Sunday, February 11, 2018

በሀሳብ መንገድ ላይ “ድንቁርና ጨካኝ ነው!!” (ተመስገን)


ሶቅራጥስ በመርዝ ተገድሏል፣ ክርስቶስ ተሰቅሏል፣ ብሩኖ ከእነ ህይወቱ በእሳት ጋይቷል፣ ጋንዲ በጥይት ተደብድቧል፣ ኦሾም ተመርዞ ነው የሞተው ይባላል፡፡ … ኧረ ስንቱ!! … ድንቁርና ጨካኝ ነው!! 
ሁሉም ሰላማዊና የፍቅር ሰዎች ነበሩ፡፡ ሁሉም ለሰው ልጆች እኩልነት ቆመዋል፡፡ ሁሉም ዓለማቀፍ ሰብዕና ነበራቸው፡፡ … ለዘር፣ ለቀለም፣ ለሃይማኖት ልዩነት አላጎነበሱም፡፡ … ሁሉም ዕውነትን በማስተማራቸው፣ ዕውነትን በመጋፈጣቸው፣ ጊዜ በሰቀላቸው ጉልበተኞችና ደንቆሮ ወገኖቻቸው መዳፍ ተጨፍልቀዋል፡፡ ደግነቱ እነሱ ቢያልፉም ሃሳቦቻቸውና አስተምህሮቶቻቸው አላለፉም። ሃሳቦቻቸው ምድራችንን የሰው ልጆች ሲዖል ከመሆን ታድገዋታል፡፡ 
ሶቅራጥስ ለመሞት ሲዘጋጅ፣ የጓደኞቹን ሀዘንና ብስጭት ተመልክቶ፡- 
“በድኔ እንጂ ‘ሚቀበረው ሃሳቤ‘ኮ አይደለም … አይዟችሁ!!” … (Be of good cheer, and say that you are burying my body) ነበር ያላቸው። እንዳለውም፤ ድንቁርና ሲሸማቀቅ፣ ጉልበተኛም በጊዜ ሂደት ሲዋረድና ሲንበረከክ እየታየ፣ እዚህ ዘመን ላይ ተደርሷል፡፡ 
ወዳጄ፡- በሃይልና በጦርነት የተያዘ የመንግስት ሥልጣን፤ በአፋጣኝ ወደ ዴሞክራሲያዊነት ካልተቀየረ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ … ሄራክሊተስ እንደፃፈው፤ ጦርነት አንዳንዱን አምላክ፣ አንዳንዱን ሰው፣ አንዳንዱን ባርያ፣ አንዳንዱን ደግሞ ነጻ አድርጎ ስለሚያልፍ፣ ብዙኃኑን ለመከራና ስቃይ ይዳርጋል፡፡ 
ጉልበት፤ የደንቆሮዎች መመኪያ ነው ይባላል። ጉልበተኞች፤ ጊዜ እስቲከዳቸውና ጥሏቸው እስኪሸሽ ወይም ታላቁ ቮልቴር፤ “ሚስማር በሚስማር ይነቀላል” እንዳለው፤ ሌላ ሚስማር እስኪመታቸው ድረስ የሚመጣውን ለመቀበልና ተተኪውን ለመጋተር ቢያደፍጡም ዞሮ፣ ዞሮ የሚሆን ከመሆን፣ የተፃፈው ከመነበብ አይቀርም። … ራቀም ቀረበ፣ ተወደደም ተጠላ፣ ተፈራም አልተፈራ፣ … ጊዜ ለባለተራው “ሞገስ” ሊሆን፣ እዛ ጋ ቆሞ ያሽሟጥጣል!!
