Sunday, October 29, 2017

በሕወሐት/ኢሕአዴግ ከተሰነዘረብን የሁለት ስለት ሰይፍ ሀገራችንን ለመታደግ ሑሉም በያለበት ዘብ ይቁም!!! (ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ)


ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ በሕወሐት/ኢሕአዴግ ባለ ሁለት ሰይፍ የጥፋት ተልዕኮ በደም እየዋኘች ትገኛለች፡፡ 
የመጀመሪያውና ዋነኛው የሕወሐት/ኢሕአዴግ ሰይፍ ስለት በጥላቻና በልዩነት ላይ ኢትዮጵያን ዘልዝሎና አዳክሞ ለመግዛት የተዘረጋው የአገዛዝ ዘይቤ ሲሆን ይህም ፍሬውን አፍርቶ የኢትዮጵያን ልጆች አባቶቻቸው ሀገራቸውን ከጠላት ለመከላከል ከአንተ እኔ ቀድሜ ልሙት እየተባባሉ በገነቧትና ባቆዩዋት ሀገር ዛሬ ላይ በሕወሐት/ኢሕአዴግ አገዛዝ የአንድ መንደር ሰው(ብሔረሰብ) ለሌላው ባዕድ ሆኖ ወንድሙን በጥላቻ ተነሳስቶ አረመኒያዊና ዘግናኝ በሆነ መንገድ ሲገለውና ንብረቱን ሲያወድመው በአይናችን እያየን በጆሯችን እየሰማን ነው፡፡ በዚህ ድርጊት በወንድሞቻቸው እጅ ህይወታቸው ያለፉ ወገኖቻችን ጉዳይ እጅግ ልብ የሚሰብርና የሚዘገንን ተግባር ከመሆኑም ባሻገር እንደ ሀገርና እንደ ትውልድ ደግሞ የሚያሳፍርና አንገት የሚያስደፋ ተግባር ነው፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን እና በቤንሻንጉል ጉመዝ ክልል ካማሽ ዞን በአማሮች ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ Image may contain: 2 people, text
ሁለተኛው የሕወሐት/ኢሕአዴግ ሰይፍ ስለት ደግሞ በግብር ከፋይ ዜጎች ሀገርን ለመከላከል የተቋቋመው ሰራዊት መለዮውን ለብሶ በባዶ አጃቸው ሰልፍ የወጡና በድንጋይና በእንጨት መንገድ የዘጉ ታደጊ ወጣቶችን ግንባር ግንባራቸውን እያለ ሲገድል እያየን እየሰማን ነው፡፡ በዚሁ ሳምንት በአምቦ ከተማ የተደረገው ድርጊት የሚያረጋግጥልን ሕወሐት/ኢሕአዴግ ማንኛውንም ለስልጣኔ ስጋት ነው ያለውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በጠመንጃ ለመፋለም ያለ ሐፍረት መወሰኑን በተግባር ያየንበት ነው፡፡ 
በአጠቃላይ ሕወሐት/ኢሕአዴግ በስልጣኑ ለመቆየት ሁለቱንም የጥፋት ዘዴዎች ማለትም እርስ በእርስ ማባላትና ከዛ የተረፈውንና በሰላማዊ መንገድ መብቱን የሚጠይቀውን በጥይት ለመቁላት መወሰኑን ከላይ በገለፅናቸው ድርጊቶቹ አረጋግጦልናል፡፡ስለሆነም ሀገራችንን ከዚህ የጥፋት አደጋ ለመታደግና ትግሉን በአሸናፊነት ለመወጣት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣና በያለበት ዘብ እንዲቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ በመጨረሻም በአገዛዙ መሰሪ ሴራና ጥይት ህይታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን፡፡
ጥቅምት 19 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment