይገባል።
ከእንግዲህ ሜዳዎቻችን የህወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓት የሚወገዝባቸው እንጂ እርስ በርስ መዘላለፊያ እንዳይሆኑ መጣር ያስፈልጋል። የአገዛዝ ሥርዓቱ ደጋፊዎቹ በዝተው በተገኙባቸው ሜዳዎች፤ የእነሱ ፉከራዎች፣ ዛቻዎችና ስድቦት ጎልተው የሚሰሙ ከሆነ፤ እነሱ በጀመሩት መስመር ከመጓዝ ጫወታውን ትቶ መውጣት ይሻላል። ከእንግዲህ የኳስ ሜዳዎችን የትግል ሜዳዎች አድርገን መመልከት ይኖርብናል። ስለሆነም እንደማንኛው ትግል በስልትና በጥበብ መመራት ይኖርብናል።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከእንግዲህ የኳስ ሜዳዎቻችን የህወሓት መፈንጫ መሆን የለባቸውም፤ ይልቁንም የሕዝባዊ ተቃዉሞና የሕዝባዊ እምቢተኝነት ማቀጣጠያ አምባ መሆን አለባቸው ይላል፤ ለዚህም እያንዳንዱ ስፓርት አፍቃሪ የእግር ኳስ ሜዳዎችን ለሕዝባዊ  ትግል መቀጣጠል እንዲጠቀምበት ያሳሳባል።
አንድነት ኃይል ነው!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!

No comments:

Post a Comment