ከአርበኞች ግንቦት ሰባትና ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የተሰጠ የጋራ መግለጫ ( PDF )
በትግራይ ሥም እየማለና እየተገዘተ ለመንግሥት በትረ ሥልጣን የበቃው ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ላለፉት 26 አመታት በአገራችንና በህዝባችን ላይ ያልፈጸመው በደል የለም። ክፉንና ደጉን በመጋራት ለዘመናት ተቻችሎና ተፋቅሮ የኖረውን ህዝብ በቋንቋና በሃይማኖት በመከፋፈል በመካከላቸው የጠላትነት ግንብ ለመገንባት አቅም የፈቀደለትን ሁሉ አድርጎአል። የአገሪቱን የአንድነት ታሪክ ጥላሸት በመቀባትና ህብረተሰባችንን ድርና ማግ ሆኖው ያስተሳሰሩ የጋራ እሴቶችን በማጣጣል አንዱ የሌላው ጠላት ተደርጎ እርስ በርስ እንዳተያይና እንዳይተማመን በርካታ ተግባራትን አከናውኖአል። እራሱ የሚቆጣጠራቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች በየክልሉ እያቋቋመና በራሳቸው ጸንተው የማይቆሙ ግለሰቦችን በመሪነት እያስቀመጠ በአገሪቱና በህዝቡ ጥቅሞች ላይ ዘላቂ ጉዳት ያላቸው ወንጀሎችን ፈጽሞአል።
እራሱን ብቸኛ የትግራይ ተወካይ በማድረግ “ህወሃትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው” የሚል ስብከት በህበረተሰቡ ውስጥ በማሰራጨት ለሚሰራቸው ወንጀሎች የትግራይን ህዝብ ምሽግ ለማድረግ ብዙ ጥሮአል። ለረጅም ዘመናት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ኑሮውን መስርቶ ከአገሩ ህዝብ ጋር በሠላም ይኖር የነበረውን የትግራይ ተወላጅ በማስገደድና በማባበል አባል ካደረገ ቦኋላ በህዝብ ላይ ለሚፈጽማቸው ጥቃቶች መረጃ አቀባይ፤ ጉዳይ አስፈጻሚና ያካባቢው የሥርዓቱ የድጋፍ ኃይል አድርጎ ተጠቅሞበታል። በዚህም የተነሳ ለአመታት ተፋቅሮና ተከባብሮ ከሚኖረው ህዝብ ጋር እንዲጋጭና በጠላትነት እንዲተያይ አድርጎታል።
ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተነሱ የጸረ ወያኔ እንቅስቃሴዎች የበቀል እርምጃ እየተወሰደባቸው ካሉ የህወሃት ካድሬዎች በተጨማሪ ከህወሃት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ያልነበራቸው ሰዎችም የጥቃቱ ሰልባ እንደሆኑ መስማት እየተለመደ መጥቶአል። የዚህ አይነት ጥቃት እንዳይደርስ መከላከል የሚኖርብን ኢፍትሀዊ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ ሰላማችንና አንድነታችን አደጋ ስላለው ጭምር ነው። ሰዎች ከህወሃት ጋር በመወገን የሠሩት ወንጀል ሳይለይ የሚወሰደ እንዲህ አይነት እርምጃ የሚያመለክተው ህወሃት በሥልጣን ዘመኑ ሁሉ ‘የትግራይ ህዝብና ህወሃት አንድ ነው” ብሎ ያካሄደው ቅስቀሳ ሰለባ መሆናችንን ነው። ይህ እንዲሆን ከተፈቀደ ደግሞ ህወሃት ሥልጣን ከእጁ የሚያመልጥ ከሆነ ህዝባችንን እርስ በርሱ ለማባላት የሚፈጽመውን ጥፋት የሚያሳካበት ዕድል መፍቀድ ስለሚሆን ለአገርና ለወገን የሚቆረቆር ቅን ዜጋ ሁሉ ይህንን አደገኛ ሁኔታ የማስቆም ግዴታ ይኖርበታል።
ህወሃት እኩይ አላማውን ለማሳካት ይረዳው ዘንድ የትግራይን ህዝብ ከሌላው ለመነጠል የሚያስችለውን ከፋፋይ ሴራ ለአመታት ሲያካሂድ በኢትዮጵያዊነቱና በአገሩ አንድነት ጥርጣሬ ከሌለው የትግራይ ህዝብ አብራክ የወጣው የትግራይ ምሁር አደባባይ ወጥቶ ድርጊቱን ማውገዝና መኮነን ሲኖርበት አይቶ እንዳላየ፤ሰምቶ እንዳልሰማ ዝምታን መምረጡ ትልቅ ስህተት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። ይህ ዝምታ የፈጠረው አደጋ ምን እንደሆነ ከሰሞኑ ከወልደያቆቦና መርሳ አካባቢ በተደረገ ህዝብ አመጽ ታይቶአል። እንዲሁም በቅርቡ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ በህወሃት አገዛዝ ዘመን የተወለዱ ለጋ ወጣቶች እርስ በራሳቸው እንዴት አድረገው እንደተጨካከኑ ማስተዋል አገራችንን ምን አይነት ፈተና ተደቅኖባት እንደሚትገኝ የበለጠ ለመረዳት ያስችላል።
