ህዝባዊ ወያኔ ሃሪነት ትግራይ የመንግሥት በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት 1983 ጀምሮ ጠባብ አላማውን ለማሳካት ሲል በርካታ ወንጀሎችንና ክህደቶችን በአገርና በወገን ላይ ሲፈጽም የኖረ ድርጅት ነው። ከነዚህ ወንጀሎች አንዱና ምናልባትም ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ያስቻለው እርስ በራሳችን እንዳንተማመን በመካከላችን የዘራው የጥላቻ ፖለቲካ ነው። በህወሃት የጥላቻ ፖለቲካ መሠረት ኢትዮጵያችን አያት ቅድሜ አያቶቻችን በጋራ በከፈሉት መስዋዕትነት የተመሠረተችና ከተከታታይ የባዕድ ወረራ ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች አገር ሳትሆን አንድ ማህበረሰብ ሌለውን ቅኝ በመግዛት የፈጠራት አገር ነች። ይህ ቅኝ ገዥ ሃይል ደግሞ ሥልጣን ላይ የተፈራረቁ መንግሥታት እስከዛሬ አገራችን ውስጥ ላደረሱት የአስተዳደር በደሎች ሁሉ ተጠያቂ ነው። ላለፉት 26 አመታት የመንግሥት ተቋማትና ሚዲያዎች በቅንጅት ሲያስተምሩና ሲቀሰቅሱ የኖሩት እንዲህ አይነት መሠረት የሌለውን መርዘኛና ከፋፋይ ቅስቀሳ ህብረተሰቡ ውስጥ ለማሰረጽ እና በአገራችን ላይ የጋራ ኩራት እንዳይኖረን የማድረግ ደባ ነው። በዚህ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ምክንያት በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲሸማቀቁ ተደርገው ያደጉ ፤ በደረሰባቸው የማንነት ቀውስ አዲስ ማንነት ፍለጋ የህገመንግሥቱን አንቀጽ 39 ተስፋ የሚያደርጉ ዜጎች ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አልሆነም። ሌላው ቀርቶ በጥቁር ህዝቦች ሁሉ ዘንድ እንደ ነጻነት አርማ ተደርጎ የሚታየው አረንጓደ ብጫ ቀይ ባንድራችን የኩራታችን ምልክት ሳይሆን የባርነት ምልክት ተደርጎ እንዲታይ ያልተሠራ ሻጥር የለም። ለአንድነታችንና ለሉአላዊነታችን ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ ጀግኖች አባቶቻችን ታሪክ ተንቋሾ እንዲናፍርባቸው ተደርጎአል። በአመታት ጥረት የተገነቡ ብሄራዊ ተቋሞቻችን እንዲፈርሱና አገራቸውን በቅንነት ሲያገለግሉ የነበሩ ብዙ ሺዎች እንዲባረሩ ተፈርዶባቸዋል። ብሄራዊ መከታችን የነበረው የቀድሞ ጦር በፋሽስትነት ተፈርጆ እንዲፈርስና ከአምስት መቶ ሺ በላይ አባላቱ ለልመናና ለጎዳና ተዳዳሪነት እንዲዳረጉ ተደርገዋል። ኢትዮጵያዊ ሪህራሄና ወገንተኝነት በጎደለው ጭካኔ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ተወልደው ካደጉበት ቄያቸው እንዲፈናቀሉና መሬታቸው ለባዕዳንና ለሥርዓቱ አገልጋዮች እንዲከፋፈል በማድረግ ከፍተኛ ሃብት ተካብቶበታል። ይሉኝታና ሃፍረት በሌለው ጋጥ ወጥነት አብዛኛውን የመንግሥት ሠራተኛና የግል ንግድ ባለቤቶችን ከሥራቸው በማፈናቀል በምትኩ የአንድ ቡድን አባላት በበላይነት የሚቆጣጠሩት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥልጣን ተፈጥሮአል። ይህንን ግፍና ኢፍትሃዊ አሠራር የተቃወሙትን ዜጎች ሁሉ በገቡበት ገብቶ ለማጥፋት በተወሰደው እርምጃ በጠራራ ጸሃይ በርካታ ዜጎች በየአደባባዩ ተገድለዋል ፤ ታስረዋል ፤ ተገርፈዋል ፤ አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ተደርጎዋል። ከግዲያ ተርፈው ዛሬ ድረስ በየ እስር ቤቱ የሚማቅቁና ፤ እዚያ እስር ቤት ውስጥ በተፈጸመባቸው ድብደባ አካል ጉዳተኛ ሆነው የሚሰቃዩ ዜጎች ቁጥር ስፍር የለውም።
ላለፉት ሶስት አመታት አገራችን ውስጥ እየተቀጣጠለ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ዋና አላማ ህወሃት የማእከላዊውን የመንግሥት ሥልጣን በመቆጣጠር ላለፉት 26 አመታት በህዝባችንና በአገራችን ላይ ሲፈጽማቸው የኖሩትን ወንጀሎችና ግፎች ሁሉ በማስቆም ነጻና ገለልተኛ በሆነ የምርጫ ሥርዓት ህግ ህዝብ በሚመርጠው መንግሥት እንዲተዳደር ለማድረግ ነው። እንዲህ አይነት የመንግሥት ሥርዓት አገራችን ውስጥ ከተመሠረተ ሂልውናው እንደሚያከትም የተረዳውና እስከዛሬ ከህዝብና ከአገር ስለዘረፈው ሃብት ብቻ የሚጨነቀው የህወሃት አመራር ይህንን የህዝብ ትግል ከተቻለ ለማስቆም ካልሆነ ደግሞ አቅጣጫ ለማስቀየር ይጠቅመኛል ብሎ ያሰበውን ሁሉ ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው። አዲስ አበባ ላይ በቅርቡ ተካሂዶ ከነበረው የኢህአደግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ቦኋላ “ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታና ለብሄራዊ መግባባት ሲባል የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ፤ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር እነጋገራለሁ” የሚለው ሁሉ ለፈፋ የዚያ ስትራቴጂ አካል ነው።
በአርበኞች ግንቦት 7 እመነት ህወሃት ስለ ፖለቲካ እስረኞች መፈታት ጉዳይ የሚያወራው አገራችንን ከከተታት ቀውስ ለማውጣት ፈቅዶና ተጨንቆ ሳይሆን ከውስጥና ከውጪ የተቀሰቀሰበትን ተቃውሞ ደፍጥጦ በአሸናፊነት ለመውጣት የሚያስፈልገውን ጊዜ ለመግዛት ያስችለኛል ብሎ አስልቶ ነው። ጠባብ አላማውን ለማሳካት ህወሃት እንዲህ አይነት ዜደ ሲጠቀም የመጀመሪያው አይደለም የመጨረሻውም ሊሆን አይችልም። ምርጫ 97 ላይ ደርሶበት ከነበረው ተመሳሳይ ውጥረት በአቸናፊነት ለመውጣት ምዕራባዊያን ወዳጆቹ ፊት ከጸሃይ በታች ከምድር በላይ ባሉ ነገሮች ሁሉ እደራደራለሁ ብሎ ምሎ ተገዝቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ተጠርቶ የነበረውን ተቃውሞ ሰልፍ እንዲሰረዝ ካስደረገ ቦኋላ እንዴት አድርጎ ስጋት የሆኑበትን የቅንጅት መሪዎችና ደጋፊዎች እንዳጠፋ እናውቃለን። ህዝብ ለማዘናጋትና የተቀሰቀሰበትን ተቃውሞ ለማርገብ ሲባል ይፋ በሆነው የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ጉዳይ የአገዛዙ ባለሥልጣናት የሰጡት እርስ በርሱ የሚጣለዝ መግለጫ በጉዳዩ ላይ በመካከላቸው ምንም መግባባት እንደሌለ አሳብቆባቸዋል።
በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ማንኛውም ሰው በፖለቲካ እምነቱና አመለካከቱ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ መታሰሩ ህገወጥ እርምጃ እንደሆነ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። በዚህም ምክንያት ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱና ዜጎችን ያለጥፋታቸው በማሰር የሚያሰቃዩ ወንጀለኞች ሁሉ ለህግ እንዲቀርቡ ሲጠይቅና ሲታገል ቆይቶአል። አሁንም ይታገላል። አርበኞች ግንቦት 7 የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ የሚጠይቀው የነርሱ መፈታትና አላማቸውን በነጻነት ማራመድ መቻል ለሚታገልለት የዲሞክራሲ ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋጾ ስላለው እንጂ ግቡ ስለሆነ አይደለም። ህወሃት በዚህ ጉዳይ እንደማይስማማ ግልጽ ነው። ስለዚህ በአንድ በኩል እስረኞችን ነጣጥሎ በመፍታት የተነሳበትን ህዝባዊ ተቃውሞ አከሽፋለሁ ብሎ ያስባል በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ጸጥታ ሃይሎችን በሙሉ በአንድ ኮማንድ ሥር በማስገባት የተነሳበትን ህዝባዊ ተቃውሞ እጨፈልቃለሁ ብሎ እንቅስቃሴ ጀምሮአል። ሁለቱም ስልቶች ካልተሳኩ ደግሞ ያለ የሌለ ሃይሉን ይዞ ትግራይ ውስጥ በመመሸግ የተቀረውን ህዝብ እርስ በርሱ አባላለሁ ብሎ ያስባል።
አርበኞች ግንቦት 7 ከአሁን ቦኋላ የትግራይ ምድርም ሆነ የአዲስ አበባው ሚኒልክ ቤተመንግሥት የህወሃት ዋሻ ሆኖ የህዝባችን መከራና ስቃይ የሚቀጥልበት ሁኔታ እንዳይኖር አቅም በፈቀደለት ሁሉ አጥብቆ ይታገላል። ያታግላል። አማራና ኦሮሞን እሳትና ጭድ በማድረግ ኢትዮጵያን እስከወዲያኛው ለመግዛት የነበረው የአመታት ምኞት ዳግም ላያንሰራራ ተንኮታኩቶ ወድቆአል። የእስረኞቻችን በከፊልም ሆነ በሙሉ መለቀቅ ህዝባችን ለሥር ዓት ለውጥ የጀመረውን ሁለገብ ትግል ለአፍትም ቢሆን አያስቆምም።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በኢህአደግ ስብሰብ ውስጥ ሆናችሁ የወያኔን ጠባብ አጀንዳ ስታስፈጽሙ የኖራችሁ የህዝብ ወገኖች ሁሉ! እየታሰርን ፤ እየተገረፍንና ፤ እየተገደልን ለዚህ ያደረስነውን የህዝብ ትግል በመቀላቀል ፍትህ እኩልነትና ነጻነት የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ኢገር በጋራ እንድንመሠርት ወገናዊ ጥሪ ቀርቦላችኋል ። ከህዝብ አብራክ የወጣህ የአገሪቱ መከላኪያ ሠራዊት ፤ የፖሊስና ደህንነት አባላት ሆይ! ለሥርዓት ለውጥ እየተካሄደ ያለው ትግል አንተን ከአንድ አናሳ ቡድን መጠቀሚያነት አውጥቶ በህገመንግሥቱ የተሰጠህን አገራዊ አንድነት የማስጠበቅ ሃላፊነትህን በነጻነት እንድትወጣ እንጂ አንተን በበቀልና በጥላቻ የመበተን አይደለም። ስለዚህ ወያኔ እኔ ከሌለሁ የሚመጣው መንግሥት ይበትነሃል ፤ እንደ ቀድሞ ጦር ልብስህን አንጥፈህ ለልመና ትዳረጋለህ የሚለውን መሰሪ ቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ ሰምተህ በገዛ ወገንህ ላይ አትተኩስ፤ አትግደል ፤ አትሰር። ይልቁንም የያዝከውን መሣሪያ በቡድን ተቧድነው አጥንትህንና ደምህን በመጋጥ በከበሩ የህወሃት አለቆችህ ላይ አዙርና የአገዛዝ ዕድሜውን አሳጥር። ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ምን ጊዜም ከጎንህ ይቆማልና ዛሬውኑ ትግላችንን ተቀላቀል።
ድል ለኢትዮጵይ ህዝብ!
No comments:
Post a Comment