#FreeNigist #Ethiopia
በእነ ንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ ብይን ለመስጠት በሚል በድጋሜ ቀጠሮ ተሰጥቷል
የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የፍ/ቤት ትዕዛዝ አላከበረም ተብሏል
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የሽብር ክስ የቀረበባቸውን የእነ ንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ የአቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾች የቀረበባቸውን የወንጀል ክስ መከላከል ያስፈልጋቸዋል ወይስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ሊሰናበቱ ይገባል የሚለውን ብይን ለማሰማት ለዛሬ ጥቅምት 21/2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዞ የነበር ቢሆንም፣ ዳኞች መዝገቡን መርምሮ ለመስራት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገናል በሚል በድጋሜ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
አክቲቪስት ንግስት ይርጋን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾችን የያዘው የእነ ንግስት ይርጋ መዝገብ ነሐሴ 12/2009 ዓ.ም ለብይን በሚል ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ ብይኑ አልደረሰም በሚል ለዛሬ ተላልፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ዛሬም መዝገቡ ተመርምሮ ብይኑ ባለመሰራቱ ለሁለተኛ ጊዜ ለህዳር 01/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ቃሊቲ ማ/ቤት የምትገኘው አክቲቪስት ንግስት ይርጋ በእስር ቤት የጥየቃ ሰዓትና የጠያቂ ገደብ ተጥሎብኛል የሚሉና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አቤቱታ አቅርባ ይህ እንዲስተካከል ፍ/ቤቱ ለቃሊቲ ማ/ቤት አስተዳደር ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም ማ/ቤቱ ትዕዛዝን አለማክበሩ ተገልጹዋል፡፡
‹‹ሐምሌ 21/2009 ዓ.ም ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶልኝ ነበር፡፡ ሆኖም ማ/ቤት አስተዳደሩ የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ አክብሮ መብቶቼን ባለማክበሩ በድጋሜ ነሃሴ 12/2009 ዓ.ም አቤቱታ አቅርቤ፣ ለዛሬ ማ/ቤት አስተዳደር ለምን ትዕዛዙን እንዳላከበረ መልስ እንዲሰጥ ታዝዞ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ በማ/ቤቱ አስተዳደር ቢሮ እየተጠራሁ ‹አንቺ ማን ስለሆንሽ ነው ማ/ቤቱን የምትከሽው፣ አንቺ ከማን ትበልጫለሽ እየተባልሁ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠኝ ነው›› በማለት ንግስት ይርጋ ስላለው ሁኔታ አቤቱታ አሰምታለች፡፡
ሌሎችም ተከሳሾች አቤቱታ እንዳላቸው ቢገልጹም ፍ/ቤቱ አቤቱታቸውን በጽሁፍ ካቀረቡ ብቻ እንደሚቀበላቸው በመግለጽ እንዳይይገሩ ከልክሏል፡፡
No comments:
Post a Comment