Thursday, March 31, 2016

ይድረስ! የጥላሁን ገሠሠን ክብር ታሪክና ዝና ለመሸከም ሁነኛ ትከሻ ላጣሽው ለወ/ሮ ሮማን በዙ!

የራስጌ ማስታወሻ፡
ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ ክብሪት ሆኖ ያነሳሳኝ ለኳሽ ምክንያት መስፍን በዙ የሚባል ሰው በጥላሁን ገሠሠ ስም በተከፈተ ቴሌቪዥን እየሰራ ያለው ነገር ከአርቲስቱ ሙያዊም ሆነ ግለሰባዊ አመለካከት ጋር የማይገናኝ የመሆኑ እንቆቅልሽ ነበር።
በመሆኑንም እንቆቅልሹን ለመፍታት የሚያግዙ መጠይቆችን አወጣጥቼ አንድ ሁለት እያልኩ ስጓዝ ለመጠይቆቼ የማገኛቸው መልሶች ደግሞ እንደ ክር እየተረተሩ ወደ ቱባው ጉዳይ ወሰዱኝ። ወደ ወይዘሮ ሮማን በዙ!።
እናም ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝን መስፍን በዙን ተውኩና በወይዘሮ ሮማን ላይ አነጣጠርኩ። ዋናው ባለጉዳይ እያለ በጉዳይ አስፈጻሚው ላይ ጊዜ ማጥፋት አልፈለኩም። ጥቂት ከማትባል ጥናትና ክትትል በኋላም እንሆ የጥላሁን ገሠሠን ክብር ዝና ለመሸከም ሁነኛ ትከሻ ላጣሺው ለ “ወሮ ሮማን በዙ” በሚል ርዕስ እጽፍ ዘንድ ብዕሬ ፈቀደ፦በግልባጭም የተወዳጁ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ወዳጅና አፍቃሪ ለሆነው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይድረስልኝ ።TG TV, Mesfin Bezu
ወይዘሮ ሮማን ፡ በቅድሚያ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ አንቱታን ከመጠቀም ይልቅ “አንቺ” እያልኩ የምጠራሽ በእድሜ ብዙም እንደማንበላለጥ ካለኝ ግንዛቤ እንጂ ከኢትዮጵያዊነት ባህልና ስነ-ምግባር ውጭ በሆነ የማሳነስ ወይም የንቀት ስሜት አለመሆኑን እንድትረጂልኝ እሻለሁ።

ስቀጠልም፡ ከላይ ለአንባቢያን ባስቀመጥኩት የራስጌ ማስታወሻ እንደገለጽኩት የዚህ ጽሁፍ ጽንስ “ቲጂ ቴሌቪዥን” አፍቃሪ-ወያኔ የመሆኑን እንቆቅልሽ ለመፍታት መነሳቴ ነው። ወንድምሽ በተወዳጁ አርቲስት ስም በተከፈተ ቴሌቪዥን እየሰራ ያለው ከአርቲስቱ ሙያዊም ሆነ ግለሰባዊ አመለካከት ጋር የማይገናኝ መሆኑ በእውነትም ለአብዛኛው ኢትዮጵ ያዊና አርቲስቱን ለሚያከብረው ዜጋ ሁሉ እንቆቅልሽ ነበር።ቢያንስ ቢያንስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ።
ይህ መሆኑ ያሳሰባቸው ጥቂት የማይባሉ ጸሃፊዎች በተለያዩ ግዚያት ለወንድምሽም ሆነ ላንቺ ምክርና ማሳሰቢያቸውን ጽፈው አንብቢያለሁ። (ማሳሰቢያ አንድ)  (ማሳሰቢያ ሁለት)  (ማሳሰቢያ ሶስት)
ይሁንና ወንድምሽ ከአሳፋሪ ድርጊቱ እንዲቆጠብ የተሰጠውን ምክርና ማሳሰቢያ ችላ ብሎ ጭራሽ ሃገርና ህዝብ አጥፊ ስራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፤ ለዚህ ማን አለብኝነቱ ዋና ጉልበቱ ደግሞ አንቺ በመሆንሽ ይህ ጽሁፍ በሳምንት አንዴ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ ከሚቀበጣጥር ተቀጣሪ ሰው ይልቅ “የአርቲስቱ 6ኛ ባለቤት” የሆንሺውን አንቺን በተጠየቅ ይሞግታል።
ታዲያ መልዕክቴ ለአንባቢም ግልጽ እንዲሆን ያንቺንና ይህ መልዕክት በተቀጣሪነቱም ቢሆን የሚመለከተውን የወንድምሽን ማንነት ላስተዋውቅ።
ውድ አንባቢያን ወ/ሮ ሮማን፤ የክቡር አርቲስት ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ 6ኛ ሚስት የነበረች፤ በአሁኑ ሰአት ደግሞ በጥላሁን ገሠሠ ስም ማለትም “ቲጂ” ወይም (TG TV) በሚል መጠሪያ በአሜሪካን … ውስጥ  የሚገኝ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባለንብረት ስትሆን ይህ ቴሌቪዥን በወንድሟ መስፍን በዙ የሚንቀሳቀስና አፍቃሪ-ወያኔ አመለካከት ያለው፤ የወያኔን ብጹኡነት የሚሰብክና የሚያራምድ ነው።
ወደ መልዕክቴ ልግባ፦
/ ሮማን ሆይ! ውዱና አይተኬው ጥላሁን ገሠሠ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ማለት እንደሆነ በስርዓተ ቀብሩ ላይ ተገኝተሽ ያየሺው ይመስለኛል ። አንቺ ልትረጂው ያልቻልሺው ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ለጥላሁን ገሠሠ ምን ማለት እንደሆኑ ነው። ይህን ደግሞ አለመታደል ሆኖ እንጂ ከማንም በበለጠ አብረሺው ጎጆ የቀለሺው (በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ያልገባሽ 6ኛ ሚስቱ ብትሆኚም) ልታውቂው በተገባ ነበር።
አዎ ! ጥላሁን ለሃገሩና ለወገኑ ስላለው ፍቅር ጥቂት እንኳ ግንዛቤ ቢኖርሽ ኖሮ ፤ ዛሬ በጥላሁን ስም ከወንድምሽ ጋር እየሰራችሁት ያለው ነገር ሁሉ! እሱ ከ14 ዓመት እድሜው ጀምሮ የደከመለትን፤ የቆመለትን፤ እያለቀሰ ያዜመለትን ኢትዮጵያዊነት የሚያጠለሽ የክህደት ሥራ መሆኑን ከማለዳው መረዳት በቻልሽ ነበር።
የጥላሁን ህዝባዊነትና የቲጂ ቲቪ (TG TV) አቋም ምንና ምን ናቸው?
