Monday, March 14, 2016

ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ተጠናክሮ ይቀጥል! March 12, 2016


def-thumb
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝባዊ እምቢተኝነት አድማሱን እያሰፋ በመሄድ ላይ ነው። የአዲስ አበባ የታክሲ አሽከርካሪዎች ያደረጉት አድማ፣ ወደ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ጋይንት፣ ደብረታቦር፣ አለምበር፣ ነቀምት፣ ወለጋ፣ ወሊሶና ሌሎችም አካባቢዎች ተዛምቷል። በተለይ በአዲስ አበባ በሙስና የተጨማለቁት የወያኔ ሹማምንት ፣ የሚይዙትና የሚጨብጡት አጥተው ሲባዝኑ ተመልክተናል። ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረው ድንፋታ ሁሉ ተንኖ፣ “ብቻ ስራ ጀምሩልን እንጅ እኛ ጥያቄውን በአፋጣኝ እንመልሳለን” በማለት ሾፈሮችን ሲማጸኑ አይተናል ።አድማው የወያኔን ትእቢት ያስተነፈሰ፣ የውስጡን ቀፎነት ገሃድ ያወጣና፣ እንደ ፊኛ ተነፍቶና ግዙፍ መስሎ የሚታየውን ሃይል በትንሽ ሃይል ማስተንፈስ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ክስተት ነው። የአለም በር አሽከርካሪዎች ደግሞ ” የምታደርጉትን አድርጉ እንጅ፣ በእኛ ላይ ቅጣት ልትጥሉ አትችሉም” በማለት ጠንካራ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ከመገናኛ ብዙሃን ሰምተናል። እንዲህ አይነት ህዝባዊ እምቢተኝነቶች፣ የነጻነት ታጋዮችን የትግል ወኔ የሚያነሳሱ ብቻ ሳይሆን፣ ወያኔ የማይቀረውን ሞት ሲሞት፣ በመቃብሩ ላይ አስተማማኝ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉ ናቸው። ወያኔ ተለጣፊ የሲቪክና የሙያ ማህበራትን በራሱ አምሳል ፈጥሮ፣ በአባሎቻቸው የተመረጡት ማህበራት እንዲኮላሹ በማደረግ ለአመታት የመብት ትግሎች እንዲቀዛቀዙ ቢያደርግም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በእነዚህ ማህበራት ተስፋ የቆረጡ ሰራተኞች ፣ የይስሙላ ማህበራቱን ወደ ጎን በመተውና ራሳቸውን ከወያኔ እይታ ውጭ በማደራጀት ያካሄዱት ትግል፣ በአርያነቱ የሚዘከርና በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ነው። ከሰሞኑ የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል የተገኘው ትልቁ ትምህርትም ይህ ነው፤ ዜጎች ለመብታቸው ለመታገል እስከቆረጡ ድረስ፣ የወያኔን አንድ ለአምስት የጥርነፋ ስልት በዘዴ በማለፍ ራሳቸውን በራሳቸው አደራጅተው መብታቸውን ለማስከበር የሚያግዳቸው ሃይል አይኖርም። በኦሮምያ የሚካሄደው ህዝባዊ እምቢተኝነትም ሆነ የታክሲ አሽከርካሪዎች አመጽ፣ ዜጎች ለመብታቸው ለመታገል ሲቆርጡ የሚፈጥሩት አቅም፣ ከወያኔ የጥርነፋ አቅም በላይ መሆኑን ያሳዬና ሌሎቻችችንም ትልቅ ትምህርት የምንወስደበት ነው።

