Monday, April 16, 2018

ኢትዮጵያዊነት ማለት አንዱዓለም ተፈራ (እስከመቼ)

“ኢትዮጵያዊነት ማለት፤ ኢትዮጵያዊያንን መውደድ፣ ኢትዮጵያን ማፍቀር፤ የኢትዮጵያን መንግሥት በተገቢው መንገድ መደገፍና፤ ይህ መንግሥት የተሳሳተ መንገድ ሲይዝ መቃወም ማለት ነው። በሥልጣን ላይ ያለው ክፍል ፀረ-ኢትዮጵያዊያንና ፀረ-ኢትዮጵያ ሲሆን፤ ያንን ክፍል በማንኛውም መንገድ ማስወገድ፤ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና የያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት፤ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው።”
አብዛኛዎቻችን በየጊዜው የምናነሳው ጉዳይ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን የፖለቲካ ሀቅና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ነው። ኢትዮጵያዊ ነኝ ወይንም አይደለሁም የሚለውን ጥያቄ አይደለም። በየቦታው፣ በተገኘው አጋጣሚ፣ በየዕለቱ በሕዝቡ ላይ የሚደረገውን በደል እናውጠነጥናለን። ኢትዮጵያዊያን ናቸው ወይንም አይደሉም የሚለው ከጥያቄያችን መካከል አይደለም። መቼም አርባ ዓመት ሙሉ፤ በአረመኔው መንግሥቱ ኃይለማርያምና በወገንተኛው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የደረሰውን ግፍና በደል ገና ብዙ ፀሐፊዎች ብዙ ይውሉበታል፣ ሊቃውንት ይቀኙበታል፣ አንጎርጓሪዎች ይደረድሩበታል፣ ሰዓሊዎች ያቀልሙታል፣ ገጣሚዎች ይሰነኙበታል፣ መጽሐፎች ይደረሱበታል። ያ ግን፤ ከኛ ቀጥለው የሚመጡት ኢትዮጵያዊያን፤ ስለኛ ስለቀደምናቸው ኢትዮጵያዊያን ለማወቅ የሚያደርጉት ጥረት ውጤት ነው እንጂ፤ ኢትዮጵያዊ ስለመሆናችን ወይም ኢትዮጵያዊ ስላለመሆናችን አይደለም።
እንግዲህ የአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? የሚለውን በደንብ መረዳት አለብን። ይኼን ስናደርግ፤ የሀገራችንን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሀቅ በትክክል እንረዳና፤ በኢትዮጵያዊነታችን፤ ምን ማድረግ እንዳለብንና ማን ኢትዮጵያዊነቷን እየተወጣች እንደሆነች እንገነዘባለን። ትናንትም፣ ዛሬም ነገም ኢትዮጵያዊነት ማለት፤ ኢትዮጵያዊያንን መውደድ፣ ሀገርን ኢትዮጵያን ማፍቀር፤ የኢትዮጵያን መንግሥት በተገቢው መንገድ መደገፍና፤ ይህ መንግሥት የተሳሳተ መንገድ ሲይዝ መቃወም ማለት ነው። በሥልጣን ላይ ያለው ክፍል ፀረ-ኢትዮጵያዊያንና ፀረ-ኢትዮጵያ ሲሆን፤ ያንን ክፍል በማንኛውም መንገድ ማስወገድ፤ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና የያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት፤ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው። ወራሪ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ፤ ይህ ግዴታ፤ ወደ መኖር ወይንም አለመኖር የሕይወት ትንቅንቅ ስለሚያመራ፤ አማራጭ የማይሠጥ ጥሪ ይሆናል። ይህ ፖለቲከኛ መሆንን ወይንም አለመሆንን አይጠይቅም። ይህ ታጋይ መሆንን ወይንም አለመሆንን አይጠይቅም። ይህ ሀገራዊ ግዴታን ነው የሚገልጸው። ይህ የኢትዮጵያዊ ሕይወት፣ የትናንት፣ የዛሬና የነገ ሕልውና ጥያቄ ነው። አሁን በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ፤ ኢትዮጵያዊ መንግሥት የለም። ሕግና ሥርዓት የሚያከብር ቡድን አይደልም በሥልጣን ላይ ያለው። ራሱ የሚያወጣቸውን ሕጎች የሚያፈርስ፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የተነሳ ክፍል ነው በሥልጣን ላይ የተቀመጠው። ኢትዮጵያዊያንን እየከፋፈለ፣ አንድነት እንዳይኖረን የሚጥር መንግሥት በሥልጣን ላይ አለ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ፤ “ኢትዮጵያዊ ነኝ። አልከፋፈልም። ጠላታችን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነው።” እያለ ትግል ይዟል። ስለዚህ፤ የአሁኗ ኢትዮጵያዊትና የአሁኑ ኢትዮጵያዊ፤ ኢትዮጵያዊ ግዴታችን፤ ይኼን ፀረ-ኢትዮጵያዊያን መንግሥት ከታጋዩ ህዝብ ጎን ተሰልፎ ማስወገድ ነው። ሕዝባዊ ንቅናቄ ከፊታችን ተደግኗል። የውዴታ ሳይሆን ግድ ሆኖብን፤ የምርጫ ሳይሆን አማራጭ ሳይኖረን ንቅናቄው አፍጥጦብናል። የዴሞክራሲ ቅንጦት ሳይሆን የሀገር አድን ጥያቄ ቀርቧል።
ባጭሩ ኢትዮጵያዊነት ማለት፤ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ወራሪ መንግሥት ማወገድ ነው። ይኼን የኔ ብሎ ያልተነሳ ግለሰብ፤ ኢትዮጵያዊነቱ ምኑ ላይ ነው? በርግጥ ትግሉ ረጅም ነው። ትግሉ የተመሰቃቀለ ነው። በሥልጣን ላይ ተቀምጦ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍናውና መመሪያው የሆነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብቻ ሳይሆን፤ ይኼኑ ፍልስፍናና መመሪያ የራሳቸው ያደረጉ ሌሎች ክፍሎችም የኢትዮጵያዊነት ትግላችን አንድ ክፍል ናቸው። በትግሉ ውስጥ ያለን ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ይኼን ሀቅ አጥብቀን መያዝ አለብን። ኢትዮጵያ ለዘመናት መንግሥት ኖሯት ስትተዳደር የነበረች ሀገር ለመሆኗ አጥጋቢ መረጃዎች አሉ። እኒህ መንግሥታት በየተከሰቱበት የታሪክ ወቅት፤ በጎም ሆነ በጎነት የጎደለው ተግባር አከናውነው አልፈዋል። በዚህ ረጅም ታሪካችን፤ የመንግሥታዊ ማዕከላቸውን በሰሜን ወይንም በደቡብ፤ በምሥራቅ ወይንም በምዕራብ እንደታሪካዊ ወቅቱም ተንቀሳቃሽ በማድረግ፣ የተለያዩ የጦር አሠላለፍን በማዘጋጀት፣ ጥንካሬያቸው እንደፈቀደላቸው፤ የሀገሪቱንም ደንበር ሲያሠፉና ስትጠብባቸው ነበር። አንዱ ከሌላው ጎጥ፤ ሃይማኖት ሳያግደው፣ የዘር ሐረግ ሳይከለክለው፣ እንደ ጥንካሬያቸውና የፖለቲካ ግኘታ አመቺነታቸው ሲጋቡና ሲዋለዱ ነበር። በኢትዮጵያዊነት ገዝተዋል። እናም በተለያዩ ጊዜያት፤ በተለያዩ መንግሥታት ዘመን፤ የተለያዩ ህዝባዊ ጥያቄዎች ተነስተዋል። ሕዝባዊ አመፆች ተካሂደዋል። መፈንቅለ መንግሥት ተደርገዋል። በንጉሥ ላይ ንጉሥ ተነስቷል። ንግሥታት ዘውድ ጭነው ገዝተዋል።