ወዳጄ፡- ጦርነት፣ ጦርነትን እየወለደ፣ አንዱ ጉልበተኛ ሌላውን እየተካ በሄደ ቁጥር ጦሱ ለብዙኃኑ ነው፡፡ ገልባጭ ተገልባጩን መቆንጠጡ ደግሞ መቼም አይቀሬ ነው፡፡ “በሰላም መለያየት” (Happy divorce) ያለው ሲኒማ ውስጥ ወይም ቼዝ ጨዋታ ላይ ነው፡፡ በሰላም መለያየት የሚፈልግ … ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፋዊ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ የመሰለፍ፣ የመናገርና የመፃፍን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊና ህገ መንግስታዊ መብቶችን አክብሮ፣ የሰለጠነ መንገድን በመከተል፣ ለሰላማዊ ሽግግር (peaceful transition) መሥራትና መታገል ይኖርበታል፡፡ የግልበጣ ነገር ከተነሳ፣ አንድ ወንድሜ በነገረኝ ቀልድ እንዝናና፡-
ሰውየውና ሚስቱ አልፎ፣ አልፎ ይጣላሉ። ይደባደባሉ፡፡ በተጣሉ ቁጥር ሴቲቱ ጉልበት ነበራትና አስተኝታ ትወቅጠዋለች፡፡ አንድ ቀን እንደለመደችው፤ጉብ ብላ ስትጠፈጥፈው፣ አጅሬ እንደ ምንም አቅሙን አሟጦ ገለበጣትና፣ ደህና አድርጎ ያቀምሳት ጀመር፡፡ .. ሴቲቱ ኡኡታዋን አቀለጠችው፡፡ ጎረቤት እየተሯሯጠ መጥቶ ሊገላግል ሲሞክር … ሰውየው፤ “እባካችሁ ተዉኝ! አዲስ ግልብጥ ነኝ፤ ትንሽ ልኮርኩማት” … ሲል ተማጸናቸው፡፡ 
ወዳጄ፡- ጉልበተኛ ለመልካም ሃሳብህ ያንገላታሃል፣ በገዛ ቤትህ ያስርሃል፣ በገዛ ሀገርህ ስደተኛ ያደርግሃል፡፡ ጉልበተኛ ንብረትህን ይዘርፋል፣ ስራህን ይቀማል፣ ቤተሰብህን ያፈርሳል፡፡ … ጉልበተኛ በዝምታህ ይበሳጫል፣ ስምህን ያጠፋል፣ ሳትነካው፣ ሳትደርስበት ይንኳኳል፡፡ ደንገጡሮቹም እንደዛ ናቸው!! … ጥቅምና ጊዜያዊ ደስታ ያሰክራቸዋል፣ አቅላቸውን የሳቱ አውደልዳዮች ያደርጋቸዋል፡፡ ለእውቀትና ምክንያታዊነት ቦታ የላቸውም፡፡ እያዩ አያዩም፣ እየሰሙ አያዳምጡም። ብዙ መስለው ትንሽ፣ የሚስቁና የሚያሽካኩ ሆነው፣ ነፍሳቸው የምታለቅስባቸው፣ የደላቸውንና የተመቻቸው መስለው፣ የመኖር ጣር ያነቃቸው ናቸው፡፡ ደስታ በገንዘብ የሚሸመት ይመስላቸዋል፡፡ 
ሾፐን ሃወር፤ “ደስታ የሚገኘው ከሃሳባችን ውስጥ እንጂ ከኪሳችን በሞላነው ገንዘብ አይደለም። (Our happiness depends on what we have on our heads rather than on what we have in pockets) ማለቱ አውደልዳዮቹ ዘንድ አይሰራም። ድንቁርና ጨካኝ ነው!!
“ማሰብ በሌለበት ሁኔታ የሚነግሰው ሁካታና ግርግር ነው፡፡ ብቸኛም ቢሆኑ ራሳቸውን ሆነው የሚኖሩ ሰዎች ይሻላሉ፡፡ አውደልዳዮች፤ ጨካኝና አመፀኞች ብቻ አይደሉም፡፡ በዕውቀት ሳይሆን በምላስ የሚነዱ፣ በቆንጆ ቃላት የሚታለሉ ጅሎች ናቸው፡፡ በመዳብ እንደተሰራ ባዶ ማሰሮ ትንሽ ሲነኩ ያለ ማቋረጥ ይጮሃሉ” የሚለን ፕሌቶ፤ “ሞት ለሶቅራጥስ!” እያሉ ሲጮሁ የነበሩትን አውደልዳዮች በመታዘብ ነው፤ እየደጋገመ፤ “ድንቁርና ጨካኝ ነው” እያለ የሚያስጠነቅቀንም ለዚህ ነው፡፡ እውነት ነው፡፡ ድንቁርና ጨካኝ ነው!!
