Sunday, March 20, 2016

የወቅታዊ ተግባራዊ ትግል (ወተት) መልዕክት: በግልጽ ጦርነት ውስጥ ካልሆን በህቡዕ ጦርነት እንሳተፍ ! (ክፍል 4: የመጨረሻ) ዶ/ር ታደሰ ብሩ


እያንዳንዱ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ሊሳተፍባቸው ከሚችሉ የህቡዕ ጦርነት ስልቶች ውስጥ አሻጥር፣ የስነ-ልቦና ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ጦርነት፣ እና ኢህአዴግን እርስበርሱ ማናከስ የተባሉት ለአብነት እንደማቀርብ ቃል ገብቼ ነበር። ሶስቱን ባለፉት ተከታታይ ክፍሎች አቅርቤዓለሁ። ይህ ክፍል “ኢህአዴግን እርስ በርሱ ማናከስ” ላይ ያተኩራል።
መ. ኢህአዴግን እርስ በርሱ ማናከስ
ከታወቁ የጦርነት ስልቶች አንዱ ጠላትን ከፋፍሎ ማጥቃት ነው። ጠላት ከላይ ግዙፍና ጠንካራ ሊመስል ይችላል፤ ሆኖም መፍራት አያስፈልግም፤ ውስጡን በጥንቃቄ መመልከትና የተሰራባቸው ክፍልፋዮችን ለየብቻ ማጥናት ይገባል። ከዚያም ደካማዎቹን ክፍሎች በማጥቃት ጠንካራ የሚመስለውን ጠላት በቁርጭራጭ መጨረስ ይቻላል።
“የህወሓት አገዛዝ” ስንል ህወሓት ብቻ የሚገዛ ከመሰለን ትክክል አይደለም። እያንዳንዱ የኢህአዴግ ድርጅት ለየብቻ መጠናት ይኖርበታል። አራቱ፣ ማለትም ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴግና ደህዴግ ቀዳሚ ትኩረት የሚሹ ናቸው። እንዲሁም አጋር ድርጅቶች የሚባሉት አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ እያንዳንዳቸው በተናጠል ሊጠኑ ይገባል።
በዚህ ተከታታይ ጽሁፍ ክፍሉ ሶስት ላይ አንድ አስተያየት ሰጪ ተረብ በሚመስል መንገድ “እያንዳንዱ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ” ማለት ምን ማለት ነው ሲል ጠይቆ ነበር። እነሆ እመልሳለሁ፤ “እያንዳንዱ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ” ማለት ከህወሓት ዘረኛና ፋሺስታዊ አገዛዝ ነፃ መውጣት የሚናፍቅ ኢትዮጵያዊ ማለት ነው።
በህወሓት አገዛዝ የተማረርነው ከኢህአዴግ ውጭ ያለነው ኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለንም። ከህወሓት አገዛዝ ነፃ መውጣትን የሚናፍቁ ዜጎች ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድ ውስጥ አሉ። ከህወሓት አገዛዝ ነፃ መውጣትን የሚናፍቁ ዜጎች አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ ውስጥ አሉ። ከህወሓት አገዛዝ ነፃ መውጣትን የሚናፍቁ ዜጎች ህወሓትም ውስጥ አሉ። ይህን ስል እነዚህ ድርጅቶች ህወሓት የፈጠራቸው ባሮች ስብስቦች መሆናቸውን ዘንግቼ አይደለም።

