Saturday, April 14, 2018

የለውጥ እንቅስቃሴን ለማራመድ ለሀገር አቀፍ ሕዝባዊ እምቢኝነት ዝግጁ እንሁን (የአርበኞች ግንቦት 7 ርዕሰ አንቀጽ)

የዶ/ር አብይ አህመድ በጠ/ሚኒስትርነት መሾም በሕዝባዊ ትግሉ ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው በርካታ ወገኖች ጥያቄ አቅርበዋል።

በንቅናቄዓችን ሰነዶች ላይ በግልጽ እንደሰፈረው የአርበኞች ግንቦት 7 ራዕይ “እያንዳንዱ  ኢትዮጵያዊ  ዴሞክራሲያዊና  ሰብዓዊ  መብቱ  የተከበረበት፤  የኢኮኖሚ ብልፅግናና  ማኅበራዊ  ፍትህ  የሚገኝበት፤  የዜጎች  ሕይወት፣  ደህንነትና  ጥቅም  የተከበረበት  እና  የሕዝቧ  አንድነትና  ትስስር የጠነከረበት ሃገር ኖሮት ማየት ነው።”
የአርበኞች ግንቦት 7 ተልዕኮ ደግሞ “የመንግሥትና  የፖለቲካ  ሥልጣን  በሰላማዊና  ዴሞክራሲያዊ  ሂደት  የሚያዝበት፤ የሃገሪቱ  ዜጎች  ምርጫ  በተግባር  የሚገለፅበት፤  ማኅበራዊና  የፖለቲካ  ችግሮች  በዲሞክራሲያዊ  መንገድ  የሚፈቱበት  እና ዲሞክራሲያዊ ባህል የሚበለፅግበት ብሄራዊ የፖለቲካዊ ሥርዓት እንዲገነባ ማገዝ ነው።”
የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ከንቅናቄዓችን ራዕይና ተልዕኮ የተለየ አይደለም። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሩ ባለቤት መሆን ይፈልጋል፤ መሪዎቹን በነፃነት መምረጥና መሻር እና በአገራችን ማኅበራዊ ፍትህ ሰፍኖ ማየት ይሻል።
ዶ/ር አብይ አህመድ ይህን የሕዝብ ፍላጎት ማሳካት የሚችሉ መሪ ናቸውን?

ዶ/ር አብይ አገራዊ አንድነትን የሚያራምዱ፤ ማኅበራዊ መግባባትን የሚሹ፤ ሁሉንም የፓለቲካ ኃይሎችን ለማሳተፍ የሚጥሩ መሆኑን በንግግራቸው ገልፀዋል። ይህ ቀና እና የሁላችንም ድጋፍ የሚሻ ዓላማ ነው።
በአንፃሩ ግን ዶ/ር አብይ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ወደ ስልጣን ያወጣቸው እንጂ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሂደት በሕዝብ የተመረጡ መሪ አይደሉም። ስለ ዶ/ር አብይ የለውጥ ግቦች ከንግግሮቻቸው ከሰማነው በላይ በዝርዝር የቀረበ ሰነድ የለም፤ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ምን ያህል ፍላጎት እንዳላቸው ግልጽ አይደለም። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከፍላጎት በላይ እነዚህን ለውጦች ተግባራዊ ለማድረግ ያላቸው ድርጅታዊ  አቅም ገና አልታየም።
ዶ/ር አብይ አህመድ የለውጥ ኃይል ናቸው ብሎ ማመን የሚቻል ቢሆንም እንኳን በለውጡ ተፃራሪ ኃይሎች ተከበዋል። እነዚህ ፀረ-ለውጥ ኃይሎች የህወሓት/ኢህአዴግ አፋኝ፣ ከፋፋይና ዘራፊ ሥርዓት እንዲቀጥል የተለያዩ ግልጽ እንቅፋቶችና ስውር አሻጥሮች መፈፀማቸው አይቀርም፤ አሁንም እየፈፀሙ ነው። እነዚህ የአፈናና የዘረፋ ኃይሎች ጦር ሠራዊቱን፣ የስለላ መዋቅሩን፣ ኢኮኖሚውንና ሚዲያውን ተቆጣጥረውታል።
የህወሓት/ኢህአዴግ ፀረ-ለውጥ አንጃ በጦር ሠራዊቱ፣ በስለላው፣ በሚዲያውና በኢኮኖሚ ላይ ያለው የበላይነት ተነጥቆ እንዲዳከም ካልተደረገ ኢትዮጵያዊያን ለምንፈልገው የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ ብቻ ሳይሆን ዶ/ር አብይ አህመድ ተግባራዊ አደርገዋለሁ ለሚሉት ለውጥም ስጋት መሆናቸው አይቀርም።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልጋቸውን ለውጦች ተግባራዊ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ዶ/ር አብይን ከህወሓት/ኢህአዴግ ፀረ-ለውጥ ኃይል ለመከላከል በመላው ኢትዮጵያ ሕዝባዊ እምቢተኝነት መቀጣጠል ይኖርበታል።  ሥርዓቱ አሁንም ሕዝብን ለመፍጀት ወታደሮቹን ማሠማራቱ አይቀርም።  በእንዲህ ዓይነት ወቅትም ራስን የመከላከል እርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል።
ስለሆነም በመላው የአገራችን ክፍሎች የሚገኙ አባሎቻችን እና ደጋፊዎቻችን እንዲሁ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገር አቀፍ ለሆነ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንድትዘጋጁ ጥሪ እናደርጋለን። ይህን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ፈር ለማሳት የህወሓት/ኢህአደግ ፀረ-ለውጥ ቡድን የተለያዩ የተንኮል አሻጥሮችን መፈፀሙ አይቀርም፤ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት ቀዳሚ ሴራ እንደሚሆን የሚጠበቅ ነው።
የህወሓት/ኢህአዴግ ፀረ-ለውጥ ቡድን ሴራን ለማክሸፍ በመላው የአገራችን ክፍሎች በተመሳሳይ ጊዜና  በተመሳሳይ አጀንዳ አገራዊ ሕዝባዊ እንቢተኝነት በአዲስ ጉልበት እንዲቀሰቀስ ማድረግ ይኖርብናል። ዓላማችን ለሁላችንም የምትመች ኢትዮጵያን መፍጠር በመሆኑ ከጎን የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ለጋራ ጉዞዓችን መሰናክል እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይገባል።
እንዘጋጅ፣ እንደራጅ፤ ለሀገር አቀፍ ሕዝባዊ እምቢኝነት ዝግጁ እንሁን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment