Saturday, March 19, 2016

የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ: በሕመምተኛ ልጁ ሕክምና ስም የሚያካሒደው የገንዘብ ምዝበራ ተጋለጠ፤ ከየአጥቢያው ከብር 3 ሚሊዮን ያላነሰ መሰብሰቡ ተጠቁሟል ሐራ ዘተዋሕዶ



ከእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንዲሰጠው ተወስኗል
ክፍያውን አልፈጽምም ያሉት የገዳሙ ሒሳብ ሹም ከሥራ እና ከደመወዝ ታግደዋል
የሒሳብ ሹሟን ተቃውሞ ተከትሎ የመዘበረውን ክዶ በግለሰቦች ለማላከክ እየሠራ ነው
አማሳኞቹ ኃይሌ፣ ዘካርያስ፣ ነአኵቶና 16 የአጥቢያ ሓላፊዎች በኮሚቴነት ያሰባስባሉ
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፰፻፵፰፤ መጋቢት ፲ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)
entoto-kidanem-and-yemane
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ “ለታማሚ ልጃቸው ማሳከሚያ” በሚል እጅግ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ እንዳሉ የጠቆሙት ምንጮቻችን፤ ከእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ብቻ፣ ግማሽ ሚሊዮን ብር ወጪ ኾኖ እንዲሰጥ በአስተዳደር ኮሚቴው መወሰኑን የተቃወሙት የገዳሙ ሒሳብ ሹም ከሥራ እና ከደመወዝ መታገዳቸውን ገልጸዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ፣ ሕመምተኛ ልጃቸውን በውጭ ሀገር ለማሳከም ይችሉ ዘንድ፣ ከሀገረ ስብከቱ የገዳማትና የአድባራት ሓላፊዎች ተውጣጥተው በየክፍላተ ከተማው በተዋቀሩ ኮሚቴዎች ቢያንስ ከሦስት ሚሊዮን ብር ያላነሰ መሰብሰቡን የጠቀሱት ምንጮች፤ የገንዘብ ርዳታውን አገልጋዮች በየግላቸው በበጎ ፈቃድ እንዲያበረክቱ ከመጠየቅ ይልቅ የአብያተ ክርስቲያናቱ ገንዘብ ለድጋፉ ወጪ መደረጉ አግባብነት እንደሌለውተናግረዋል፡፡
“ድጋፉ በሥራ አስኪያጁ ዕውቅና የሚደረግ ከመኾኑ አንጻር ባለው ተጨባጭ ኹኔታ ከተጽዕኖ የጸዳና በበጎ ፈቃድ ብቻ የሚደረግ ነው ለማለት እንቸገራለን፤” ያሉት ምንጮቹ፣ ተቃውሞን ማሰማት ከሥራ አላግባብ መታገድንና መዛወርን ጨምሮ በተለያዩ ሰበቦች ሽፋን ለጉዳት ሊዳርገን ይችላል ብለው እንደሚሰጉ ያስረዳሉ፡፡
ለዚህም፣ የእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ሒሳብ ሹም፣ የገንዘብ አሰባሰቡን ሕገ ወጥነት በመቃወማቸው ብቻ ባለፈው ሰኞ የተወሰደባቸውን ከሥራ እና ከደመወዝ የማገድ ርምጃ በአስረጂነት የሚጠቅሱ ሲኾን ውሳኔውም በሌላ ሰበብ ሽፋን መተላለፉን ጠቁመዋል፡፡
ሒሳብ ሹሟ እማሆይ ዐጸደ ማርያም ማሞ፣ ቀድሞ ከሚሠሩበት ቤቴል ቅዱስ ሚካኤል ወደ ገዳሙ ተዘዋውረው የመጡት፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ባለፈው ኅዳር ወር ከደርዘን በሚልቁ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሠራተኞች ላይ የሥራ ዝውውር ባደረገበት ወቅት ነው፡፡ በወቅቱ ገዳሙ፣“ሕገ ደንባችን አይፈቅድም” በሚል ምደባቸውን ቢቃወምም ይህንኑ ቅሬታ በውስጡ እንደያዘ ተቀበሏቸው እንደነበር ይገልጻል፡፡ እማሆይ ዐጸደም ላለፉት አራት ወራት የገዳሙ ሒሳብ ሹም ኾነው ሥራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ከመጋቢት 5 ቀን ጀምሮ ግን ከሥራና ከደመወዝ መታገዳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ባለፈው ሰኞ ከገዳሙ ጽ/ቤት ደርሷቸዋል፡፡
