May 21, 2015
ከአክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ከመቶ ዓመታት በላይ ነው። ይኼ ግንኙነት በሁለቱ ሃገሮች መካከል ሊኖር የሚገባውን የእኩልነትና የጋራ ጥቅም መሰረት ያደረገ እንደ ነበረ ታሪክ ያስታውሳል። መንግሥታት ቢለዋወጡም በሁለቱ ሃገሮች መካከል የተመሰረተው የቆየ ግንኙነት አይፈርስም የሚል እምነት አለኝ። የኢትዮጵያ ስደተኞች አሜሪካን የመጀመሪያ መድረሻ አድርገን አሜሪካዊ የሆንንበትና ወደፊትም የምንሆንበት ዋና ምክንያት የአሜሪካ አስኳል እሴቶች–ነጻነት፤ የግለሰብ ክብር፤ ፍትህ-ርትእ፤ የሰብአዊ መብቶች መከበር፤ በሕግ ፊት ማንኛውም ግለሰብ እኩል መሆን፤ የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሳዊ አገዛዝ ስለሳቡንና የመስራት እድል በጎሳ ሳይሆን በሞያ የሚወሰን መሆኑን ስላወቅን ነው። ዛሬ ብዙ መቶ ሽህ የኢትዮጵያ ትውልድ በአሜሪካ ይኖራል፤ ድምጽና መብት አለው። በኢትዮጵያ የማናገኘውን በተሰደድንበት አሜሪካ እናገኛለን። ይኼን እድል ተጠቅመን ለተወልድንባት ሃገር ጠበቃ እንሁን።
በሁለቱ ሃገሮች የተመሰረተው የቆየ ግንኙነት በወታደራዊው፤ ሶሻሊስት አምባገነን መንግሥት ዘመን ተለውጦ አሜሪካኖች አቋማቸውን ለውጠው ተተኪ መንግሥት ይጠባበቁ እንደ ነበር ብዙ ማስራጃዎች አሉ። ደርግን የተካው የጎሳ ልሂቃን ቅንጅት ህወሓት በበላይነት የሚያሽከረክረው የኢህአዴግ መንግሥት ከምእራብ ሃገሮች፤ በተለይ ከአሜሪካ ጋር ያለው የጥቅም ትሥስር እጅግ በጣም የጠነከረ ነው። የኢትዮጵያ እድገት ፈጣን የሆነው በውጭ እርዳታ፤ ስደተኛው በሚልከው ገንዘብ፤ በሃገር ውስጥ ብድርና በቅርቡ በውጭ ኢንቬስተሮች ድጋፍ ነው። ኢኮኖሚው በራሱ ለመንቀሳቀስ አልቻለም፤ ፍትኅ ከሌለ አይችልም። በአሜሪካኖች ስሌት፤ በፈራረሰው፤ እርጋታና ሰላም በሌለበት የአፍሪካ ቀንድና አካባቢ (በሰሜን ኤርትራ፤ በምስራቅ፤ ሶማሊያ፤ በምእራብ ደቡብና ሰሜን ሱዳን፤ በባህር ማዶ በየመን፤ በሶሪያ፤ በኢራክ፤ በሰሜን አፍሪካ በሊብያና በግብፅ) ያለውን የርስ በርስ ግጭት፤ የሃገሮች መፈራረስና የሃብት ውድመት ሲመለከቱ ኢትዮጵያ “የእርጋታና የልማት” ደሴት ናት ወይንም ትሆናለች ብለው ማመናቸው አያስገርምም። ግዙፉ እርዳታ ከዚህ ስሌት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ጸረ-ሽብርተኛነት ሰብሳቢ መርህ ሁኗል። አሜሪካኖች ያላስተዋሉት፤ ቢያስተውሉትም የሚመጣውን ችግር ከራሳቸው ጊዚያዊ ጥቅም ባሻገር ያልተገነዘቡት፤ አምባገነኖች ፀረ-ሽብርተኛነትን ምክንያት በማድረግ ራሳቸው ሽብር ፈጣሪዎችና ሽብርተኞች መሆናቸውን ነው። የሰብአዊ መብቶችና የነጻነት መገፈፍ ሁለተኛ ወይንም ሶስተኛ ደረጃ የያዘው ለዚህ ነው። የሕዝብ መብቶች በተከታታይ ሲጎዱ አፍራሽ ኃይሎች፤ ሽብርተኞችን ጨምሮ መግቢያ ቀዳዳ ያገኛሉ፤ ስደተኝነት እየከፋ ይሄዳል።
የአሜሪካ መንግሥት መሪ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ልክ የዛሬ ሁለት ዓመት በደቡብ አፍሪካ እንዲህ ብለው ነበር። “በአፍሪካ ሃገሮች በሙሉ የማንኛውም ግለሰብ ክብር ቢከበር አሜሪካኖችም ነጻ ይሆናሉ። እኔ የማምነው እያንዳንዳችን ነጻ ለመሆን ከተፈለገ የሁሉም ሰብአዊ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከድህነት ወይንም ከበሽታ ወይንም ከጭቆና ነጻ መሆን አለባቸው።” ይኼ እሴት የአሜሪካኖች እሴት ነው፤ የመላው በነጻነት ለመኖር የሚፈልግ ሕዝብ እሴትና ተስፋ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለክብሩ፤ ለፍትህ፤ ለነጻነት፤ ለሕግ የበላይነትና ለዲሞክራሲ ሲታገል ከዓመሳ አመታት በላይ ሁኗል። ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአንድ አምባ ገነን ፓርቲ ስትገዛ ቆይታ አሁንም በአራት ቀናት በሚካሄድ “የይስሙላ ምርጫ” የተጠበቀ ውጤት ለሚከተሉት አምስት አመታት ትገዛለች። የኢትዮጵያ የመንግሥት ስርዓት ልክ የፈረሰውን የሶቬት ሕብረት አገዛዝ የሚመስል ጋርዲያን የተባለው ጋዜጣ “ኦርዌሊያን” የሚለው፤ ወይንም በእኔ አመለካከት ፍጹም የሆነ በስለላ መረብ የተቆራኘ፤ በአንድ አናሳ ብሄር የበላይነት የመከላከያ፤ የስለላና የኢኮኖሚ የበላይነት የሚተዳደር አገዛዝ ነው።
ይኼ አገዛዝ ያለ ዓለም ትሥስር የገንዘብ የስለላ፤ የመከላከያ፤ የዲፕሎማሲና ሌላ ድጋፍ ህይወት አይኖረውም። የማይካደው ገዢው ፓርቲ ባለፉት ሃያ አራት አመታት ለልማት ድጎማ ብቻ አርባ ቢሊየን ዶላር ተሰጥቷታል። ኢህአዴግ ከሙስናው፤ ከሃገር በገፍ እየተሰረቀ ከሚሸሽውና ከሌላው ውድመት የተረፈውን ተጠቅሞ መሰረተ ልማት አካሂዷል። ከእድገቱ ባሻገር መታየት ያለበት ሃቅ፤ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ የምግብ እርዳታ ጥገኛ ከሆነችው፤ ወጣቱ ትውልድ በገፍ ከሚሰደድባት ኢትዮጵያ ተሰርቆ የሸሸው ሃብት ግምት አስር ቢሊየን ዶላር ነው። ይኼ ስንት ፋብሪካ ይከፍት ነበር፤ ለስንት ወጣቶች የስራ እድል ያቀርብ ነበር? የተሰረቀው ተሰርቆና ከሃገር ሸሽቶ፤ የተረፈው መንገድ ስርቷል፤ ሃዲድና ግድቦች እየሰራ ነው። ይኼ ግዙፍ እርዳታና መንግሥት ከባንኮች ተበድሮ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፤ ቪላዎች፤ መንገድና ሌላ ቢሰራ ምኑ ያስደንቃል? የማይካደው ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ደረጃ ጥገኛ መሆኗ ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ በያመቱ የአራት ቢሊየን ዶላር እርዳታ ተቀባይ ሁናለች፤ ከአፍሪካ ከፍተኛው ከሆነ ቆይቷል። በመንግሥት ደረጃ ሲታይ ከሁሉም ሃገሮች ከፍተኛውን እርዳታ የምትለግሰው አሜሪካ ናት። ፈጣን እድገት አለ በሚባልባት አዲስ አበባ ከፎቆቹ ባሻገር ለማየት ለፈለገ ታዛቢ ቢያንስ አንድ መቶ ሽህ ህፃናት በመንገድ ያድራሉ፤ ብዙ መቶ ሽህ ነዋሪዎች ምግብ ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ እየለቀሙ ይበላሉ። ከስምንቶ መቶ ሽህ እስከ አንድ ሚሊየን የኢትዮጵያ ስደተኞች በየመን ብቻ ይገኛሉ። በሊቢያ የታጎሩትን ቁጥር አናውቅም። ለጋሶች ይኼን ሁሉ ግፍ አያውቁም ለማለት አልችልም። በተጨማሪ፤ መጭው ምርጫ ለይስሙላ መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት ያውቃል። ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የያዘው ስራ ይረጋገጥለታል፤ አሜሪካኖች ይኼን እንደሚደግፉ አልጠራጠርም። ሕዝብ የፈለገውና እውነተኛ ውድድር ያለበት ምርጫ ቢሆን ኑሮ፤ የአሜሪካ ኢምባሲና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች በምርጫው ቀንና ተከታታይ ቀኖች “ብጥብጥ” ይነሳል በሚል ስሌት የተጠንቀቁ መልእክቶች አያወጡም ነበር።
ከላይ የቀረበውን መሰረት በማድረግ አሜሪካኖችን የጠየቅኋቸውና ያሳስብኳቸው የእርዳታውን ጥቅምና ጉዳት ከራሳቸው መብትና ጥቅም አንፃር እንዲያዩት ነው። “እስኪ አስቡት፤ በአሜሪካ በተከታታይ አንድ ፓርቲ በየ አራት አመቱ በሚደረገው ምርጫ ቢያሸንፍ ምን ትላላችሁ? የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች መብታቸውን ለማስከበር ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ ፖሊስ ቢደበድባቸው፤ ቢያስራቸው፤ ቢያሳድዳቸው ምን ትላላችሁ? ምርጫው ሰፊ ውድድር ተካሂዶ የፖሊሲ አማራጮች ውይይት ባይደረግባቸው ምን ትላላችሁ? አስቡት፤ ኢትዮጵያ ከአርባ ቢሊየን ዶላር እርዳታ በኋላ ከዓለም ሃገሮች መካከል አሁንም ፍፁም ድሃና በዓመት የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ከአፍሪካ ሃገሮች አንድ ሶስተኛ የሆነ፤ ከዓለም ሃገሮች መካከል በሙሰኛነት የተበከለች፤ ከዓለም ሃገሮች መካከል ከፍተኛውን የምግብ ጥገኝነት ቦታ የያዘች፤ በአፍሪካ ጋዤጠኞችን ከሚያስሩ ሃገሮች መካከል ሁለተኛውን ደረጃ የያዘች፤ በዓለም ደረጃ አራተኛውን ደረጃ የያዘች መሆኗን ብታውቁ ምን ትላላችሁ? ይህች የምግብ ጥገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ አብዛኛውን የምግብ እርዳታ የምታገኘው ከአሜሪካ መንግሥት ነው። ከድሃይቱ ኢትዮጵያ በአራት ዓመታት ብቻ አስር ቢሊየን ዶላር ተሰርቆ ሲሸሽ ለሃገር ጥቅም ቢውል ኑሮ ስንት ፋብሪካዎች ለማቋቋም እንደሚያስችልና ለስንት ኢትዮጵያዊያን የስራ እድል እንደሚፈጥር አስቡት?