ስለባርነት ጥናት ያደረገ ማንኛውም ሰው እንደሚያውቀው ባሮች ሁለት ዓይነት ትግል ውስጥ ራሳቸውን ያገኛሉ። (1) በባርያዎች መካከል “ምርጥ ባርያ” ለመሆን የሚደረግ ትግል አለ። ይህንን ትግል አሸንፈው “ታማኝ ባርያ” ለመባል የበቁ ባሮች በሌሎች ባሮች ላይ እልቅና ይሰጣቸውና ታማኝነታቸው ለማረጋገጥ ሲሉ ከጌቶቻቸው በላይ ክፉዎች ይሆናሉ፤ (2) ባሮች “ሰው” ለመሆን ይታገላሉ። ባርነት የነፃነት እጦት እንጂ በዘር የሚተላለፍ እዳ አለመሆኑ የተገነዘቡ ባሮች ነፃነት ናፋቂዎች ይሆናሉ። ነፃነት ናፋቂ ባሮች ሁኔታው ሲያመቻቸው ጌታቸው ላይ ያምፃሉ፤ ያሳምፃሉ። የመጀመሪያው ዓይነት ባሮች የፀረ-ባርነት ጦርነት ዒላማዎች ናቸው፤ የባርያ አሳዳሪዎችን በምንወጋበት ምሬትና እልህ ታማኝ ባሮችንም መውጋት ይኖርብናል፤ ታማኝ ባሮች ሳይጠፉ ባርነት አይጠፋም። ሁለተኛው ዓይነት ባሮች ግን የፀረ-ባርነት ትግል አካሎች ናቸው - በአንዳንድ ሁኔታዎች በግንባር ተሰልፈው የሚዋጉ የነፃነት አርበኞች ሊሆኑ ይችላሉ። የፀረ-ባርነት ትግል ድል ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች እነሱ ናቸው።
ከላይ የተገለፁት ሁለቱም ዓይነት ትግሎች በብአዴን፣ ኦህዴግ፣ ደህዴግ አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ ውስጥ አሉ። ለምሳሌ የህወሓት ታማኝ አገልጋይ ለመሆን ሲሉ ከህወሓት የባሰ ዘረኛና ክፉ የሆኑ ሰዎች ብአዴን፣ ኦህዴግና ደህዴግ ውስጥ አሉ፤ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በአጋር ድርጅቶችም ውስጥ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የብአዴን፣ ኦህዴግ ወይም ደህዴግ አባል በመሆን የህወሓት መገልገያ መሆናቸው ጥቅም እንዳስገኘላቸው ቢያውቁም እንኳም ህሊናቸው የሚወቅሳቸው፤ በወገኖቻቸው ላይ የሚያደርሱት በደል እነሱኑ የሚያሳምማቸው እና እራሳቸውን ነፃ ለማውጣት የሚያልሙ ዜጎች አሉ።
የህቡዕ ጦርነት አንዱ ስልት ሁለቱን ዓይነት አገልጋዮች መለየት ነው። “ለምርጥ ባርያነት” የሚተጋው ከባርያ አሳዳሪው በላይ ጠላት መሆኑን ማወጅ ያስፈልጋል። የእነዚህ ምርጥ ባሮች አስተዋጽዖ ባይኖር ኖሮ ህወሓት አቅም ሊኖረው አይችል እንደነበር ማስታወስ ይገባል። ነፃነት ናፋቂ የሥርዓቱ አገልጋዮች ግን ሊደገፉ እና መሸሻ ሊዘጋጅላችው ይገባል። ከህወሓት አገዛዝ በኋላ በምትመጣው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ እነሱም እንደሌላው ኢትዮጵያዊ በነፃነት እንደሚኖሩ ማረጋገጫ መስጠት ያስፈልጋል።
እያንዳንዱ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ በቀላሉ ሊያደርጋቸው ከሚችላቸው ነገሮች አንዱ ሁለቱን ዓይነት አገልጋዮች መለየት ነው። በየሠፈራችን የምናውቃቸውን ለህወሓት ምርጥ ባርያነት የሚተጉ አገልጋዮች ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድ፣ አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊ ወይም ኢሶዴፓ መሆናቸው ልዩነት ሳያመጣ በጠላትነት መፈረጅ እና የህቡዕ ጦርነቱ ዒላማዎች ማድረግ ይገባል። ስለእነዚህ ሰዎች የተሟላ መረጃ መያዝ ያስፈልጋል፤ ፍልሚያችን ከእነዚህ ጋር ነው፤ እነዚህን በአስተሳሰብም በአካልም ማሸነፍ ይገባል። በአንፃሩ ነፃነት ናፋቂ የሥርዓቱ አገልጋዮችን በትጋት መፈለግና ማቅረብ በዘወትር ሥራዎቻችን አንዱ መደረግ አለበት። ሰው የብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድ፣ አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊ ወይም ኢሶዴፓ አባል ስለሆነ ብቻ ጠላት ነው ማለት አይደለም፤ እነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ነፃነት ናፋቂዎች አሉና። ሰዉ የህወሓት አባል ስለሆነ ብቻ ጠላት አይደለም እዚያም ነፃነት ናፋቂዎች አሉና። እነዚህን ነፃነት ናፋቂዎችን ፈልጎ ማግኘት፣ ማበረታታትና ከትግሉ ጎን ማሰለፍ አንዱ የህቡዕ ጦርነት ስልት ነው።
ከላይ በግለሰብ የተነገረውን ከመጠነኛ ማስተካከያ ጋር ወደ ድርጅት ማሳደግ ይኖርብናል። ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴግና ደህዴግ አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ ተመሳሳይ ቢሆኑም አንድ አይደሉም። ግለሰቦች ነፃነት እንደሚሹ ሁሉ ድርጅቶችም ነፃነት ይሻሉ። በሁሉም ውስጥ ያለው የነፃነት ፍላጎት እኩል አይደለም፤ ይህንን በጥንቃቄ ማጥናት እና በጥናት ውጤት የተደገፈ የህቡዕ ጦርነት ስልት መንደፍ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ኦህዴድ ከዓመታት በፊት በነበረው ታማኝነቱ መቀጠል አይችልም፤ ብአዴንም ላይ ተመሳሳይ ነገር እየተስተዋለ ነው። ደህዴድ መሀል ላይ የሰፈረ ይመስላል። ብአዴን፣ ኦህዴድና ከፊል ደህዴድ በህወሓት ላይ እንዲያምፁ (ማመፅ ከቸገራቸው አሻጥር እንዲሠሩ) መበረታታት ይኖርባቸዋል። እንዲህ ካደረጉ እንደግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደቡድንም ራሳቸውን ማዳን የሚችሉ መሆኑን ፍንጭ መስጠት ያስፈልጋል።
አንድ ከባድ ችግር ሲገጥመን ከፋፍለን መፍትሄ እየሰጠን ደረጃ በደረጃ ችግሩን እንደምንፈታው ኃይለኛ ጠላት ሲገጥመን ማየት ያለብን እውስጡ ወደአሉ ክፍሎቹ ነው። ኢህአዴግን ቆራርጠን ከፊሉን ወገን አድገን፤ ከፊሉን ደግሞ በጠላትነት ፈርጀን እርስ በርሱ አባልተን ባነሰ መስዋዕትነት ማዳከም አንድ አቢይ የህቡዕ ጦርነት ስልት ነው።
+++

No comments:

Post a Comment