ወ/ሮ ሮማን ለመሆኑ (TG TV) ብላችሁ በንጉሱ ስም በከፈታችሁት ቴሌቪዥን የሚተላለፈው “አፍቃሪ-ወያኔ” የሆነ ዘገባ ከጥላሁን ገሠሠ ማንነት ጋር ምን ያገናኘዋል ነው?
እንደ ግለሰብ ያሻችሁን መደገፍም ሆነ መንቀፍ መብታችሁ ነው፡፤ የኢትዮጵያዊው ጥያቄ ለምን በጥላሁን ስም በተከፈተ ቴሌቪዥን የወያኔን መንግስት ማገልገል ተፈለገ? የሚል ነው።
በአርቲስቱ ስም እስከተከፈተ ድረስ ፕሮግራሙም በእሱውና ሰፋ ካለም በኢትዮጵያ ሙዚቃና አርቲስቶች ዙሪያ መሆን አይገባውም ነበርን? ቴሌቪዥኑ የተቋቋመበት አላማ ምንድነው ?
በነገራችን ላይ እንዲሁ ሳስበው፤ ትንሽም ቢሆን ፊደል የቆጠርሽ ይመስለኛልና ስለ ጋዜጠኝነት ሙያ ግንዛቤ እንደሚኖርሽ እገምታለሁ። በመሆኑም የወያኔ ባለስልጣኖችን ጭራና ዱካ እየተከተለ ሳይጠሩት አቤት፤ ሳይልኩት ወዴት የሚለው ወንድምሽ በቴሌቭዥን ጣቢያው በሚያቀርበው ፕሮግራም የምትሸማቀቂ እንጂ የምትኮሪ አይመስለኝም። ደግሞስ አሸከርነት ምን ያኮራል ብለሽ ነው?
ታዲያ! ወንድሟ ይህን የሚያሳፍር ስራ ሲሰራ እያየች ዝምታ መምረጧ ለምንድነው? ብዬም መጠይቄ አልቀረም። ባይገርምሽ ይህ ጣጠኛ ጥያቄ ነው ለመስፍን በዙ የታሰበውን ጽሁፍ አቅጣጫ አስለውጦ ላንቺ እንድጽፍ ያደረገኝ።መስፍን በዙ! ብዙነው መዘዙ …ሆነ መሰለኝ። ስለዚህ ጉዳይ ወደ ኋላ እመለስበታለሁ።
ከላይ እንደገለጽኩልሽ ምንም እንኳ የውዱ አርቲስት የአንድ ወቅት ጎጆ ተጋሪ ብትሆኝም እንደ አለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ለጥላሁን ገሠሠ ምን ማለት እንደሆኑ የተረዳሽ አይመስለኝም ። ስለዚህ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ለጥላሁን ምን ማለት እንደሆኑ በመጠኑም ቢሆን ላመላክትሽ።
/ ሮማን አንቺንና የምትደግፊውን የወያኔ መንግስት የሚያመሳስላችሁ አንድ ነጥብ አለ። ወያኔዎች የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው እኛ ስልጣን ከያዝንበት ጊዜ ጀምሮ ነው ሲሉ አንቺም የጥላሁን ታሪክ የሚጀምረው እኔ ካገኘሁት ጊዜ ጀምሮ ነው ማለትሽ ነው።
/ ሮማን ጥላሁን የቀድሞውን ሰራዊት ዩኒፎርም ለብሶ ሰራዊቱን ለመቀስቀስ ሲሄድ መንደፈራ ላይ በፈንጂ ተመቶ መቁሰሉን ታውቂያለሽ ? ዳሩ ከጥላሁን ዝና እንጅ ከታሪኩ ምን አለሽ? ዝና እንጂ ታሪክ አይመነዘር።
ቴሌቪዥናችሁ ስለ ህውሃት 40ኛ ዓመት ተጋድሎና ጀግንነት ሲዘክርልን በአኳያው ደግሞ የቀድሞውን ሰራዊት  ፋሽሽትነት ሲያውጅልን እንደ ባላቤትነትሽ “ እረ ይሄ ነገር ደግ አይደለም! ከጥላሁን ገድልና ታሪክ ጋር ይጣረሳል ” ብለሽ ማሰብ የተሳነሽ ለምን ይሆን? ። (ይቅርታ ለካስ ጥላሁን ለናንተ ስም ነው)
TG TV, Mesfin Bezu
ወሮ ሮማን!  ጥላሁን “አጥንቴም ይከስከስ ደሜም ይፍሰስላት፤
እንጂ ሃገሬን ጭራሽ አይደፍራትም ጠላት”

ያላት ሃገር ኢትዮጵያ ነች! በዜማው ብቻ ሳይሆን በተግባርም ደሙን አፍስሶላታል! አጥንቱን ከስክሶላታል! ።  ዛሬ ወንድምሽ ባስነጠሱ ቁጥር መሀረብ የሚቃጣላቸው ስመ-መንግስት የያዙትን ወንበዴዎች ለመፋለም ከዘመተው ጦር ጋር ዘምቶ መንደፈራ ላይ ነበር የቆሰለው።
አንቺም ራስሽ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ከሚታተመው ቁምነገር ጋዜጣ ጋር ባደረግሺው ቃለ ምልልስ ፦
