ዶክተር አቢይ በመቀሌ ጉዞውና ከተመረጡ የህውሓት አባላት ጋር ባደረገው ምክክር በርካታ ነጥቦች ጥሏል። አንዳንዶቹ በጣም የሚያስደነግጡ ናቸው። ለምሳሌ የአቶ መለስ ዜናዊን የሙት መንፈስ የወረሰ በሚመስል ሁኔታ " የትግራይ ሕዝብ በእሳት የተፈተነ ወርቅ ነው!" በማለት ሲናገር የተሰብሳቢው ጭብጨባ አስደማሚ ነበር። መቼም ይሄ ከናዚዝም የሚቀዳ አነጋገር አቶ መለስን ምን ያህል ራቁቱን እንዳሳየው ዶክተር አቢይ ያጣው አይመስለኝም።
ዶክተር አቢይ አንድን ብሔረሰብ አግንኖ ለማውጣት ከፍ ከፍ ለማድረግ የሚካሄድ ጥረት ሁሉ ከፍተኛ አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል የሚያጣው አይመስለኝም። አንደዚህ አይነት አባባል በሌሎች ላይ ጥላቻ ያሳድራል። የወርቅ ፍልቃቂ የተባለው ጐሳ የገዥነት፣ ከሕግ በላይ የመሆን መንፈስ እንደሚፈጥርበት ሳይታለም የተፈታ ነው። በሂደትም ወደ ነሀስና ብር ብሎም ወደ ጨርቅ የወረደው ሀይል ወደ አመፅ በመሄድ የጥቃት ሰለባ ሊያደርጋቸው ይችላል።
እንደ አንድ ሞጋች ደጋፊው ዶክተር አቢይ ከአቶ መለስ በፍፁም መውረስ የለበትም ብዬ ከምመኘው የመጀመሪያው ነገር " የወርቅ፣ ነሀስ፣ብርና ጨርቅ ብሔር" ጽንሰ አሳብ ነበር። ይሄ ጽንሰ አሳባ አደገኛ ከመሆኑም ባሻገር የንቀት፣ ጥላቻ፣ የብዝበዛና የጭቆናና ኢፍትሐዊነት ይፈጥራል። በዚህ አደገኛ አባባሉ ዶክተር አቢይ ሊያፍር ይገባል። ከእንደዚህ አይነት ከፋፋይና አስቀያሚ ንግግር ራሱን ማቀብ ይኖርበታል። የኢትዬጲያን ሕዝብ በወርቅና ጨርቅ በመከፋፈል ለአንዱ ኩራት ለሌላው ውርደት የፈጠረውን፣ አደህይቶ የገዛውን፣ አገርን ታሪክ አልባ ያደረገውን፣ አሰቃይቶ መግዛት ፓሊሲው ያደረገውን መለስ ዜናዊ በአንደበቱ ማሞካሸት ያሳፍራል። ያሳቅቃል።
#ነጥብ ሁለት: " ማይ መቐለ!"
ዶክተር አቢይ አህመድ በዛሬው የመቀሌ ንግግሩ፣
" የመቀሌን ውሃ በተመለከተ ምንም የማውቀው ነገር የለም። የመቀሌ ውሃ መቼ ተጀመረ፣ የት ደረሰ ሚስጥሩን አላውቀውም። የትግራይ ህዝብ እንዲያውቅ የምፈልገው አንድ ጉዳይ ቢኖር የመቀሌም፣ የአክሱምም፣ በሙሉ በትግራይ ያለ የመጠጥ ውሃ ጉዳይ የፌዴራል መንግስትን አይመለከትም። መቶ ፐርሰንት የክልል ስራ ነው" ነበር ያለው።
ይሄንን የዶክተር አቢይ ምላሽ ስሰማ በጣም ደንግጫለሁ። ዶክተሩ ተረጋግተው መቀመጥ ባለመቻላቸው አጠገባቸው ምን እየተሰራ እንደሆነ ማወቅ አለመቻላቸውን አመላክቶኛል። "በሙሉ በትግራይ ያለ የመጠጥ ውሃ ጉዳይ የፌዴራል መንግስትን አይመለከትም፣ መቶ ፐርሰንት የክልሉ መንግስት ነው" ማለታቸው ከመረጃ እጥረት የመነጨ ወይንስ ሽምጥጥ አድርጐ መካድ ይሆን የሚል ጥያቄ ጭሮብኛል። እንደ ሞጋች ደጋፊነቴ ላምናቸው ስለምፈልግ ዶክተሩ ተረጋግቶ ባለመቀመጥ ምክንያት የመረጃ እጥረት አጋጥሟቸዋል ብዬ ማመን እፈልጋለሁ።
እናም ለዶክተሩ መረጃውን ልሙላላቸው።
#የህውሓት ንብረት የሆነው ሬዲዬ ፋና ከትላንት ወዲያ እንደዘገበው የፌዴራል መንግስቱ የመቀሌን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በሁለት እጥፍ ለማሳደግ 8ቢሊዬን ብር ከቻይና መንግስት ተበድሮ የግድብ ግንባታ ጀምሯል። በዘገባው መሰረት " የሰሜኗ ኮከብ መቐለ!" በየቀኑ የሚያስፈልጋት የውሃ መጠን 50ሺህ ሜትር ኪዩብ ነው። በአሁን ሰአት እየቀረበላት ያለው ደግሞ 25ሺህ ሜትር ኪዩብ ( 50 በመቶ) ያህል ነው።
የትግራይ ክልላዊ መንግስት በራሱ በጀት 18ሺህ ሜትር ኪዩብ የሚያስገኝ ግድብ አጠናቋል። ከላይ ከተጠቀሰው ጋር ስንደምረው " የሰሜኗ ኮከብ!" የቀን አቅርቦቷ 43ሺህ ሜትር ኪዩብ ይሆናል። መሰረታዊ የሂሳብ ስሌቶችን ተጠቅሞ መደመርና መቀነስ ለሰራ ( አባዱላን አይመለከትም) መቐለ የቀን ፍላጐቷን ለማሟላት የሚቀራት 7ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ብቻ ነው።
አሁን ወደ ፌዴራሉ የቻይና ብድር እንመለስ። የፌዴራል መንግስቱ ከቻይና ተበድሮ ( ወለዱ ስንት እንደሆነ አልተገለጠም) ለመቐሌ በሚሰጠው 8ቢሊዬን ብር ተጨማሪ በየቀኑ 147ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ አቅርቦት ይኖራል። አሁንም መደመርና መቀነስ ሲሰራ በአጠቃላይ በመቀሌ በቀን የሚመነጨው የመጠጥ ውሃ መጠን ከፍላጐቱ በ140ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ብልጫ ይኖረዋል።
እንግዲህ ፍርዱን ለዶክተር አቢይና አንባቢያን እተዋለው። ፌዴራል መንግስቱ በመቶ ሚሊዬን የኢትዬጲያ ህዝብ ስም 8 ቢሊዬን ብር ተበድሮ ( ያውም የወለድ መጠኗ እስከ 35% የምታደርሰው ቻይና) ለመቐሌ እየሰጠ እውቀት የለኝም ማለት ምን ማለት ነው? በፓርቲ ሚዲያ ለአለም ህዝብ የተገለጠ መረጃ አለማንበብ ማለት ምን ማለት ነው? ፌዴራል መንግስቱ ያን ያህል ገንዘብ ተበድሮ ሲያበቃ " ክልሉ እንጂ ፌዴራል አያገባውም!" ብሎ መናገር አያሸማቅቅም ወይ? ሐይለማርያም ደሳለኝ ( የቀድሞ ተጠቅላይ በሉኝ ብሏል!) በአንድ ወቅት መረጃዎች አይደርሱኝም ብሎ ከተናገረው በምን ይለያል?
የንፁህ መጠጥ ውሃን በተመለከተ የቀረምኳቸውን አንዳንድ መረጃዎች ለዶክተር አቢይ ላካፍለውና የመጀመሪያ ክፍል ፅሁፌን ላጠናቅ። ተጨማሪ መረጃዎች ካሉ እባካችሁ አንባቢያን ጨምሩለት።
#አንደኛ: -የከተሞችን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት ብድር የተገኘው በፈረንጆቹ አቆጣጠር Nov 2011 ከቻይና መንግስት ነው። የብድሩ መጠን 100 ሚሊዬን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን የብድሩ ተጠቃሚ አዲስ አበባ ነበረች። ሁለተኛው ብድር የተገኘው May 2012 ከአለም ባንክ ሲሆን የብድሩ መጠን 150 ሚሊዬን የአሜሪካ ዶላር ነው። የብድሩ ተጠቃሚ የሆኑ ከተሞች አዲሳአባ፣ ጐንደር፣ ሐዋሳ፣ መቐሌ፣ ጅማ፣ ድሬደዋ ነበሩ። የከተሞች የህዝብ ብዛት በቅደም ተከተል አዲሳአባ፣ አዳማ፣ ጐንደር፣ መቀሌ፣ ሐዋሳ መሆኑን ማእከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን ያሳውቃል።
#ሁለተኛ :- በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና በውሃ ጉዳዬች ላይ ጥናት በሚያደርግ water.org ጥናት መሰረት 61 ሚሊዬን የሚጠጋው የኢትዬጲያ ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አያገኝም።
ሞጋች ደጋፊ ስህተቶቹን ብቻ ነቅሶ የሚያወጣ ሳይሆን የመፍትሔ ሃሳቦችንም ይጠቁማል። በዚህ መሰረት ዶክተር አቢይ በተሰጠው ስልጣን ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ የሚከተለውን እንዲያደርግ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
#1: የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክት ድልድል በህዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋት ከሆነ በኢህአዴግ መቃብር ላይ ይሆናል ያለውን አቶ አባይ ፀሀዬ ከመንግስታዊ ስልጣኑ በአስቸኳይ ማባረር።
#2: የህውሓት ስራ አስፈፃሚና የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር የሆነውን ዶክተር አብርሃም ተከስተ መጥራት። ለከተሞች ፌዴራል መንግስት ባለፋት 5 አመታት ለመጠጥ ውሃ የተወሰዱ ብድሮችን ለኢትዬጲያ ሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ማድረግ። በፓርላማም ቀርቦ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጥ ማድረግ።
…//…