Wednesday, March 23, 2016

የአባይን ግድብ ሊጎበኙ የሄዱ የመንግስት ጋዜጠኞች ታገዱ


መጋቢት ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአባይን ግድብ 5ኛ የምስረታ አመት ለማክበር ሽር ጉድ እየተባለ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ስለግድቡ ለመዘገብ ወደ ስፍራው የተንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች መንገድ ላይ እገዳ ተጥሎባቸዋል። ከአማራ ክልል ብዙሃን መገናኛ የተውጣጣው የጋዜጠኞች ቡድን፣ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ በሚል ወደ ግድቡ እንዳይገቡ ተደርጓል። የፕሮጀክቱ ስራ መሪ ኢንጂነር ስመኛው ጉብኝቱ ከመካሄዱ በፊት ተጠይቀው፣ ጋዜጠኞች ቢመጡ ችግር እንደሌለና ሙሉ ፕሮጀክቱን መጎብኘት እንደሚችሉ አሳውቀው የነበረ ቢሆንም፣ ጋዜጠኞቹ ወደ አካባቢው ሲደርሱ ግን መጎብኘት አይቻልም በሚል ተከልክለዋል። ጋዜጠኞች የሚሰሩት በማጣታቸው ፕሮጀክቱ በሚሰራበት አካባቢ ያሉ ከተሞችን ፣ ከግድቡ ባገኙት ጥቅም ዙሪያ ህብረተሰቡን በማናገር ፣ ዘገባቸውን በዚሁ ለመሸፈን ጥረት እያደረጉ ነው። የግድቡ 50 በመቶ ተጠናቋል በሚል ለህዝብ የተነገረው መረጃ እንዳይጋለጥ በመፍራት የተደረገ ነው በማለት ጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ተናግረዋል። መንግስት ግድቡ ሲጀመር በ4 አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል መግለጫ መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሰሞኑን ደግሞ 50 በመቶ የሚሆነው የግድቡ ስራ ተጠናቋል በማለት መግለጫ ሰጥቷል።

No comments:

Post a Comment