Saturday, February 3, 2018

የአርበኞች ግንቦት 7 ተልዕኮ ራዕይ

የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቱ የተከበረበት፣ የኢኮኖሚ ብልፅግናና ማኅባራዊ ፍትህ የሚያገኙበት፣ የዜጎች ህይወት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበረበት ሃገር እንዲኖረው ማድረግ ነው።
ተልዕኮ
የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ፣ ቀዳሚ ተልዕኮ የመንግስትና የፖለቲካ ስልጣን በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚያዝበትንና የሃገሪቱ ዜጎች ምርጫ በተግባር የሚገለፅበትን ብሄራዊ ሥርአት እንዲገነባ ማገዝ ነው።
መሰረታዊ ዕሴቶችና መርሆዎች
የግለሰቦችና የህዝብ መብቶች መከበር የአዲሱ ፖለቶቲካዊ ሥርአት የሚዕዘን ድንጋይ ነው፣
የአዲሱ ፖለቲካዊ ስርአት የጀርባ አጥንት በመሆን የአምባገነን መንግስታትንም ሆነ ፓርቲዎችን፣ እንዲሁም ፖለቲከኞችን መረን ያጣ ሥልጣን ለመቆጣጠር፣ ነፃ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ተቋማት ምሥረታና መጠናከር አስፈላጊነቱን በማመን፣ ነፃ የፖሊስና የመከላከያ
ሃይል፣ ነፃ የምርጫ ቦርድና ነፃ ፕሬስ እንዲመሰረቱና እንዲጠናከሩ መታገል፣
የሃይማኖት፣ የዘውግ፣ የባህልና የመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ልዩነቶች የሚያደምቁን ውበቶቻችን እንጂ፣ የርስ በርስ መጠቃቂያ መሳሪያዎች አለመሆናቸውን በማመን፣ ይህንን ውበት ያላበሱን ልዩነቶቻችንን የሚያከብር በሃገራዊ አርበኛነት ላይ የቆመ ጠንካራ ህብረተሰብ መገንባት፣
ዜጎች ከሚጋሩት ህይወት፣ ህልምና ተስፋ እንዲሁም በታሪክ ካዳበሩት የጋራ ትስስር ይልቅ፣ የዘውግ፣ የሃይማኖትና ባህላዊ ልዩነቶቻቸውን ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ጥቅም የሚቆምሩ ፖለቲካዊና ተውፊታዊ ጎታች ሃይሎችን መታገል፣
ዜጎች በዘውግ ጀርባቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በቋንቋቸው፣ በባህላቸው፣ በእድሜያቸው፣ በጾታቸው ወይም በመልክአ ምድራዊ ልዩነቶቻቸው ወይም በግላዊ አቅመ-ደካማነታቸው የተነሳ አድልኦ የማይፈጸምባቸውና የዜግነት የእኩልነት መብታቸው የሚከበርበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ማመቻቸት፣
ሃገሪቱን ለማገልገል የቆረጡ፣ ታታሪ፣ ብሩህ፣ አርቆ አሳቢና ሆደ-ሰፊ፣ ለዜጎች አርአያ የሚሆኑ መሪዋች እንዲፈጠሩ ማገዝ፣
የመልካም አስተዳደር፣ የተጠያቂነትና የግልፅነት መርሆዎች፣ ህዝብን ማዕከል ካደረገ የውሳኔ አሰጣጥ ጋር ተሳስረው በተግባር የሚተረጎሙበትን ሥርአት መመሥረት፣
በጥረት የሚገኝ ውጤት የሚከበርበት፣ ሃገርን ማገልገል ድንቅ የሚባልበት፣ ችሎታና ታታሪነት ብቻ የሽልማት መስፈርቶች የሆኑበት፣ ዜጎች በፖለቲካ ትስስራቸውና በዘውግ ማንነታቸው ሳይሆን በአበርክቶአቸው የድካማቸውን ውጤት የሚያገኙበትና የሚወደሱበት ፖለቲካዊ ሥርአት መመሥረት፣
ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና ህዝባዊ ግንባሮች ጋር ቅንብርና ትብብር በመፍጠር፣ በመሃላቸው ያለውን ውጥረት ማርገብ፣ ብሎም፣ ሁሉን በአካተተ፣ ሰፊ የፖለቲካዊ ስርአት አማካይነት ብሄራዊ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር፣
ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የህዝብ ግንባርና እንዲሁም መብትና ጥቅሜ አልተጠበቀም የሚል ቡድን፣ በፖለቲካ ዕምነቱም ሆነ ፕሮግራሙ የተነሳ የማይገለልበትን፣ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሥርአት ማቋቋም ነው።

No comments:

Post a Comment