ገዳሙ የሒሳብ ሹሟን ምደባ የተቀበለው፣ “ከበላይ መሥሪያ ቤት ላለመጋጨትና ትእዛዝ ለማክበር ሲባል” እንደነበር በደብዳቤው አስታውሶ፣ ይህም የገዳሙን ማኅበር ዕረፍትና ሰላም ነስቶ ቁጣን እንደቀሰቀሰ የገለጸ ሲኾን፤ እገዳው፥ “የገዳሙን ሕገ ደንብና ሥርዓት ለመጠበቅና ለማስከበር ሲባል” የተላለፈ መኾኑን ከመግለጽ በቀር ጽ/ቤቱ የጠቀሰው አዲስ ምክንያት የለም፡፡ የምደባው ጉዳይ ጽ/ቤቱ በሽፋንነት የተጠቀመበት መኾኑን የሚናገሩት ምንጮቹ፤ ለወራት ሥራቸውን ሲያከናወኑ በቆዩት ሒሳብ ሹሟ ላይ የተላለፈው እገዳ ተገቢነት የሌለውና፣ የገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ የካቲት 25 ቀን ባካሔደው ስብሰባ ካሳለፈው ውሳኔ ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደኾነ ያረጋግጣሉ፡፡
በተጠቀሰው ቀን የገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ በዋና አስተዳዳሪው ሰብሳቢነት ባካሔደው ስብሰባ፤ ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ለልጃቸው ማሳከሚያ ገንዘብ ለማሳባሰብ በተዋቀሩ ኮሚቴዎች የቀረበው የድጋፍ ጥያቄ፣ ተገቢነት ያለውና ገዳሙ “የተቻላቸውን ከሰጡት” ሌሎች ገዳማትና አድባራት ሳይለይና ብዙ ሳይዘገይ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ኮሚቴው በውይይቱም፣ “ጥያቄው ሰብአዊ ፍጡርን የማዳን ወሳኝ ጉዳይ መኾኑ ታምኖበት፣ ከገዳሙ ገቢ ላይ ብር 500‚000 ወጪ ኾኖ እንዲመደብ ከዚኽ ውስጥ ብር 300‚000 በገዳሙ ስም፤ ብር 200‚000 በገዳሙ ሠራተኞች ስም ተሠይሞ መጠነ ሒሳቡ በገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ አማካይነት ለክቡር ሥራ አስኪያጁ ስም እንዲደርሳቸው” በሚል ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የገዳሙ ጽ/ቤት፣ ውሳኔ ያሳለፈበትን ቃለ ጉባኤ አባሪ በማድረግ በውሳኔው መሠረት እንዲፈጸምና ሒሳቡ እንዲወራረድ የካቲት 30 ቀን ለሒሳብ ክፍሉ በጻፈው መሸኛ ትእዛዝ ቢሰጥም ሒሳብ ሹሟ ክፍያውን እንደማይፈጽሙ በመግለጽ ውሳኔውን ተቃውመዋል፤ ይህንኑም ተከትሎ አራት ወራት ያስቆጠረው የምደባቸው ጉዳይ በሽፋንነት ተጠቅሶ ባለፈው ሰኞ በዋና አስተዳዳሪው ፊርማ ከጽ/ቤቱ ወጪ በኾነ ደብዳቤ ከሥራ እና ከደመወዝ መታገዳቸው ታውቋል፡፡
ሒሳብ ሹሟ እገዳውን በመቃወም ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አቤቱታ ማቅረባቸው የተጠቆመ ሲኾን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱም ጉዳዩን በመረጃ ደረጃ እንዲያውቀው መደረጉ ተገልጿል፡፡

No comments:

Post a Comment