በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ የሃገሪቱ ባለስልጣናት የአለም አቀፍ ማህበረሰብ አፋጣኝ ድጋፍን እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረባቸውን አሶሼየትድ ፕሬስ ሃሙስ ዘገበ። በድርቁ አደጋ ዙሪያ ከዜና አውታሩ ጋር ቃለ-ምልልስን ያደረጉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በአለም ዙሪያ ሌሎች ቀውሶች ቢኖሩም ሃገራቸው በምንም መልኩ ችላ መባል እንደሌለበት ገልጸዋል። በሃገሪቱ ያሉ ከ10 ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች በቂ እርዳታን እያገኙ እንዳልሆነ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። የህጻናት መርጃ ድርጅቱና ሌሎች አለም-አቀፍ ተቋማት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት በከፋ የምግብ እጥረት፣ የአካልና የጤና ጉዳት ደርሶባቸው እንደሚገኝ ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል። ህጻናቱን የመታደጉ ሄደት አፋጣኝ ርብርብ ካልተደረገበት በሃገሪቱ አስከፊ አደጋ ሊያደርስ እንደሚችልም እነዚሁ የእርዳታ ተቋማት በማሳሰብ ላይ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የህጻናት መርጃ ድርጅቱ ድጋፉን እንዲያጠናክር መጠየቃቸውን አሶሼይትድ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል። ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡና ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ከሶስት ሳምንት በኋላ የሚቀርብላቸው የምግብ ድጋፍ እንደማይኖም የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች በመግለጽ ላይ ናቸው። ከእነዚሁ ተቋማት ሲሰጥ የቆየውን ማሳሰቢያ ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩም የአለም አቀፍ ማህበረሰብ እጁን እንዲዘረጋ አሳስበዋል። በቅርቡ የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ሃገሪቱ በቂ የምግብ ክምችት አላት በማለት አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ሲሰጡ የነበረን ማሳሰቢያ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል። ረቡዕ ከብሉምበርግ የቴለቪዥን ፕሮግራም ጋር ቃለምልልስን ያደረጉት የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ አቶ አርከበ እቁባይ በበኩላቸው የምግብ ሰብል ምርት ራሷን እንደቻለችና 95 ሚሊዮን የሚሆነው የሃገሪቱ ዜጋ የዚሁ ተጠቃሚ እንደሆነ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ይሁንና፣ በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብ ሊለወጥ ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
No comments:
Post a Comment