እኔ ይኼን ሃተታ ለአሜሪካ ሕዝብና መንግሥት በታወቁ ጋዜጦች አማካይነት ለማቅረብ የተገደድኩት በሙስናውና በገንዘቡ መሰረቅ ምክንያት አይደለም። ያሳሰበኝ፤ የኢትዮጵያዊያን ሰብ አዊ መብቶች በተከታታይ መገፈፋቸው፤ የማህበረሰብ ድርጅቶች፤ ነጻ ጋዜጦችና ጋዜጠኞች፤ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉና የተሻለ አማራጭ ለሕዝብና ለሃገር ለማቅረብ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መደምሰሳቸው፤ መናገር፤ መሰብሰብ፤ መንግሥትን መተቸት ወንጀል መሆኑ ነው። እነዚህን እሴቶች እንደምታከብሩና እንደምትታገሉላቸው አምናለሁ። ታዲያ፤ የአሜሪካ መንግሥት የሚሰጠው እርዳታ እነዚህን እሴቶች ካላጠናከረ ዘላቂ ጥቅሙ ምንድን ነው? የመናገር፤ የመሰብሰብ፤ የመከራከር፤ የመተቸት፤ የመወዳደር ወዘተ መብቶች ፍጹምና አደገኛ በሆነ ደረጃ ታፍነዋል። ሂውማን ራይትስ ወች እንዲህ ሲል አስጠንቅቆ ነበር። “የኢትዮጵያ መንግሥት በአሰቃቂ ደረጃ ከመንግሥት ቁጥጥር ነጻ የሆነውን መገናኛ ብዙሃን አውድሞታል፤ ቢያንስ ሃያ ሁለት ጋዜጠኞች፤ አሳታሚዎችና ብሎገሮችን በወንጀለኛነት ከሶ አስሯል፤ ከሰላሳ በላይ ጋዜጠኞች በፍርሃት ከሃገር እንዲሰደዱ አድርጓል።” ገዢው ፓርቲ ይኼን ሲያደርግ የሚጠቀምባቸው በ2009 ያፀደቃቸው የጸረ-ሽብርተኛና የመንግሥት ያልሆኑ የበጎ አድራጎትና የማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚመለከቱ ሕጎችን ነው። ለነጻነት፤ ለፍትህ፤ ለዲሞክራሲና ለሕግ የበላይነት የተሟገተና የቆመ ግለሰብ ሁሉ ሰለባ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። በስራ እድል በኩል ሲታይ፤ ለገዢው ፓርቲ ወይንም ለጎሳ ጥቅም ታማኝነት ያላሳየ ሁሉ እድል አይኖረውም። አስተዳደሩ በባለሞያዎች ሳይሆን በታማኝነት ይመራል። ይኼን ሁኔታ ስታዩ፤ አፈናው፤ አድልወው፤ ጭካኔው፤ መገለሉ ወዘተ ለሰላም፤ አብሮ ለመኖር፤ ለእርጋታ አደገኛ መሆኑን ትገምታላችሁ። የአገዛዙ አፋኝነትና አግላይነት ለሽብርተኛነት አመች ሁኔታ ፈጥሯል። የአሜሪካ መንግሥት እንደዚህ ያለ አፋኝና አግላይ መንግሥት ሲደግፍ የአሜሪካን የረዢም ጊዜ ጥቅም ይጎዳል ወይንስ አይጎዳም? ብላችሁ የመጠየቅ ሃላፊነት አለባችሁ።
ይኼን አደጋ በተደጋጋሚ የምናቀርበው ኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለንም። በዚህ ዓመት ፍሪደም ሃውስ ስለ ዓለም ሃገሮች ነጻ መሆን አለመሆን ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያ ከአርባ ዘጠኝ ነጻ ካልሆኑ የአፍሪካ ሃገሮች መካከል አርባ ሶስተኛውን ደረጃ ይዛለች፤ ከኢትዮጵያ የባሱ ስድስት ሃገሮች ብቻ አሉ ማለት ነው። በተመሳሳይ፤ ዘ ኮሚቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ የተባለው ተቋም “ጋዜጠኞችን በከፍተኛ ደረጃ ከሚያስሩ ሁለት የአፍሪካ ሃገሮች መካከል አንዷ መሆኗን፤ በዓለም ደረጃ ሲታይ አራተኛ መሆኗን አመልክቷል። እንደዚህ ጨለማ በሆነ ሁኔታ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሊካሄድ አይችልም። ምርጫውን በሚመለከት በዚህ ወር ሂውማን ራይትስ ወች “ምርጫ–የኢትዮጵያን ፈለግ የተከተለ” በሚል እንዲህ ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። “ካለፈው ምርጫ ወዲህ፤ ገዢው ፓርቲ በባሰ ደረጃ ቁጥጥሩን አጠናክሯል፤ የመናገር፤ የመሰብሰብ፤ የመደራጀት መብቶችን ከልክሏል… ኢትዮጵያዊያን ወደ ምርጫ ሲሄዱ ተቃዋሚዎች በገጠማቸው አፈና የተነሳ ያላቸው እድል በጣም የጠበበና ጨለማ የሆነ ነው።” የኢትዮጵያን ሕዝብ፤ በተለይ ተቃዋሚውን በንቀት መነፅር ያየችው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል የፖለቲካ ሃላፊ ዌንዲ ሸርማን “ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ናት፤ ምርጫውን በሚመለከት ነጻ፤ ፍትሃዊ፤ ተቀባይነት ያለው፤ ክፍትና ሁሉን አቀፍ የሆነ ምርጫ እንደሚካሄድ እናምናለን” ያለችው ውሸት ብዙ የምእራብ ታዛቢዎችን ቁጣና ትዝብት አምጥቷል። ዋሽንግተን ፖስት የተባለው የታወቀ ጋዜጣ እሷንና የኢትዮጵያን መንግሥት በሚመለከት “የማስመሰል ምርጫ በኢትዮጵያ” በሚል አርእስት እንዲህ ብሏል። “የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥት ማውገዝ እንጅ ማሞገስ የለበትም።” ስለሆነም፤ የአሜሪካን መንግሥትና ሕዝብ አደራ የምለው ሽብርተኛነትን ለመከላከል በሚል ምክንያት ሽብርተኛነትን የሚፈጥርና የሚያጠናክር መንግሥት መደገፉን ያቁም ነው።
ምን አማራጭ አለ?
ጠቃሚውን ተቃውሞ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆነን ግለሰብ ወይንም መንግሥት ለማሳመን አስቸጋሪ ነው። በእኔ ግምት ለኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ ለመላው ሕዝቡ የኑሮ መሻሻል፤ ለአሜሪካ ዘላቂ ጥቅም አጋባብ ያለው አማራጭ ያለምንም ማወላወል ለሰብአዊ መብቶች፤ ለነጻነት፤ ለፍትህና ለሕግ የበላይነት መከበርና ለዲሞክራሲ ግንባታ ያለተቆጠበ ድጋፍ መስጠት ነው። ቢያንስ የአሜርካ መንግሥት ለራሱ ዘላቂ ጥቅም ሲል የሚለግሰውን እርዳታ በሙሉ ከሰብ አዊ መብቶች መከበርና ከዲሞክራሲ ግንባታ ጋር ማጣመር አለበት። ነጻ፤ ፍትሃዊ፤ ተቀባይነት ያለው፤ ክፍትና ውድድር ያለበት ምርጫ ለማካሄድ ቅድመ ሁኔታዎች መከበር ነበረባቸው። አለመከበራቸው ውጤቱን አስቀድሞ ወስኖታል። ገዢው ፓርቲ ያሸንፋል።
የአሜሪካን ሕዝብ፤ የምክር ቤት አባላትንና የመንግሥት ሃላፊዎችን በቀጥታ የምጠይቀው ከሕዝብ ተሰብስቦ ለኢትዮጵያ አምባገነን መንግሥት የሚሰጠው እርዳታ ከዲሞክራዊው አገዛዝ ጋር ምን ግንኙነት አለው፤ ከሌለው ለምን ለሰብአዊ መብቶች፤ ለነጻነት፤ ለፍትህ፤ ለእውነተኛ እኩልነትና ለዲሞክራሲ አትቆሙም? የሚል ነው።”
በእኛ በኩል አብሮና ተባብሮ ከመስራት ሌላ አማራጭ የለንም። የአሜሪካ ዜግነት ያለን ኢትዮጵያዊያን በያለንበት ለአሜሪካ ምክር ቤት ተወካዮች ሳንሰለች ድምፃችን ብናሰማ ከፍተኛ አስተዋፆ እንደምናደርግ አምናለሁ፤ እስቲ ያልሞከርነውን እንሞክር እላለሁ።
No comments:
Post a Comment