ኢሳት (መጋቢት 1 ፥ 2008) በሱርማ ብሄረሰብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ወንጀል ለአስርተ-አመታት የቆየ፣ መንስዔውም 100 ኪሜ የኢትዮጵያ የነበረ መሬት በደቡብ ሱዳን በመወሰዱ፣ እና አካባቢው የበለጸገና የተፈጥሮ ሃብት በኢንቨስትመንት ስም እየተነጠቀ ያለ በመሆኑ ነው ሲሉ የአካባቢው የፓርላማ አባል ገለጹ። ይህንን የገለጹት የሱርማ ብሄረሰብን በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት ከፓርላማ አባልነታቸው በፊት የቤንች ማንጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ቦዲ ባይከዳ ናቸው። አቶ ቦዲ ባይከዳ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የሱርማ ብሄረሰብ ተወላጆች ይኖሩባቸው የነበሩ አካባቢዎች በደቡብ ሱዳኖች በመወሰዳቸው ምክንያት ወደ ጎረቤት ወረዳዎች መሰደዳቸው አንዱ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል። በተለይም ቀድሞ ይኖሩበት ከነበረው ወደ ቲርማጥድ ተገፍተው ወደ ተልቢትና ቲቢክ አካባቢዎች በየጊዜው በመሄዳቸው የሚፈጠር ግጭት ኣንዳለ አስታውሰዋል። አካባቢውን በመወከል ከምርጫ 97 በኋላ በነበሩ ሁለት አመታት ፓርላማ ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩት አቶ ቦዲ ባይከዳ፣ የአካባቢው መሬት በደቡብ ሱዳን መወሰዱ በህዝብ ውስጥ የፈጠረውን ቅሬታ በፓርላማ በተደጋጋሚ ቢነሳም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም ብለው የፌዴራሉ ባለስልጣን በተለይም የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኩማ ደመቅሳ ማስፈራሪያ ያዘለ ማስጠንቀቂያ እንሰጣቸው አስታውሰዋል። አቶ ቦዲ ባይከዳ የቤንች ማጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የካቢኔ አባል በነበሩ ሰዓት አካባቢው ያለው የተፈጥሮ ሃብት ከፍተኛ በመሆኑ የአገዛዙ ባለስልጣናት አይን እንዳረፈበት አስታውቀዋል። ይህን ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብትና ለም መሬት ለመቀራመት ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግ እንደነበር ወደኋላ ሄደው አስታውሰዋል። ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ-ገጾች የተሰራጩትን ፎቶግራፎች አስመልክቶ ሲናገሩም “እንደዚህ አይነት አረመኔያዊ ተግባሮች በሱርማና በአካባቢው በሚገኘው ህዝብ ላይ ሲፈጸም ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፥ በጥንት ጊዜ ይደረግ እንደነበረው አይነት የጭካኔ እርምጃ በተደጋጋሚ ይወሰዳል” በማለት ገልጸዋል። የቀድሞ የአካባቢ ባለስልጣናትና የፌዴራል ፓርላማ አባል አቶ ቦዲ ባይከዳ በሱርማ ብሄረሰብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ወንጀል የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በአስቸኳይ ማስቆም እንዳለበት ጥሪ አስተላልፈዋል። በኢንቨስትመንት ስም የህወሃት ባለስልጣናት የሚያካሄዱትን የመሬት ነጠቃ እንዲያቆሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅን በአንድነት ማሰማት እንዳለበት አሳስበዋል።
No comments:
Post a Comment