“ጥላሁን የውልደት ቦታ ወይም የብሔር ነገር የሚያሳስበው ሰው አልነበረም፡ ፡ በተለያዩ ቦታዎች የሆነ ፎርም ሲሞላ እንኳ ብሔር ሲባል ኢትዮጵያዊ ብሎ ነበር የሚሞላው፡፡ ጥላሁን ኢትዮጵያዊ ነው፡፡” (ቃል በቃል የተወሰደ)
ብለሽ እንደነበር አንብቢያለሁ ፡: በስሙ የከፈትሺው ቴሌቪዥን ጣቢያሽ ደግሞ ዘርን እንጂ ኢትዮጵያዊነት መስማት ለማይፈልገው የወያኔ መንግስት አገልጋይ መሆኑን እንዴት ታስታርቂዋለሽ?፡:
ወ/ሮ ሮማን ጥላሁን እንዲህም ሲል ያዜመው ለኢትዮጵያ ነው።
ለሀገሬ ስታገል ለድንበሯ
ወድቂለሁ እኔ አፈሯ
ስለ ድል ታሪኬ ስታነሱ
ቤተሰቦቼን ግን እንዳትረሱ

አየሽ..? ወሮ ሮማን! ጥላሁን ቤተሰቡን እንኳ አደራ ብሎ የተናዘዘው ለኢትዮጵያ ህዝብ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አደራ ጠባቂ ህዝብ ነው። አሁንም ቢሆን የጥላሁንን የአብራክ ክፋዮች አክብሮና አፍቅሮ ይኖራል። የሚገርመው ግን ጥላሁን “ቤተሰቦቼን ግን እንዳትረሱ”  ብሎ ለህዝብ በሰጠው የአደራ ኑዛዜ ውስጥ በህዝባር እንኳ ሊጠቀስ የማይችለው ወንድምሽ ዝክር አውጭ ሆኖ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቱ ነው።
ጥላሁን በዜማዎቹ “ኢትዮጵያ” ን ሲያነሳ እንባ ከጉንጮቹ ይቀዳ እንደነበር ሳስታውስና ዛሬ ደግሞ በስሙ በተከፈተ ቴሌቪዥን ያቺ የሚያነባላት ሃገሩን እያጠፉ ያሉ አረመኔዎች መወደሳቸውን ሳስብ፤ ሃዘኔ ይከብዳል!!!።
ጥልዬ፤ በህይወት ዘመኑ ህዝብን ሲያስደስት ቢኖርም የራሱ ህይወት ግን በብዙ መከራዎች የተሞላች ነበረች።  ሞቶም አትረፍ ቢለው ወራሽ ነኝ ባይዋ ክብሩን ታሪኩንና ዝናውን መሸከም ተሳናት።
/ ሮማን ሆይ እውነት! እውነት! እልሻለሁ የጥላሁን ገሠሰን ክብር ታሪክ ዝና የሚሸከም ትከሻ የለሽም!
ብዙ ጊዜ ሰዎች ዝናን ይወዳሉ፤ ብዙዎች በየሄዱበት መታወቅ፤ እከሌ መባል ያስደስታቸዋል። ፍላጎቱ ተፈጥሯዊ ነው። ዝናና ታዋቂነቱ በስራና ማህበራዊ አግባቡን ጠብቆ የተገኘ ከሆነ ማለቴ ነው። በሌሎች ትከሻ መታወቅን አልሞ መነሳት ግን ጸያፍ ነው.። አንቺም የፈለግሺው የጥላሁን ባለቤት እየተባልሽ በቀይ ምንጣፍ ላይ መራመድና በሁሉም ያገልግሎት መስጫ ቦታዎች ቅድሚያ ማግኘትን ነው። ትንሽ ተሳክቶልሽ ይሆናል፡፡ ጥላሁንን የሚወዱ ሁሉ በዩሉኝታም ይሁን በጥላሁን ፍቅር በመሸነፍ አንድ እርከንም ቢሆን ከፍ ሳያደርጉሽ አልቀሩም። ወሮ ሮማን አንድ ያልተረዳሽው ነገር የታዋቂ ሰው ሚስት መሆን ያውም የጥላሁን! ጓዙ ብዙ…. መሆኑን ነው። ወደ አደባባይ ስትወጭ ከፀጉር አሰራርሽ እስከ እግርሽ ቅርፅ ለእይታና ለትችት ይጋለጣሉ። አንዱ አይኗ ያምራል ሲል፤ ሌላው እግሯ ወፍሯል ይላል። ይሄ እንግዲህ ከዝናና አደባባይ ከመዋል ጋር የሚመጣ ነው።በዚህ ላይ ደግሞ ቴሌቪዥን ከፍታችሁ ሰውን ስታዋርዱ በአፀፋው የሚመልስ ሰው መኖሩን ያስተዋላችሁ አይመስለኝም ።
እንዳሁኑ ከጥላሁን ፍላጎት ጋር የማይዛመድ ነገር የመስራትሽ ዚቅ አደባባይ ሲወጣ ደግሞ በይሉኝታም የተሰጠሽ የክብር እርከን ይገፈፋል፡፤ ቁልቁል ተመዘግዝጎ ይወርዳል።ወ/ሮ ሮማን ያገባቺው ጥላሁንን ሳይሆን ዝናውን መሆኑን ህዝብ እንዳሁን ሲደርስበት ማለቴ ነው።  የጥላሁን ዝና ምንጩ ደግሞ ድንቅ ስብዕናውና የሃገር ፍቅሩ ነው፡፡ አንቺ ደግሞ ድንቅ ስብዕናውንና የሃገር ፍቅሩን አውልቀሽ ጥለሽ ዝናውን ብቻ ለመሸከም ፈለግሽ። ትከሻሽ ሁሉንም መሸከም ስላልቻለ የማይነጣጠሉ ነገሮች ነጣጠልሽ። አዲዎስ!!