የውጭ ሀገር ጉልበተኛ መንግሥታት ሀገራችን ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖራት የተጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም። እንዲያውም ከሞላ ጎደል የሀገራችን የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ከውጭ ወራሪዎችና ጣልቃ ገቦች ጋር የመኖርና ያለመኖር ተጋድሎ ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል። አሁንም የውጭ ኃይላት ለጥቅማቸው ሲሉ ያላቸው እርጎ ዝምብነት ትልቁ በሽታችን ነው። አሁን በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን በጠቅላላው በውጭ ሀገር መንግሥታት ላይ ልናደርግ የምንችለው ጫና ወይንም ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው የምናደርገው ጥረት፤ የትም አይደርስም። ይልቁንስ በራሳችን መካከል ያለውን ጥንካሬ በአንድነት በመሰባሰብ ብናጎለብት፤ እኛ ወደነሱ ለአቤቱታ ከመሄድ፤ እነሱ ወደኛ ለጥቅማቸው የሚመጡበትን መንገድ እንፈጥራለን። የሚረዱት ቋንቋ፤ የራሳቸው ጥቅምና የኛ ጥንካሬ ብቻ ነውና! ሆኖም ወደኛ ስንመለስ፤ በዚህ በሀገራችን የታሪክ ጉዞ፤ ኢትዮጵያዊነት በጥያቄ ውስጥ ገብቶ አያውቅም። ለምን?
አንድ ግለሰብ በመንግሥት ውስጥ የያዘው የሥልጣን ደረጃ፣ ያለበት ድርጅት አባልነቱ፣ የተወለደበት አካባቢ፣ የሚናገረው ቋንቋ፣ ያለው የሀብት ብዛት ወይም ማነስ፣ የትውልድ ሐረጉ መሠረት፤ የግለሰቡ ብሶት ወይም ምቾት፤ ይህ ሁሉ አንድን ኢትዮጵያዊ ከሌላዋ ኢትዮጵያዊት ያነሰ ወይንም የተለቀ ኢትዮጵያዊ አያደርግም። ሁላችን ኢትዮጵያዊያን፤ በአንድነት ሙሉ ኢትዮጵያን እንጋራታለን። የጋራ ሀገራችን ናት። የነበሩት፣ ያለነውና የሚመጡት ሁላችን በአንድነት ባለቤቶች ነን። አንድ የተቧደነ ክፍል፤ በመንግሥት ደረጃ ሥልጣን ላይ ወጣም ወይንም በተቃውሞ አፈነገጠ፤ የኢትዮጵያ ግለኛ ባለቤት ወይንም የኢትዮጵያዊነትን ትርጉም ሠጪና ነሽ አይደለም። ይህ ደግሞ ነገሥታትንና ማንኛውንም በሥልጣን ላይ የሚወጣን ክፍል ይጨምራል። ኢትዮጵያዊነት በሥልጣን ላይ የሚወጣው መንግሥት ወይንም አንድ ጅንን ግለሰብ ትርጉም የሚሠጠው ጉዳይ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ከዚያ በላይ ነው። የታሪክ ትስስር ነው። እትብት ነው።
አይደለሁም ብሎ እስካላፈነገጠ ድረስ፤ አንድ ግለሰብ፤ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በመወለዱ ኢትዮጵያዊ ነው፤ ወይንም የኢትዮጵያ ዜግነት አለው። ኢትዮጵያዊነት የሀገረ ኢትዮጵያ ዜጋ ሆኖ መገኘት ነው። ኢትዮጵያዊነት በዜግነት ላይ የተመሠረተ የግለሰብ ሀገራዊ መብት እንጂ፤ የስብስብ ወይንም የአካባቢ ጥምር መብት አይደለም። “በግል ወይንም በአካባቢ በደል ደርሶብኛልና ኢትዮጵያዊነት ለኔ ምን ያደርግልኛል?” የሚለው አባባል፤ በቀላሉ ሲታይ የየዋህነት አለዚያ ደግሞ የመሠሪነት ገጽታ ነው። መገንዘብ ያለብን፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሠረት አድርጎ የተነሳው፤ በራሳቸው መሥራችና የጦር መሪ አረጋዊ በርሄ እንደተገለጸልን፤ አፄ ሚኒሊክ የጣሊያንን ወራሪ ጦር ለማባረር ትግራይ ሲሄዱ፤ ለወታደሮቻቸው ምግብ እንዲያቀርብ፤ የትግራይን ገበሬ ስላዘዙት ነው። እናም ሀገርን ከወራሪ ለማዳን የዘመተን ጦር መመገብ በደል አድርገው ቆጥረው፤ የዛሬዎቹ ገዝዎቻችን ተስባስበው ደደቢት ገቡ። ኢትዮጵያዊነት ገደል ይግባ አሉ። አሁንም በደደቢቱ ግንዛቤያቸው ኢትዮጵያን ወረዋል። መንግሥታቸው ኢትዮጵያዊ አይደለም። ሌሎችን በሚመለከት፤ እስኪ አስቡ፤ በደል አለብኝ ባይ ኢትዮጵያዊነቱን በጥያቄ ውስጥ ካስገባ፤ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ምን ለየው?
“ኢትዮጵያዊ አይደለሁም፤ ሌላ ነኝ።” ማለት፤ የግለሰብ መብት ነው። ያ በግል፤ አንድ ግለሰብ፤ ለራሱ ለግለሰቡ የሚሠጠው ዜጋ የመሆን ወይንም ያለመሆን ጉዳይ እንጂ፤ አንዱ ለሌላው ሊሠጠው ወይንም ሊነፍገው የሚችል ዜግነት አይደለም። በመንግሥት ደረጃ፤ ትክክለኛውን የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት በመከተል፤ ለአዲስ አመልካቾች ዜግነት ሊሠጥ ወይንም ሊነፈግ ይቻላል። ኢትዮጵያዊ የሆነውን ዜጋ ግን፤ በምንም መንገድ ኢትዮጵያዊ አይደለህም ሊል የሚችል ማንም የለም። ግለሰብ ኢትዮጵያዊ ሲያጠፋ በሕግ ይጠየቃል። ፀረ-ኢትዮጵያ ተግባር ሲሠራ ደግሞ፤ በከሃዲነቱ ባንገቱ ላይ ሽምቅቅ ያርፍበታል። ሀገር አስመስጋኝ ተግባር ሲፈፅም፤ የሀገር ታዋቂነትን ያገኛል። ኢትዮጵያዊነት ይህ ነው። በወራሪ መንግሥት ላይ ማመጽ፤ አርበኝነት እንጂ፤ ወንጀል አይደለም። ይህ ለግለሰብ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ተቋማትም ይሠራል። አስመስጋኝ ተግባር ሲያከናውኑ፤ ሀገራዊ ታዋቂነት ይሠጣቸዋል። ፀረ-ኢትዮጵያ ሲሆኑ ይዘመትባቸዋል። እንደግለሰቡ ሽምቅቅ፤ ለተቋማቱ ደግሞ ፍፃሜያቸውን የሚያገኙበት ክንውን ይደረጋል። መንግሥትም ሀገራዊ ተቋም ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ፀረ-ኢትዮጵያ ነው። እናም ፍፃሜውን ማምጣት፤ ኢትዮጵያዊ ግዴታችን ነው።
“እኔ አንድ ግለሰብ ነኝ። ምን ማድረግ እችላለሁ?” በማለት ኢትዮጵያዊ ኃላፊነታችንን ከኛ ማራቅ አንችልም። ኢትዮጵያዊነት አንዴ የሚመጣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚሸሽ ጥላ አይደለም። ሁሌም አብሮን አለ። በደማችን ውስጥ ፈሳሹ፣ በአጥንታችን ውስጥ ጽናቱ፣ በቆዳችን ላይ ሰብሳቢ ክኑ ነው። በድርጅት ተሰባሰብን ወይንም የመንግሥት ሠራተኛ ሆን፤ ኢትዮጵያዊነታችን አይለወጥም። ኢትዮጵያዊነትን ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ሆነን የምንጠይቀው ጉዳይ አይደለም። ነን ወይንም አይደለንም? ብቻ ነው መለኪያው። ግማሽ ኢትዮጵያዊ የለም። ሩብ ኢትዮጵያዊት የለችም። “ቆይቼ እሆናለሁ አሁን ተበድያለሁ።” ብለን በቆይታ የምናስቀምጠው ጉዳይ አይደልም። በደል ሌላ! ማንነት ሌላ!