ወዳጄ፡- ለዕውቀት፣ ለሰላምና ለነፃነት ዕድል መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አንድነት የሚፀነሰው እዛ ነው፡፡ የእውነተኛ ልማት መሰረትም እነሱ ናቸው። አውሮፓውያን ለዕውቀት ትልቅ ቦታ አላቸው። አንድ ቀን በንግድና ገበያ ልማት ትስሰር ሳቢያ ወደ አንድነት እንደሚመጡ፣ ፍሬድሪክ ኒች፣ ከመቶ ሰላሳና አርባ ዓመታት በፊት ተንብዮ ነበር፡፡ ትንቢቱም ተፈጽሟል፡፡ የአውሮፓውያኑን አንድነት ሳስታውስ፣ የአህጉራችን ነገር ያሳስበኛል። አፍሪካውያን ምሁራንም፤ የአውሮፓውያኑ ዓይነት ህልም ነበራቸው፡፡ ህልማቸው፣ ምናልባት አንድ ቀን ዕውን ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን እንኳን ለአፍሪካዊ አንድነት ልንቆም፣ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ማለት እንኳ የተረሳ ይመስላል፡፡ 
“ህዝቦች የሃገራቸውን ስም ጠርተው እንደዚህ ነኝ ማለት፣ እስከ መከልከል በደረሰበት ዘመን፤ አፍሪካዊነት ምን ይበጃል? ጋናዊ ሆኖ፣ “ጋናዊ ነኝ” ካላለ፣ አፍሪካዊነት ቢቀርበት ምን ይጎዳዋል? “ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” ይባል የለ? … የገዛ ሀገሩ አፈር እየሸተተው፣ በወንዙ እየተለቃለቀ፣ነገር ግን የማንነቱን መታወቂያ በስውር ተነጥቆ፣ የሃገር ውስጥ ስደተኛ ለሆነ ህዝብ፤ “አፍሪካዊ ነኝ” ማለቱ ይጠቅመው ይሆን?” … ፍርዱን ለአንባቢ ትቼዋለሁ። 
* * *
ወዳጄ፡- ለሃሳብም ሆነ ለጉልበት ባርነት ጊዜው አልፏል፡፡ ሀገርም ሀገር፤ ሰውም ሰው የሚሆነው፣ ከሙስና የፀዳ አስተዋይ ህብረተሰብ የሚፈጠረው፣ የሀገር ፍቅርና አንድነት የሚደምቀው፣ ለዕውቀት፣ ለነፃ ሀሳብና ፍልስፍና መስፋፋት ቅድሚያ ሲሰጥ ነው፡፡ በራሱ የሚተማመን ዜጋ የሚበረክተው፣ ችግሮችን በብልሃትና በዘዴ መፍታት የሚቻለው፣ አድልዎ የሌለበት ፍትሃዊ አስተዳደር የሚገነባው፤ በድንቁርና ላይ ሲዘመት ይመስለኛል፡፡ ዕውነት ዕውነት እልሃለሁ፤ ድንቁርና ጨካኝ ነው!!
“ዕውቀት፤ ሙሰኛና ፈሪ ከመሆን ያድናል” (Learning conquers or mitigates the fear of death and adverse fortune) የሚለን ፍራንሲስ ቤከን ነው፡፡ ቤከን፣ ይህንኑ እውነት እንዲያረጋግጥልንም ባለቅኔ ቨርጂልን ምስክርነት አቁሞታል፡፡ ቨርጂልም፡- 
“የነገሮችን ምንነት መርምሮ የሚረዳ ሰው … እሱ ደስተኛ ነው፡፡ ፍርሃት፣ ስግብግብነትና አጉል ምኞት አያንበረክኩትም፡፡” (Happy the man who has learned the causes of things, and has put under his feet all fears and inexorable fate, and the noisy strife of the hell of greed) በማለት ቤከንን አስጨብጭቧል፡፡ 
ወደ መነሻችን ስንመለስ፣ በጉልበትና በተፅዕኖ ሃሳብን ለማፈን መሞከርና አሳቢዎችን ማንገላታት፣ በቆሸሸ መስታወት ውስጥ የራስን ገፅ እንደ መመልከት ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ ወዳጄ፡- ሎዮናርዶ ዳቪንቺ የመጨረሻው እራት “The last supper” የተባለውን ስዕል እንዲሰራ በተጠየቀበት ጊዜ ያለማመንታት ነበር የተቀበለው፡፡ ዳቪንቺ በተወጠረው ሸራ ፊት ለፊት ረዥም ሰዓት ቁጭ ብሎ ያስብ ነበር፡፡ ሚካኤል አንጀሎ፤ “ስዕል በአእምሮ እንጂ በእጅ አይሳልም፡፡” (One paints not with the hands but with the brain) እንዳለው፡፡ … ይሄ ያልገባቸው አለቃ (Abot) በየጊዜው እየመጡ፤ “አሁንም አልጀመርክም?” በማለት ከሃሳቡ እየቀሰቀሱ, ተፅዕኖ ሊያደርጉበት ፈለጉ፡፡ …
ዳቪንቺ ተበሳጨ፡፡ ስራው ተጠናቆ ታላቅ የጥበብ ውጤት መሆኑ በዓለም ጠቢባን ዘንድ ተናኘ፡፡ ቀስ በቀስ ስዕሉ ሲጠና፣ ዳቪንቺ፤ የአስቆሮቱ ይሁዳን የወከለበት ምስል፣ አለቃ (Abot) ራሳቸው ነበሩ፡፡ “Davinch’ used the gentle man as unconsious model for the figure of Judas” … በማለት ቬነዲቶ ክሮቼ ጽፎልናል፡፡ 
ወዳጄ! እውቀት የሚጫኗትን እንኳ በጥበብ መንገድ ነው፣ክፋታቸውን የምታሳየው፡፡ ድንቁርና ግን ጨካኝ ነው!!
ሠላም!!

No comments:

Post a Comment