ልቀጥል…..ወ/ሮ ሮማን
ጥላሁን ለሰው ህይወት ያለውን ክብርና ሰባዊነት በተለይም በህጻናት ላይ የሚደርስ እንግልት የሚያሰቃየው ሩህሩህና አዛኝ እንደነበር “በወሎ ድርቅ” ዘመን “ዋይ! ዋይ! ሲሉ የርሃብን ጉንፋን ሲስሉ” እያለ በርሃብ ሲሰቃዩ ለነበሩት ሕጻናት በእንባ እየታጠበ ያዜመላቸውን ዜማ ብቻ ማስታወስ በቂ ነው።
ዛሬ ደግሞ በዚህ ሩህሩህና አዛኝ አርቲስት ስም የተከፈተው የወሮ ሮማን ቴሌቪዥን የ14 ዓመት ሕጻን ጭንቅላት በጥይት የበረቃቀሱ አረመኔዎች ይወደሱበታል።ይሞገሱበታል።
TG TV, Mesfin Bezu
ወሮ ሮማን ባንክ ሊዘርፍ ሲል ተገደለ የተባለ ው የ14 ዓመት ህጻን ነብዩ ይህ ነው። ይህ ህጻን ዛሬ ቢኖር የ25 አመት አበባ ሊሆን እንደሚችል የምታስብ እናት ገዳዮቹን መደገፍ ቀርቶ ማየትም የምትፈቅድ አይመስለኝም።
ወሮ ሮማን በጥላሁን ስም የከፈትሺው ቴሌቪዥን ከሱነቱና ከብሄራዊ ስሜቱ ጋር ፍጹም የማይገናኝ ጭራሹኑ የሚቃረን ስለመሆኑ በቂ ማሳያ የጠቃቀስኩ ይመስለኛል። አነሰ ከተባለም መጨመር ይቻላል። እድሜ ተዝቆ ለማያልቀው የጥልዬ ገድልና ዝብርቅርቁ ለወጣበት የወንድምሽ ዘገባ …እያነጻጸሩ መዘርዘር ይቻላል፡፤ለጊዜው ግን የአንባቢን ጊዜ ሳልሻማ ወደ ቀጣዩ ጉዳይ ላምራ፦
በነገራችን ላይ ወንድምሽ መስፍን በዙበቴሌቭዥኑ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ሲያጥላላቸው ከነበሩና እያጥላላቸው ከሚገኙት የወያኔ መንግስት ጠንካራ ተቃዋሚዎች መካከል ዋናውና ግንባር ቀደሙ አርቲስት ታማኝ በየነ ነው።
ወንድምሽ በታማኝ በየነ ላይ የሰራውን ከ8 ሰዓት ያላነሰ ዘገባ ተመልክቻለሁ። ይህን ያህል ሰአታት የፈጀው ዘገባ ጠቅላላ ይዘት በሁለት ክሶች ላይ ያጠነጠነ ይመስለኛል።
1ኛው ታማኝ ጥላሁንን አስቀይሞታል! ጥላሁን በታማኝ ምክኒያት አዝኖ ያለቅስ ነበር
2ኛው ታማኝ በጥላሁን የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ህዝብ እንዳይገባ አሳድሟል! የሚሉ ናቸው።
እነኚህ ክሶች ውስጤን ይከነክኑት ስለነበር ታማኝ በየነን አግኝቼ የምጠይቅበትን አጋጣሚ በጣም እጓጓ ነበር። ጉጉቴ በከንቱ አልቀረም። ከለታት አንድ ቀን ታማኝ በየነ ለኢሳት ዝግጅት እኔ ያለሁበት ሃገር መጣ።  አጋጣሚውን በመጠቀም እኔና እንደኔው ነገሩ የከነከናቸው ሌሎች ሁለት ሰዎችን ጨምሬ 3 ሆነን ታማኝን ለ30 ደቂቃ እንዲያገናኙን የኢሳት ዝግጅት አስተባባሪዎችን  ጠየቅን።  የአዘጋጆቹም የታማኝም ፈቃድ ሆነና ከታማኝ ጋር ተገናኘን። ከሰላምታ ልውውጥ በኋላ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ በመግባት በመስፍን በዙ ስለሚቀርቡበት ክሶች ያለውን አስተያየት ጠየቅነው።
በመጀመሪያ እኛ የፈለግነው ለጋራ የሃገር ጉዳይ መስሎት ስለነበር የግል ጉዳይ ስናነሳበት  “አዬዬ….!’’ ካለ በኋላ ለተሰነዘረበት ነገር ብዙም ቁብ እንደማይሰጠው የሚገልጽ ፈገግታ አሳይቶን፤ ነገር ግን ለኛ ባለው ክብር ብቻ የሚከተለ ውን መልስ ሰጠን።
ሁለት ነገር ብቻ ልንገራችሁ፡
1 እኔ ጥላሁንን የወደድኩት በፈቃዴና በፍላጎቴ ነው። ሰውን ስትወድ ደግሞ ከነ ሁለመናው መሆን አለበት።ሰለዚህ ራሴን ለመከላከል ብዬ በሰላም ያረፈውን ንጉስ ከመቃብር እያወጣሁ በዚህ ምክኒያት …እንዲህ ስለሆነ..እያልኩ የጥላሁንን ክብር የሚነካ ክርክር አልከራከርም። እኔ ስለ ጥላሁን ያለኝን ስሜት ሶስታችን እናውቃለንእግዚአብሄር ጥላሁንና እኔ!  ሌላው ትርፍ ነው።
2 በጥላሁን ጉዳይ የሚጠይቀኝና የሚከሰኝ ከጥላሁን ልጆች አንዳቸው ቢሆኑ ኖሮ መለስ እሰጥ ነበር ለነዚህ ሁለት ሰዎች ግን ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢል አልመልስላቸውም  ማን ናቸው ብዬ??? ይልቅ እናንተ እውነትን የማወቅ ፍላጎት ካላችሁ ለምን ከጥላሁን  ልጆች አንዳቸውን አትጠይቁም??ነበር ያለን።
