Tuesday, October 24, 2017

በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ከፍተኛ የጦር አዛዦ ከሃላፊነታቸው እየተነሱ ነው (የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ)



በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ መከላከያ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ኦሮሞ የሆኑ የጦር አዛዦች ቀጥታ ሰራዊቱን ከሚያዙበት ምድቦች እየተነሱ ምንም ስራ በሌለባቸው ቦታዎች እየተመደቡ እንደሆነ ታውቋል። በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ኦሮሞ የሆኑ የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች ተቃውሞውን ይደግፋሉ የሚል ምልከታ በህወሃት የጦር አዛዦች መያዙን ለመረዳት ተችሏል። ታችኛው ላይ ያለው አብዛኛው ሰራዊት ከሌላ ብሄር የመጡ በመሆናቸው እነዚህ የኦሮሞ ከፍተኛ መኮንንኖች ኦሮሚያ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ምክንያት አድርገው ታች ላይ ያለውን ሰራዊት በማንቀሳቀስ ህወሃት ላይ አደጋ እንዳያመጡና የተቃውሞው አካል እንዳይሆኑ በማለት ቀጥታ ሰራዊት ማዘዝ የማይችሉባቸው ቦታዎች ላይ እንዲመደቡ ተደርጓል። በዚህ መሰረት የ24ኛ ክ/ጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ብ/ጄነራል ሹማ አብደታ ከሃላፊነታቸው ተነስተው በሹመት ስም ምንም ጦር ማዘዝ በማይችሉበት ቦታ በሆነው የደቡብ ምስራቅ እዝ ም/ል አዛዥና የሰው ሃብት ልማት ሃላፊ በማለት እንዲመደቡ ተደርገዋል። በብ/ጄነራል ሹማ አብደታ ምትክ የ24ኛ ክ/ጦር ዋና አዛዥ በመሆን ኮ/ል የማነ ገ/ሚካኤል የተባሉ የህወሃት የጦር አዛዥ ተመድበዋል። የ13ኛ ክ/ጦር ዋና አዛዥ የሆኑት ብ/ጄነራል ከድር አራርሳ ቀጥታ ጦሩን ከሚያዙበት ሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጎ በሹመት ስም ምንም ጦር ወደ ማይመሩበት የማዕከላዊ እዝ ም/ል አዛዥና የሰው ሃብት ልማት ሃላፊ በመሆን ተመድበዋል። የ6ኛ ሜካናይዝድ ክ/ጦር ዋና አዛዥ የሆኑት ብ/ጄነራል ከፍያለው አምዴ እንዲሁ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል። የ21ኛ ክ/ጦር ዋና አዛዥ የሆኑት ብ/ጄነራል ዋኘው አማረ ከሃላፊነታቸው ተነስተው በመሃንዲስ ዋና መምሪያ ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርጓል። የአጋዚ ኮማንዶና ልዩ ሃይሎች ጠቅላይ መምሪያ ም/ል አዛዥና የኦፕሬሽን ሃላፊ የሆኑት ብ/ጄነራል ሙላት ጀልዱ ከላፊነታቸው ተነስተው በመከላከያ የስነምግባር መከታተያ ዳይሬክተር በማድረግ ከሰራዊቱ ጋር ቀጥታ ከሚያገናኛቸው ስራዎች እንዲገለሉ ተደርጓል። በርካታ የአማራና የኦሮሞ ከፍተኛ መኮንኖች በሰላም ማስከበር ሰበብ ከሰራዊቱ እንዲገለሉ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ መከላከያ ውስጥ ያሉ ምንጮቻችን ገልጸዋል። በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ሰራዊቱ ተቃውሞውን እንዳይቀላቀል በህወሃት በኩል ከፍተኛ ስራዎች እየተሰሩ ያሉ ሲሆን ለህዝብ ወገኝተኝነት ያሳያሉ የሚባሉ የጦር አዛዦችን ከሃላፊነታቸው በማንሳት ምንም ወደ ማይሰሩበት ቦታዎች በሹመት ስም እየተዛወሩ መሆኑ ታውቋል።
ምስል ከፋይልImage may contain: 10 people, people standing

No comments:

Post a Comment