ስለዚህ በአገራችንና በህዝባችን ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለመቀልበስ የሚቻለው ህወሃት ላለፉት 27 አመታት በመካከላችን የዘራውን የጥላቻና ያለመተማመን ግድግዳዎችን አፍርሰን ሁላችንም በጋራ ታግለን የህወሃትን ሥራአት ስንጥልና በምትኩ የእያንዳንዳችንን መብትና ጥቅም ማስከበር የሚችል ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገራችን ማስፈን ስንችል ብቻ እንደሆነ አርበኞች ግንቦት 7ና የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ያምናሉ።
ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሰፊው የትግራይ ህዝብ የህወሃት አምባገነን አገዛዝ በህዝባችንና በአገራችን ላይ እየፈጸመው ያለውን ወንጀል ለማስቆም የጀመረውን ህዝባዊ ትግል በማስቀጠልና መድረኩን በሚመጥን መልኩ በማጠናከር በተቀረው የአገራችን ክፍሎች በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ትግል ሲቀላቀለው ነው። የትግራይ ምሁራንም በዚህ ህዝባዊ እንቅስቃሴ በንቃት በመሳተፍ ሃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ትግራይ ውስጥ ህወሃት የሚያደርሰውን በደል በመቃወምና አገራችንን ለመበተን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማስቆም ላለፉት ጥቂት አመታት አገር ውስጥና ከአገር ውጪ ሆነው በመታገል ላይ ያሉት እንደ አሬና ትግራይ ያሉ ድርጅቶች ባስቸጋሪ ሁኔታም ሆነው ቢያንስ ይህንን የወያኔ እኩይ ስራ በማጋለጥ በኩል የሚያደረጉትን እንቅስቃሴ እያደነቅን እነኝህ ድርጅቶች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ በመሆን የወያኔ ስርዓት እስኪወድቅ ድረስ ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እናበረታታቸዋለን። ከዚህም ባሻገር አርበኞች ግንቦት7ና የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ በጋራ እያካሄዱት ያለውን ትግል በመቀላቀል የህወሃትን አገዛዝ ዕድሜ እንዲያሳጥሩ ወገናዊ ጥሪ ስናቀርብላቸው ከሰሞኑ ተጋሩ የውይይት መድረክ በሚል ማዕቀፍ ሥር የተሰባሰቡ የትግራይ ተወላጆች ያወጡት መግለጫ እጅግ ወቅታዊና አገራችን የገባችበትን ችግር ጥልቀት በመገንዘብ የተወሰደ አቋም መሆኑን እውቅና በመስጠት የስብስቡ አባላትም የጋራ ትግላችንን እንዲቀላቀሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ህወህት የትግራይን ህዝብ በማስፈራራትና ከጎኑ ለማሰልፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትግራይ ውስጥ የጀመረውን “እኔ ከሌለሁ የደርግ ርዝራዦች መጥተው ያጠፉዋችኋል” ቅስቀሳ ለትግራይ ህዝብ ክብር የማይመጥንና ህወሃት ጠባብ አላማውን ለማሳካት ለአመታት ሲያካሂደው የነበረው ተንኮል አካል መሆኑን አገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለህዝባቸው በግልጽ መናገር ይኖርባቸዋል።
የህወሃትን እኩይነትና ጸረ ትግራይና ጸረ ኢትዮጵያ አቋም በመረዳት የሥልጣን ዕድሜውን ለማሳጠር ጠምንጃ ያነሱ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ያቀፈው የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ደምህት) ከአርበኞች ግንቦት 7ና ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን የአገራችንን ትንሳኤ ለማምጣት አቅም የፈቀደውን ሁሉ ትግል እያካሂደ መሆኑ ሠፊው የትግራይ ህዝብና ወያኔ አንድ አለመሆናቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ ነው። ስለዚህም በዚህ ትግል ውስጥ በቀጥታ የምትሳተፉ የሀገራችን ወጣቶች የወያኔ ስርዓት በመጥፊያው ጊዜ የትግራይን ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አቆራርጦ ለመሄድ ለሚያደርገው ሴራ መሳሪያ እንዳትሆን የጋራ ጥሪያችንን እናቀርብልሀለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
No comments:
Post a Comment