Thursday, March 24, 2016

ወልቃይት: ተስፋዎች እና አደጋዎች Tadsse Biru Karsomo




ወልቃይት፣ የህወሓት የግዛት አልጠግብ ባይነት፤ ተቃውሞን ደፍጥጦ የመግዛት ፍላጎት እና ዘርን ብቻ መሠረት ያደረገ የአስተዳደር ክልል መዘዝ ጎልቶ ከታየባቸው ቦታዎች ግንባር ቀደሟ ሆናለች።
የወልቃቶች “የማንነት ጥያቄዬ አልተመለሰም?” እና የህወሓት “የማንነት ጥያቄ የለህም፤ ድሮ ተመልሷል?” የሚለው ክርክር በውይይት ወይም በድርድር የሚፈታ ነገር አይደለም። ክርክሩ ራሱ ሁለቱን ወገኖች የሚያስማማ መሀል መንገድ የለውም። በሕዝበ-ውሳኔ (referendum) ይፈታ እንዳይባልም (1ኛ) ህወሓት የአካባቢውን የሕዝብ አሰፋፈር ለራሱ በሚያመች መንገድ ቀይሮታልና ተቀባይነት የለውም፤ እና (2ኛ) በሕዝበ-ውሳኔ የሚያስፈጽም፤ ክርክሮች ቢነሱ ላይ ዳኝነት የሚሰጥ ገለልተኛና ተዓማኒን አካል የለም።
የወልቃት ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኘው የህወሓት አገዛዝ ሲወገድ ብቻ ነው። ከዚህ አንፃር ስናየው የወልቃይት ጥያቄ “ህወሓት ኢትዮጵያዊያንን እያስገበረ መግዛቱ ይቀጥል ወይስ አይቀጥል” የሚለው ጥያቄ አካል ነው። የወልቃይቶች ተጋድሎ በመላው ኢትዮጵያው እየተቀጣጠለ ያለው የለውጥ ነበልባል አካል ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የወልቃይት ጥያቄ የአገዛዝ ሥርዓቱ እንዳለ ሆኖ “በአማራ ስር እንካለል” እና “የለም በትግራይ ስር ነው መካለል ያለባችሁ” ወደሚል ደረጃ ከወረደ አደጋ ነው። ትግሉን ኢትዮጵያ ከህወሓት አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ከምታደርገው ትግል አውርዶ በአማራና በትግራይ መካከል ያደርገዋል። እንዲህ ዓይነቱ ግጭት ወደ አስፈሪው የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት እንደማይለወጥ ማስተማመኛ የሚሰጥ የለም። ህወሓት ደግሞ በተለመደው መሠሪነቱ ግጭቱ ወደ ሕዝብ ለሕዝብ እንዲወርድለት መሥራቱ አይቀርም እየሠራም ነው።
ምን ይደረግ?
የህወሓት አገዛዝ ተወግዶ በአገራችን ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የምንመኝ ኢትዮጵያን ዜጎችና ድርጅት በሙሉ የወልቃይቶችን ትግል በሙሉ አቅማችን እንደግፍ። እገረመንገዳችን የወልቃትን ጥያቄ ኢትዮጵያዊ እናድርገው። የወልቃይት ብቻ ሳይሆን በአገራችን በርካታ አካቢዎች ያሉ ተመሳሳይ ጥያቄዎች የሚመለሱት የህወሓት አገዛዝ ተወግዶ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት ሥልጣን ሲይዝ መሆኑ ግልጽ እናድርግ። ጊዜ የለም፤ ሁላችንም አፋጣኝ ምላሽ እንስጥ። የወልቃይቶች ትግል የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ትግል አካል እናርገው !!!

No comments:

Post a Comment