የአለማችን የነጻነት ትግሎች ታሪክ እንደሚነግረን በጭቆናና አፈና ቀንበር ውስጥ የሚገኙ ህዝቦች ትክክለኛ አላማና ራእይ አንግበው አንድ ጊዜ ቆርጠው ትግል ከጀመሩ፣ ትግላቸው እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ይሄዳል እንጅ፣ በገዢዎች የአፈና መሳሪያዎች አይቆምም። ከአራት አመታት በፊት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የለኮሱት የድምጻችን ይሰማ ትግል፣ ከ 2 ዓመታት በፊት በደቡብ የአገራችን ክፍል ለነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ እርሾ ሆኖ አገልግሏል፤ የደቡቡ ህዝብ ትግል ደግሞ ኦሮምያን ከጫፍ ጫፋ ላዳረሰው ህዝባዊ ትግል መነሻ ሆኖ አግልግሏል፤ በኦሮምያ የቀጠለው ትግልም እንዲሁ በአማራ ክልል ለሚታዩት ተቃውሞች እና በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች ለታዩት የታክሲ ሾፈሮች አድማ መነሻ ሆኗል። እነዚህ ተቃውሞች እስካሁን ተቃውሞውን ባልተቀላቀሉ ሌሎች ማህበረሰቦችም ዘንድ ተመሳሳይ መነቃቃት እንደሚፈጥሩና እኔም ለመብቴ መከበር መነሳት ይኖርብኛል የሚል እልህና ቁጭት እንደሚፈጥር አይጠረጠርም:: በዚህም ምክንያት መምህራን፣ የተለያዩ የፋብሪካ ሰራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ የተለያዩ የሙያ ማህበራት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ጡረተኞች፣ ፖሊሶች፣ የቀድሞ ወታደሮች፣ አርሶ አደሮች ወዘተ መብታቸውን ለማስከበር በአንድነት ወይም በየግላቸው እንደሚነሱ ይጠበቃል:: ህዝባዊ ትግል እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጣይ ነውና። ህዝባዊ አመጽ የሚቆመው ፣ በጥይት ወይም በዱላ ሳይሆን፣ ለአመጽ ምክንያት የሆነውን ጥያቄ በመመለስ ብቻ በመሆኑ፣ በአሁኑ ሰአት በአገራችን ዋነኛው የአመጽ መንስኤ የሆነው የመብት ጥያቄ ፣ ትክክለኛውን ምላሽ እስካላገኘ ድረስ ሊቆም አይችልም።
አርበኞች ግንቦት7 ህዝባዊ እምቢተኝነትን እንደ አንድ የትግል ስልት አድርጎ ሲያውጅ፣ የወያኔን አፋኝ ስርዓት በውጭም በውስጥም ለመከፋፋልና ለማዳከም ይጠቅማል ከሚል ስልት ብቻ ሳይሆን፣ የህዝባዊ እምቢተኝነት መጠናከርና ይህን ትግል የሚያካሂዱት የሲቪክም ሆነ የሙያ ማህበራትን ማጠናከር ፣ ከወያኔ ፍጻሜ በሁዋላ፣ በአገራችን ለሚጀመረው የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ከልብ በማመንም ጭምር ነው። ወያኔ ገና ወደ ስልጣን ሲመጣ፣ የሰራተኛ ፣ የመምህራን ፣ የጋዜጠኞች ወዘተ ማህበራትን ዳግም እንዳያንሰራሩ አድሮጎ የመታቸው፣ የማህበራቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንደልብ የሚዘርፍበትን ስልጣን እንደሚያሳጣው ስለሚያውቅ ነው፣ ለነገሩ ከመጀመሪየውም ለዝርፊያና ለቅሚያ የመጣ ሽፍታ፣ በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፈጠር ፍላጎት ሊኖረው ይችላል ብሎ ማሰብም የዋህነት ነበር። አስገራሚው ነገር ደግሞ ይህ የሽፍታ ስብስብ፣ ከ25 አመታት ዝርፊያ በሁዋላ፣ በቃኝ ብሎ ከዘረፋ ተግባሩ ለመታቀብ አለመቻሉና የዘረፈውን ህብት እንኳን ተመቻቸቶ ለመብላት የሚያስችለውን ስርዓት ለመገንባት አለመቻሉ ነው። ስብስቡ ላለፉት 25 ዓመታት ዘርን ከዘር እያጋጨ፣ እየገደለና እያሰረ፣ ያለከልካይ እንዲዘርፍ በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት የህዝባችን ነጻነትም በዛው ልክ እየተደፈጠጠ መጥቷል፣ ዛሬ እስከናካቴው ሰብሰብ ብሎ የግል ጉዳይን መጫወትም እንደሰላማዊ ሰልፍ እየተቆጠረ፣ የሚያስከስስበትና የሚያስደበድብት ደረጃ ተደርሷል ። የሙያና የሲቪክ ማህበራት እንዲኮላሹ መደረጋቸው፣ ወያኔ እንደልቡ እንዲዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ ለነጻነቱ የሚታገል፣ ወኔና የአገር ፍቅር ስሜት ያለው ትውልድ እንዳይፈጠር አድርጓል። ነገር ብዙ ጥፋቶች ከደረሰም በሁዋላም ቢሆን፣ ህዝባችን ቀስ በቀስ የወያኔን ማንነት ይበልጥ እያወቀ ሲመጣ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምናየው ፣ ህዝባዊ ተቃውሞችና አልገዛም ባይነቱን እያሳደገ መጥቷል። ለዚህ ውጤት መገኘት ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፤ ህዝባችን ለመረጃዎች ቅርብ እየሆነ በሄደ ቁጥር የመብት ትግሎችም በዚያው ልክ እየተጠናከሩ የሚሄዱ በመሆኑ፣ መጪዎች አመታት የኢትዮጵያውያንን የነጻነት ትግል የሚያስተናግዱ ብቻ ሳይሆን የአገራችን መጻኢ እድል የሚወሰንባቸው ወሳኝ አመታት በመሆናቸው ሁላችንም ማንኛውንም እንቅስቃሴ በንቃት እየተከታተልን የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለብን።
አርበኞች ግንቦት7 በሃይል ትግሉም በህዝባዊ እምቢተኝነቱም በኩል ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ሌት ተቀን አቅም የፈቀደለትን ሁሉ እያደረገ ይገኛል። የንቅናቄያችን ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንዳደረጉት ሁለቱም የትግል ስልቶች ተቀናጅተው የወያኔን ግብአተ መሬት እንዲያፋጥኑ ድርጅታችን ሁኔታዎች አመቺ ናቸው ብሎ በሚያምንበት ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኛ ነው። ፍትህ፤ እኩልነትና ነጻነት በአገራችን እንዲሰፍን የሚሻ ማንኛውም ዜጋ በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ንቅናቄያችን የቆመለትን አላማ ለማሳካት በያለበት ሆኖ ትግሉን እንዲቀላቀል ወገናዊ ጥሪያችንን መላልሰን እናቀርባለን:: በሥራ ዋስትና ሰበብ ከወያኔ አለቆቻቸው የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው በገዛ ወገኖቻቸው ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ በማካሄድ ላይ የሚገኙ የመከላከያ ፤ የፖሊስና የደህንነት ሃይሎችም ቆም ብለው በማሰብ ከህዝባቸው ጋር እንዲወግኑ አርበኞች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪውን ያስተላልፋል::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
አርበኞች ግንቦት7

No comments:

Post a Comment