የታማኝ አጭርና ግልጽ መልስ በተለይ እኔን ለሌላ ነገር አነሳሳኝ። አዎ! እውነቱን ለማወቅ ከጥላሁን 6ኛ ሚስት ወንድም ይልቅ የአብራኩ ክፋዮች ይቀርባሉና ከጥላሁን ልጆች አንዱን ማግኘትና ማናገር ፈለኩ ።
ይህን ያሰብኩት ከታማኝ ከተለየሁ በኋላ ነበርና የጥላሁን ልጆችን የማገኝበትን መንገድ እንዲነግረኝ አለመጠየቄ ሲያስቆጨኝ ያየው አንደኛው ወዳጄ የጥላሁን ገሠሠ ሁለተኛ ልጁ “ንጹህብር ጥላሁን ገሠሠ” ስለታማኝና ጥላሁን አባትና ልጅነት የሰጠቺው ምስክርነት እንዳለ ነግሮኝ ቪዲዮውንም አሳየኝ(ቪዲዮውን ለማየት)። ይህን ካየሁና ካደመጥኩ በኋላ መስፍን በዙ የሚባል ሰው ርካሽነት ገዘፈብኝ!። ጉዳዩ በአንቺም እውቅና የሚካሄድ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያለው “የስም ማጥፋት ዘመቻ” መሆኑ ደግሞ በተከታታይ ባደረኳቸው ጥናቶች ግልጽ ሆነልኝ ።
ወሮ ሮማን በነገራችን ላይ! በታማኝ ላይ የምታነሱትን ክስ አንዱም የጥላሁን ልጅ አብሯችሁ የማያነሳው ለምን ይሆን? ጭራሽ አባታቸውን በድሏል የተባለውን ታማኝን የጣት ቀለበትን ያህል ክቡር ሽልማት እንዴት ሊሸልሙት ይችላሉ ? ለመሆኑ እናንተስ በቴሌቭዥናችሁ የጥላሁንን መታሰቢያ ፕሮግራም ስትሰሩ ከጥላሁን ልጆች አንዱን እንኳ ጋብዛችሁ ታውቃላችሁ? ታማኝ ባዘጋጀው የጥላሁን መታሰቢያ ላይ ደግሞ ካንቺ በስተቀር ሁሉም የጥላሁን ቤተሰቦች መገኘታቸውስ ምን ማለት ይሆን? ታዲያ ለጥላሁን የሚቀርበው ማን ነው?  …..ወደ ሌላው ለልፍ
ወ/ሮ ሮማን እዚህጋም አንድ ግዙፍ ቁምነገር የሳትሽ ይመስለኛል!
“አይተኬው የህዝብ ልጅ” ከዚህ አለም በሞት በተለየበት መጥፎ የታሪክ አጋጣሚ ባለቤቱ ስለነበርሽ የቁሳዊና የሌሎችም ተያያዥ ንብረቶቹ ወራሽ መሆንሽን የሚያረጋግጥ ወረቀት በነጋሪት ጋዜጣ አሳውጀሽ አግኝተሽ ይሆናል። ነገር ግን ትልቁን ሃብትና ንብረቱን “የህዝብ ፍቅር” ልትወርሺ አትችዪም። አልቻልሽምም፡፡
የጥላሁን ገሠሠ ሥራ፤ ታሪክና ማንነት ብቸኛ ወራሽ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ። ይህ የህዝብ መብት ደግሞ በጋዜጣ ታውጆ በዳኛ መዶሻ የሚጸድቅ መብት ሳይሆን አርቲስቱ በህዝብ ልብ ውስጥ በገባበት ቅጽበት የጸናና ይግባኝ የማይባልበት መብት ነው። እናም ኢትዮጵያዊው ሁሉ የጥላሁን …  ወራሽ ባለመብት ነው።
በጥላሁን ጉዳይ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ባለመብት መሆኑን ደግሞ ብዕሩ የተባረከ ይሁንና ‹‹ጥላሁን ገሠሠ የሕይወት ታሪክና ምስጢር›› በሚል የውዱን አርቲስት ታሪክ ግሩም አድርጎ ጽፎ ለንባብ ያበቃው ጋዜጠኛ ዘከርያ መሐመድ በማያዳግም መልክ ያስገነዘበሽ ይመስለኛል።
ወሮ ሮማን! ጋዜጠኛ ዘከርያ መሐመድ የጥላሁንን ታሪክ ለመጻፍ ሲነሳ አርቲስቱን ከህጻንነት እስኪ እልፈቱ ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች በቅርብ የሚያውቁትን በርካታ ወዳጆቹንና ቤተሰቦቹን አነጋግሯል። አንቺን ግን አላናገርሽም። ማናገርም አልፈለገም። ለምን ይመስልሻል? የጥላሁን ታሪክ ወራሽ የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ አንቺም ሆንሽ ዘመድ አዝማዶችሽ አለመሆናችሁን ሲነግርሽ ነው።
የመጽሃፉ ደራሲ ዘካሪያ መሃመድ ከቁምነገር ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡
ቁም ነገር፡- የጥላሁን ቤተሰቦች ስለ መፅሐፉ ያውቃሉ?
ዘከሪያ፡- የግል ታሪክ መፅሐፍ እራሱ ነው የሚመራህ፤ የሰውየውን የህይወት ምዕራፍ ነው የምትከተለው፡፡ የአቶ ፈይሳ ሐሰና ሀይሌ የቤተሰብ ማስታወሻ ከተመለከትኩ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ታሪኮችን ለማሰባሰብና ለመተንተን የጥላሁንን ቤተሰቦችና የሱን የቅርብ ወዳጆችን አነጋግሪያለሁ፡፡ ከወዳጆቹና የስራ ባልደረቦቹ መካከል እነ መሐሙድ አህመድ፣ ደበበ እሸቱ፣ አቶ ከበደ ወጋየሁ፣ ወ/ሮ ቆንጅት፣ ወ/ሮ አድባሪቱ የመሳሰሉትን አነጋግሪያለሁ፡

ቁም ነገር፡- ከቤተሰቦቹስ?
ዘከሪያ፡- ወ/ሮ ማርታ፣ ወ/ሮ ሒሩትን እንዲሁም ልጆቹንም አግኝቻቸዋለሁ፤ ይህን ስራ እየሰራሁ እንደሆነ የማያውቁ አሉ ብዬ አላስብም፡፡ ልጆቹንና የትዳር አጋሮቹን አግኝቻቸዋለሁ፡፡

የጥላሁንን የትዳር አጋሮች ሁሉ ሲያነጋግር አንቺን ማናገር አልፈለገም። አንቺን ማማከር ያለመፈለጉ በራሱ የጸሃፊውን በሳልነት ያሳያል። ምክንያቱም አንቺን ካማከረ እያንዳንዷ የጥላሁን ታሪክ ጠብታና እንጥፍጣፊ አንቺና አንቺ ጎጆ ጣሪያ ላይ ብቻ እንድታርፍ ማድረግ እንደምትፈልጊ አውቋል። ይህ መሆኑ ደግሞ የጥላሁንን ታሪክ ያጠለሸዋል። እናም ጸሃፊው አንቺን አለማማከሩ የኢትዮጵያ ህዝብና የጥላሁን ድንቅ ባለውለታ ነው።እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስኩት ደግሞ ይህንኑ ታሪከኛ መጽሃፍ ካነበብኩ በኋላ ነበር። (ስለ መጽሃፉ ከተሰጡ አስተያየቶች አንዱ ይህን ይመስላል)
የሙዚቃውን ንጉስ እንደ ጆንያ ከሰል…
መስፍን በዙ በታማኝ በየነ ላይ ካነሳቸው ክሶች አንዱ፦”ጥላሁን በታማኝ ምክኒያት አዝኖ ያለቅስ ነበር” የሚል ነው። ለመሆኑ ጥላሁንን ያሳዘነው ማን ነው?
‹‹ጥላሁን ገሠሠ የሕይወት ታሪክና ምስጢር›› በሚል በጋዜጠኛ ዘከርያ መሐመድ የተጻፈው የጥላሁን ታሪክ ጥላሁንን ማን እንዳሳዘነው በማያሻማ ምስክርነት አስደግፎ ያስነብበናል።
በመጸሃፉ ላይ ምስክርነታቸው የሚሰጡት ፕ/ር ኃይሌ የጥላሁን የረዥም ጊዜ ወዳጅ ናቸው። ጥላሁንን በተለያዩ ጊዚያት እቤቱ እየሄዱ ይጠይቁታል። አይዞህ! ይሉታል።
ፕ/ር ኃይሌ በአንድ አጋጣሚ ጥላሁን ቤት ሄደው ያስተዋሉትን ለጋዜጠኛ ዘከርያ መሐመድ እንዲህ ብለው ገልጸውለታል። ቀጥሎ ያለውን የመጽሃፉን አንድ ገጽ ቁራጭ ኮፒ ያንብቡ
TG TV, Mesfin Bezu
ወ/ሮ ሮማን፡ ለመሆኑ የፕ/ር ኃይሌን ምስክርነት እንደምን ታይዋለሽ? መቼም ፕ/ሩ ፈጥረው ተናገሩ ብለሽ ለማስተባበል እንደማትሞክሪ እገምታለሁ። ታዲያ የኢትዮጵያ ህዝብ “የሙዚቃው ንጉሥ” እያለ የሚያከብረውን ታላቅ ሰው “እንደ ጆንያ ከሰል” መኪና ውስጥ ክተቱት ብሎ እንግዳ ፊት ማበሻቀጥ በምን …. ሊገለጽ ይችላል? ምን የሚሉት ስነ-ምግባር ነው? … ጥላሁንን ይህ ያላሳዘነው! ይህ ያላስለቀሰው! ምን ሊያሳዝንና ሊያስለቅሰው ይችላል?
በዚህ ምግባርሽ  እንኳን  የጥላሁን  አፍቃሪ  ኢትዮጵያዊ  ይቅርና  ልጆችሽም  ይቅር የሚሉሽ አይመስለኝም!።
ወ/ሮ ሮማን የመጽሃፉ ደራሲ አንቺን ያልጠየቀበት ምክንያት ለማንም ግልጽ ነው። በቁሙ ያላከበርሺውን ሰው ከሞተ በኋላ የታሪኩም የክብሩም ሆነ የዝናው ተጋሪ የመሆን መብትም ሆነ የሞራል ብቃት ሊኖርሽ እንደማይገባ በማመኑ ነው። ትክክልም ነው። አንቺ ግን በሚገርም ይሉኝታ አጥነት የጆንያ ከሰልን ያህል ክብር የነሳሽውን ሰው “ በሱ ጉዳይ የሚያገባኝ እኔና እኔ ብቻ ነኝ!” ብለሽ ትናውዢያለሽ። ካንቺ የተረፈ ውርሰ-ዝና ካለም ወደ ዘር ማንዘርሽ እንዲፈስ ወንድምሽን የፍሳሽ አሸንዳ አርገሽ አሰለፍሽ። አይ የሰው ተፈጥሮ…..!?
ጥላሁን እውነትም ያልታደለ ሰው ነው!
በዚሁ ታሪካዊ መጽሃፍ ውስጥ የጥላሁን አምስተኛ ሚስት ወ/ሮ ማርታ ሲማቶስ ጥልዬን እንዴት ትንከባከበው እንደነበርና ለጤንነቱ ምን ያህል ትጨነቅ እንደ ነበር በስፋት ተገልጿል።
ወ/ሮ ማርታ ሲማቶስ ያገባቺው ጥላሁንን እንጂ ዝናውን እንዳልነበር፤ በተለይ በከፍተኛ ህክምና እግሩ ከመቆረጥ ተርፎ ነገር ግን ሲጋራ ማጨስና ህመሙን የሚያባብሱ ነገሮችን ሁሉ ካላቆመ፤ እግሩ መቆረጡ እንደማይቀር ከሃኪም የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተቀብላ፤ በከፍተኛ ትጋት እየተገበረች፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የጥላሁንን ጤንነት ፍጹም ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር መቻሏ በጥላሁን ልጆችም ሳይቀር ተመስክሮላታል።
እውነተኛ የትዳር ጓደኛ ማለት እንዲህ ነው።እንደ ወ/ሮ ማርታ…!
ወ/ሮ ሮማን ሆይ!  የጥላሁን ልጆች የሚያሳስባቸው የአባታቸው ደህንነትና ጤንነት ብቻ ስለነበር ወ/ሮ ማርታን አመስግነዋል።  አንቺንስ ለምን አላመሰገኑም?…. መልሱን ለአንባቢ ግንዛቤ ልተውና ወደ መጽሃፉ ይዘት ልመለስ፦
ማርታ ለጥላሁን ታደርግለት በነበረው እንክብካቤ ከተደሰቱት የጥላሁን ገሠሠ ልጆች አንዷ ንጹህ ብር ጥላሁን ገሠሠ በዚህ መልክ ነበር ለማርታ ምስጋናና ምስክርነቷን የሰጠቺው፡፤ አሁንም ከመጽሃፉ ኮፒ የተደረገውን ክፍል ያንቡት።
TG TV, Mesfin Bezu
TG TV, Mesfin Bezu
ይህን የንጹህ ብርን የምስጋና መልእክት ሌሎቹም የጥላሁን ልጆች እንደሚጋሩት ደራሲው አነጋግሯቸው እንዳረጋገጠ በዚሁ ምስል ግርጌ መጽሃፉ ላይ አብራርቶ ገልጾታል።
ታዲያ ይሄ አለመታደል አይደለም ትላላችሁ? “አንተ ንጉስ ነህ ከዙፋንህ አትውረድ!” ከምትለው የእናት ምትክ የትዳር አጋር ጉያ ወጥቶ እንደ ጆንያ ጫኑት ወደምትል “ዝና ብቻ” ወራሽ …መግባት። የህይወት መንገድ እንዲህ እንዲህ ነች! … ደልዳላውን መሬት አስትተው መቀመቁን የሚያስመርጡ አስመሳይና አሳሳች መሰናክሎች የበዙባት…
የሚጮህው ቁራ የሚበላው አሞራ!
ሌላው ታማኝ በየነ ላይ ያቀረባችሁት ክስ በጥላሁን ኮንሰርት ላይ ሰው እንዳይገባ አሳደመ የሚል ነው። ለመሆኑ በጥላሁን ገሠሠ ኮንሰርት ላይ ማንስ ቢሆን ማሳደም ይቻለዋልን? ጥላሁን ይዘፍናል ተብሎ አትግባ ቢባል እሺ የሚል ኢትዮጵያዊ አለን? ጥላሁን እኮ የመድረክ ጸሃይ ነው፡፡ ጸሃይ እንዳትወጣ ማሳደም ይቻላል እንዴ? እውነት እውነት እልሻለሁ ይህ ክሳችሁ “የሚጮኽው ቁራ የሚበላው አሞራ” እንዲሉ በሱ ድካም ልታገኙት የነበረው ጥቅም በሆነ ምክንያት ማነሱ ወይም መቅረቱ የፈጠረባችሁን ቁጭት ከመግለጽ ባሻገር ማንንም አያሳምንም።
ወሮ ሮማን ጥላሁን በህይወት እያለ በሰጠው አንድ ቃለ መጠይቅ ላይ “የስኳር ህመምተኞችን የሚረዳ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለማቋቋም እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር ማድመጤን አስታውሳለሁ። አላማውን ከግብ ለማድረስ ሳይችል ማለፉ ያሳዝናል። ይሁንና እሱ ቢያልፍም አላማውን ከግብ በማድረስ የሙት መንፈሱ እንድታርፍ ለማድረግ በአንቺ በኩል እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሰምቼ ደስ ብሎኝ ነበር። አሁንስ ምን ደረሰ ?…
እኛ እያየን ያለነው ግን የስኳር ህመምተኞችን ስትረዱ ሳይሆን  ፤ በስኳር ፋብሪካ ስም ህዝብን ከመሬቱ የሚያፈናቅ ለውን የወያኔ መንግስት አበጀህ! በርታ! እያላችሁ በአሽከርነት ስትባዝኑ ነው።ህዝብ እየታዘበ ያለው በአርቲስቱ ስም በከፈታችሁት ቴሌቭዥን ገዳዩን መንግስት እያገለገላችሁ የአርቲስቱን የሙት መንፈስ እረፍት መነሳታቸሁን ነው ።
ወሮ ሮማንና የወያኔ መንግስትን ምን አፋቀራቸው?
ወ/ሮ ሮማን የጥላሁን የመጨረሻ ሚስትነት በጋብቻ ቅደም ተከተል ብቻ ሳይሆን በህዝብ ዘንድ ባላትም ቅቡልነት ነው፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የግለሰቧ ሁሉን ለኔ ሁሉን በኔ ባይ ባህሪ ነው። በታሪክ አጋጣሚ ጥላሁን ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ የጎጆው ተጋሪ መሆኗ የፈጠረላትን የተጠሪነት መብት ብቻዬን ካልያዝኩ ፤ የጥላሁን ክብርና ዝና እኔው ላይ ብቻ ካልተርከፈከፈ ማለቷ በጥላሁን ቤተሰብና ወዳጆች ብሎም ጥላሁን በሚያፈቅረው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ቅቡልነትን አሳጣት።
ምክንያቱ ደግሞ ጥላሁን የህዝብ መሆኑ ነው።ታሪኩም፤ ሥራውም ብቻ ሁሉም ነገሩ…..የህዝብ ነው፡፤ ከዚያም ቀረብ ሲል የአብራኩ ክፋይ ልጆቹ በሙሉ የሚጋሩት ይሆናል እንጂ የአንድ የመጨረሻ ሚስቱና የሷ ቤተሰቦች ሊሆን አይችልምና ነው፡፡
ወ/ሮ ሮማን በራሷ “ሁሉን በኔ” ባይ ባህሪ ያጣቺውን ህዝባዊ ቅቡልነት የወረቀት ህጉ በሰጣት መብት ለማካካስና የጥላሁን ብቸኛ ወራሽነቷን አድምቃ ለማሳየት ተነሳች ። ይህን እውን ለማድረግ ገባ ወጣ በምትልባቸው ቢሮዎች ፈጣን ግልጋሎት ታገኝ ዘንድ የወያኔ ድጋፍ አስፈለጋት። ወያኔ ደግሞ ሲፈጥረው ከህዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የቆመ መንግስት ነውና ህዝብ  የጠላውን ሰው “በሰጥቶ መቀበል” መርህ እንዴት ማስተናገድ እንዳለበት ስለሚያውቅ በደስታ ተቀበላት። ብቸኛ የጥላሁን ገሠሠ ወራሽ ባለመብትነቷ ደምቆ እንዲታይ መድረኩን ሁሉ አመቻቹላት። በልደቱ … በሃውልቱ… በመጽሃፉ… በፋውንዴሹኑ ምን ቅጡ! ጥላሁን ሲነሳ ሮማንም አብራ እንድትወሳ ሆነ። ወያኔ ይህን ሰጣት!  እሷስ ለወያኔ … ? አዎ እሷም ደግሞ በጥላሁን ስም የተከፈተው ቴሌቪዥን ከኮምኒኬሽን ጽ/ቤት በሚደርሰው መመሪያ መሰረት እንዲያገለግል ፈቀደች፡፡ ወንድሟንም ቀለቡን ችለው እንዲጠቀሙበት መርቃ ሰጠች። ይህው ነው እንቆቅልሹ ሲፈታ።
እስከ ዛሬ መስፍን በዙ ለምን እንዲህ ያደርጋል? እያልን የምንገረመውና የምንጮኽው ሁሉ የባከነ ጩኽት ነበር።መስፍን በሰጥቶ መቀበል መርህ ወያኔና እህቱ ሮማን የተረካከቡት መገልገያ መሆኑን ካለማወቅ የሚነሳ ጩኽት።
መደምደሚያ፦ ወ/ሮ ሮማን ሆይ!  አሁን ምን ሁኔታ ላይ እንዳለሽ ጠንቅቀሽ የምታውቂ ይመስለኛል። አዎ! ጥላሁንን የሚወደው ኢትዮጵያዊ ህዝብ ጀርባውን ሰጥቶሻል። ጥላሁን “ቤተሰቦችን ግን እንዳትረሱ” ሲል ለህዝብ ከሰጠው “የአደራ ኑዛዜ” ላይ ፍቆሻል። ለምን? ብለሽ እንደማትጠይቂም ተስፋ አደርጋለሁ።
አዎ! ለጊዜው የወያኔ መንግስት እስካለ ድረስ የጥላሁን መታሰቢያ ዝግጅት ላይ፤ ልደቱ ሲከበር፤ .. ብቻ የጥላሁን ዝክር ባለበት ቦታ ሁሉ የፊት ወንበር ተይዞልሽ በቴሌቪዥን መስኮት ልናይሽ እንችላለን። ይህም ቢሆን የሚቀጥለው ለጥቂት ጊዚያት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ መንግስት እስክትታደል! ያኔ! ከሃዲና ባንዳው አንድም ሲፈረጥጥ አልያም በተከሳሽ ሳጥን ሲቀመጥ፤  የጥላሁን እውነተኛ ወራሽና ቤተሰቦቹም በሰገነታቸው ላይ ይቀመጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም እንደገና አደራውን አድሶ ይቀበላቸዋል። አንቺና ወንድምሽም በጥፋት ዘመኑ የወያኔ የመንግስትነት ታሪክ ተገቢው ምዕራፍ አይነፈጋችሁም። “ህዝባዊውን አርቲስት የነገዱበት…” በምትል ርዕስ የክህደት -ገድላችሁ ይዘከራል። እስከዛው ግን ከአጥፊዎቹ ትዕዛዝ እየተቀበላችሁ ጥፋታችሁ ቀጥሉ….
ካፈርኩ አይመልሰኝ እንዲሉ፤- ቀጣዩ የመስፍን በዙ ሩጫ የተጋለጠውን የእህቱን ገመና ለመታደግ የጥላሁንና የወ/ሮ ሮማንን ትዳር ከአብርሃምና ሳራ ትዳር ለማመሳሰ መባዘን ነው፡፤ ከቻለ እንደ አለቆቹ የሰው ምስክር አሰልጥኖ በቃለ መጠይቅ መልክ ያቀርብልናል፡፤ ያም ካልሆነ የአፍላ ፍቅራቸውን ጊዜ የቪዲዮና የፎቶ ክምችት አቧራውን እያራገፈ ዘጋቢ ፊልም ያስኮመኩመናል ። እኛም “የዛሬን አያድርገውና ድሮማ …. ነበሩ” እያልን ለማየት ያብቃን። የፕ/ር ኃይሌ ትዝብት ግን ከጭንቅላታችን አይጠፋም፡፤”….ንጉሱን እንደ ከሰል ጆንያ ክተቱት አለች?” …እንቆጫለን እንገበገባለን! ።
ወሮ ሮማን! ለጥሞና ንባብሽ ምስጋናዬን እያቀረብኩ ለዛሬ መልዕክቴን በዚሁ ልቋጭ፤ በቅርቡ ሌሎችንም መረጃዎች አሰባስቤ በተመሳሳይ መልዕክት እንደምንገናኝ ተስፋ አለኝ። በጥላሁን ስም መነገዱ እስካልቆመ እኔም መቃወሜን አላቆምም…… ምኑ ተነካና…
TG TV, Mesfin Bezu
ውድ አንባቢያን ሆይ የሙዚቃውን ንጉስ ታሪክ ካላነበባችሁ ይህን የዘካሪያ መሐመድ መጽሃፍ እንድታነቡ አጥብቄ እመክራለሁ።
አለማየሁ ላቀው መኮንን ! ነኝ
ቸር ይግጠመን !  በመጨረሻም፦

1 comment:

  1. የደርግ ፡ ሠራዊት ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሠራዊት ፡ ሳይሆን ፡ የደርግ ፡ ህይወት ፡ ማራዘሚያ ፡ ኪኒን ፡ ነበር። ኪኒኑ ፡ ኤክሰፓየርድ ፡ ሲደርስ ፡ በሽተኛው ፡ ሞተ። እሄ ፡ ነው ፡ ታሪኩ።

    ReplyDelete