እኛ አሁን ኢትዮጵያዊያን ነን ብለን፤ በዚህ በዘመናችን የኖርንበትና የምንኖርበት፤ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነታችንን አስመልክቶ፤ ምን እያደረግን ነው? የሚለው ደግሞ የዛሬ ጥያቄ ነው። በመካከላችን የተለያየ መልስ የምንሠጥ አለን። ከነዚህ መካከል በዚህ በያዝነው ወቅት ነበርን ለማለት የሚያስችል ምልክታችን ምንድን ነው? የወቅታችን ማመልከቻ ሆኖ የሚታየው፤ አንድም በደሉን በመፈጸም የተሠለፉት ጥቂት የሥልጣን ጥመኞች እና በዝርፊያ በሕዝቡ ገንዘብ ለግላቸው የገነቧቸው ሕንፃዎች ሲሆኑ፤ ሌላ ደግሞ እኒህን ሲታገሉ ሕይወታቸውን ለሕዝቡ ድል የሠጡት ናቸው። በመካከል የሠፈርነው ከሞላ ጎደል ብዙዎቻችን፤ እድሜያችንን ቆጥረን ከማለፍ በላይ የምናስመዘግበው የለንም። በእርግጥ ትግል ተደራጅቶ ነው። ብዙ የሚታገሉ ድርጅቶች አሉ። የድርጅቶቹ ታሪክና የአሁን ሁኔታ ደግሞ አያስመረቃም። ነገር ግን ሌሎቻችን እጅና እግሮቻችንን አጣጥፈን በመቀመጥና “እነሱ” እያልን ተደራጅተው በሚታገሉት ላይ እጣቶቻችንን በመቀሰር፤ ከኢትዮጵያዊ ኃላፊነታችን ነፃ መውጣት አንችልም። ድርጅት መኖሩ ታጋዮች የሚያደርጉትን ጥረት አመልካች ነው። ከነዚህ ጋር መተባበር ካልቻልን፤ ድርጅቶቻቸውን እንደጣዖት የሚያመልኩና ከሀገራቸው ከኢትዮጵያ የሚያስቀድሙ ከሆነ፤ ሌሎችን በማስተባበር እንዲስተካከሉ የማድረጉ ኃላፊነት ከራሳችን አይወርድም። ድርጅት ምክንያት ሆኖ ከኢትዮጵያዊ ኃላፊነታችን ነፃ አያወጣንም። እነ ርዕዩት ዓለሙ፣ እነ አንዱዓለም አራጌ፣ እነ እስክንድር ነጋና የእስልምና እንቅስቃሴው ተወካዮች፤ የድርጅት አባል ስለሆኑ ወይንም ስላልሆኑ አይደለም የታሠሩት። ግለሰቦቹ እንጂ ድርጅት አይደለም የታሠረው። የታሠሩት ኢትዮጵያዊ መብታቸውን ስለጠየቁ፤ በሥልጣን ላይ ያለውን ፀረ-ኢትዮጵያ ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በመቃወማቸውና ለገዥው ክፍል ጉቦም ሆነ የገጠጠ እብሪት አንገታቸውን ባለመድፋታቸው ነው። ባጭሩ ኢትዮጵያዊ ሆነውና ኢትዮጵያዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ በመገኘታቸው ነው።
ታዲያ እንዲህ ያሉ ታጋዮች በእስር ቤት በሚማቅቁበት ወቅት፣ አብዛኛው ሕዝብ እንደሁለተኛ ዜጋ በሚንገላታበት ሀገር፣ መሳደዱና መገፋቱ ሀገርን እንደ የእሳተ ጎመራ ግንፍል እየሮጡ ለማምለጥ ብዙዎቹ በሚሽቀዳደሙበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነታችን ምን እንድናደርግ ያስገድደናል? በድርጅት ዙሪያ የልተካተቱ ግለሰቦች በተደጋጋሚ ከሚሠጧቸው ምክንያቶች አንዳንዶቹ እኒህ ናቸው፤
