Wednesday, March 16, 2016

“የብሔር ብሔረሰብ ታሪክና አገራዊ ታሪክን ለማጣጣም ችግር እየተፈጠረ ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተናገሩ።


ፕሮፌሰር ባህሩ ይህን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ከምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ይለማርያም ውይይቱን ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር፦"መንግሥት ኅብረተሰቡን ለማንቀሳቀስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን፣ እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶችን አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚያስችል አኳኋን ቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ እየጣረ ቢሆንም፣ ፖለቲከኛው ጥግ ጥጉን ይዞ ከመታኮስ ባለፈ የመቻቻልና የመወያያት ዴሞክራሲያዊ ባህልን ማዳበር አቅቶታል" ብለዋል። አቶ ሀይለማርያም አክለውም፦ ‹‹በአንድ ትውልድ የተጣመመ የፖለቲካ ባህል ተሸክመን ቁርሾን ለዚህ ትውልድ እያስተላለፍን ነው፤›› ሲሉ ይተደመጡ ሲሆን፤ "አመፅ የማይቀሰቀስ የሐሳብ ብዝኃነት እንዴት ነው እዚህ አገር መፍጠር የሚቻለው?" ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ያቶ ሀይለማርያምን ማብራሪያ ተከትሎ ሀሳብ ለመሰንዘር እድል ያገኙት የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ፦‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ ከታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ህዳሴውን ዕውን ለማድረግ የኢትዮጵያን ታሪክ ማወቅ ያስፈልጋል፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ከፍተኛ ብዥታ ይታያል፤›› ብለዋል፡፡ "የብሔር ብሔረሰብን ታሪክና አገራዊ ታሪክን ለማጣጣም ችግር እየተፈጠረ እንደሆነ ያወሱት ፕሮፌሰር ባህሩ፣ ‹‹ብዙ ጊዜ ከሚያቀራርቡን ይልቅ የሚያለያዩንን ማጋነን እየተለመደ መጥቷል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ብሔርን ከብሔር ከማናቆር ያለፈ ፋይዳ የሌለው ሐውልት እስከ መሥራት ተደርሷል፤›› ያሉት ፕሮፌሰር ባህሩ፤‹‹እነዚህን ችግሮች አስወግዶ አገራዊ መግባባት በመፍጠር ረገድ መንግሥት ምን ያህል ተዘጋጅቷል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አንድ ምሁር በበኩላቸው "የኢትዮጵያ ህዳሴ"የተባለበት ምክንያት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለማንቀሳቀስ ታስቦ መሆኑ እንደሚያስደስት በመጠቆም፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ግን ሕዝቡን ለህዳሴ ከማነሳሳት ይልቅ ቀዝቃዛ ውኃ እየቸለሰበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ፖለቲካዊ ሥርዓት የተለየ አመለካከት ማስተናገድ የማይችል፣ ይልቁንም የሚያሸማቅቅ መሆኑንም ምሁሩ ጠቁመዋል። ‹‹አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠቧል ይላሉ፡፡ ነገር ግን የጠበበው ሁሉም ነገር ነው፡፡ የጋዜጠኝት ምኅዳሩ፣ የሲቪል ሶሳይቲ ምኅዳሩ፣ የነጋዴነት ምኅዳሩ፣ ሁሉ ጠቧል››ያሉት ምሁሩ፤ ይኼ የሆነው የወጡትን የፀረ ሽብር፣ የፀረ ሙስና፣ የግብር፣ የበጎ አድራጎት አዋጆች በመቀጠም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ መስከረም ላይ ባካሄደው ጉባዔ በአገሪቱ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ጠቅሶ በዋናነት ከፍተኛውን አመራር ተጠያቂ ማድረጉን እንደገለጸ ያስታወሱት ምሁሩ፤ "እርስዎ በጥቅምት ወር ካቢኔዎን ሲያሾሙ ግን ፓርላማ ይዘዋቸው የመጡት እኒያኑ የድሮ ካቢኔ አባላትን ነው፡፡ በካቢኔው ያላካተቷቸውን ደግሞ አማካሪ ብለው አጠገብዎ አድርገዋቸዋል፤ይኸው በመጋቢት ወርም ምንም ለውጥ የለም" ሲሉ ተችተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክን በተመለከተ ስላለው ብዥታ ፕሮፌሰር ባህሩ ያነሱትን ሀሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም እንደሚጋሩት ገልጸዋል። አቶ ሀይለማርያም አያይዘውም፦‹‹‹‹በመጀመርያዎቹ ምዕተ ዓመታት አካባቢ የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ የእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ታሪክ ነው፣ በዚህ ላይም መግባባት አለብን፤›› ብለዋል፡፡ በተነሱት ሌሎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

No comments:

Post a Comment