እያንዳንዱ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ሊሳተፍባቸው ከሚችሉ የህቡዕ ጦርነት ስልቶች ውስጥ አሻጥር፣ የስነ-ልቦና ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ጦርነት፣ እና ኢህአዴግን እርስበርሱ ማናከስ የተባሉት ለአብነት እንደማቀርብ ቃል ገብቼ ነበር። ሶስቱን ባለፉት ተከታታይ ክፍሎች አቅርቤዓለሁ። ይህ ክፍል “ኢህአዴግን እርስ በርሱ ማናከስ” ላይ ያተኩራል።
መ. ኢህአዴግን እርስ በርሱ ማናከስ
ከታወቁ የጦርነት ስልቶች አንዱ ጠላትን ከፋፍሎ ማጥቃት ነው። ጠላት ከላይ ግዙፍና ጠንካራ ሊመስል ይችላል፤ ሆኖም መፍራት አያስፈልግም፤ ውስጡን በጥንቃቄ መመልከትና የተሰራባቸው ክፍልፋዮችን ለየብቻ ማጥናት ይገባል። ከዚያም ደካማዎቹን ክፍሎች በማጥቃት ጠንካራ የሚመስለውን ጠላት በቁርጭራጭ መጨረስ ይቻላል።
“የህወሓት አገዛዝ” ስንል ህወሓት ብቻ የሚገዛ ከመሰለን ትክክል አይደለም። እያንዳንዱ የኢህአዴግ ድርጅት ለየብቻ መጠናት ይኖርበታል። አራቱ፣ ማለትም ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴግና ደህዴግ ቀዳሚ ትኩረት የሚሹ ናቸው። እንዲሁም አጋር ድርጅቶች የሚባሉት አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ እያንዳንዳቸው በተናጠል ሊጠኑ ይገባል።
በዚህ ተከታታይ ጽሁፍ ክፍሉ ሶስት ላይ አንድ አስተያየት ሰጪ ተረብ በሚመስል መንገድ “እያንዳንዱ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ” ማለት ምን ማለት ነው ሲል ጠይቆ ነበር። እነሆ እመልሳለሁ፤ “እያንዳንዱ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ” ማለት ከህወሓት ዘረኛና ፋሺስታዊ አገዛዝ ነፃ መውጣት የሚናፍቅ ኢትዮጵያዊ ማለት ነው።
በህወሓት አገዛዝ የተማረርነው ከኢህአዴግ ውጭ ያለነው ኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለንም። ከህወሓት አገዛዝ ነፃ መውጣትን የሚናፍቁ ዜጎች ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድ ውስጥ አሉ። ከህወሓት አገዛዝ ነፃ መውጣትን የሚናፍቁ ዜጎች አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ ውስጥ አሉ። ከህወሓት አገዛዝ ነፃ መውጣትን የሚናፍቁ ዜጎች ህወሓትም ውስጥ አሉ። ይህን ስል እነዚህ ድርጅቶች ህወሓት የፈጠራቸው ባሮች ስብስቦች መሆናቸውን ዘንግቼ አይደለም።