“ድርጅት ለኔ አይመቼኝም። ሃሳቤን በነፃ የማካፍልበትን መድረክ ብቻ ነው የምፈልገው።
“ድርጅት ለኔ አልጣመኝም። ከዚህ በፊት የነበረኝ ተመክሮ አስቸጋሪ ነበር።”
“እኔ ሌሎች ወደ ተግባር እንዲሄዱ በሃሳብ ልረዳ እችላለሁ።”
“የትግል ማዕከል እኮ የለም። የተያዙት መሥመሮች በሙሉ ትክክል አይደሉም።”
“እኔ በሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ዙሪያ እየሠራሁ ነው።”
“ድርጅቶች እኮ የሚረቡ አይደሉም። እውነተኛ ድርጅት የት አለና!”
“ትንሽ ጊዜ መቆዬት እፈልጋለሁ።”
የሚሉት ናቸው። እኒዚህና የመሳሰሉትን በመደርደር ከኢትዮጵያዊ ግዴታ ለማምለጥ መሞከር ሀቁ ምንድን ነው? በተለይ በአሁኑ ሰዓት! በየጊዜው የሀገራችን የኢትዮጵያንና የህዝቧን ሁኔታ እያነሳን፤ በብዙ የመገናኛ መንገዶች ሁሉ ጽፈናል፣ ተርከናል፣ አንብበናል፣ ተንትነናል። አሁን በያዝነው መንገድ እየተጓዝን የትም አንደርስም። ተባብረን መታገል ያለብን መሆኑ ግልጽ ነው። ዋናው “ሌሎች ይተባበሩ!” “ድርጅቶች ይተባበሩ!” “ህዝቡ ይተባበር!” ማለቱ አይደለም። እኛስ በግለሰብ ደረጃ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ምን ኃላፊነት አለን? እያልን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ሀገራችን ለሁላችን እኩል ናት። መደራጀታችን ወይንም አለመደራጀታችን ያነስን ኢትዮጵያዊያን አያደርገንም። የሀገራችን ችግር የተደራጁ ኢትዮጵያዊያን ችግር ብቻ አይደለም። ታዲያ ኃላፊነቱን እኩል መካፈል አለብን። እናም እኛስ ምን እንደርግ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እና እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት፤ ተደራጁም አልተደራጁም እኩል ኃላፊነት አለብን። እናም እያንዳንዳችን መፍትሔ ፍለጋውና የመፍትሔው አካል መሆኑ ላይ፤ እኩል ድርሻ ሊኖረን ይገባል። ይህ የሀገር አድን ወቅት ነው።
ትግሉ የራሱ የሆነ ዕድገት ያለው፤ ሕጉ የማይታወቅበት ሂደት ነው። አሁን በረጋ መንፈስ ባጭር ጊዜ ውስጥ በቀላሉ የምንችለውን የትግል ማዕከል የመፍጠር ሂደት ብናዘገየው፤ ተቀምጠን የተውነውን ቆመን የማናገኝበት ጊዜ ይመጣል። ዛሬ በግልፅ መነጋገር፣ መሰባሰብና ትግሉን በአንድነት ማድረግ ካልቻልን፤ ነገ ይኼ መሰባሰብ ላም አለኝ በሰማይ ይሆንና ቁጭቱ፤ ድሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ወጪት ጥዶ ማልቀስ፤ ይሆንብናል።
ለድርጅቶችም ሆነ ለግለሰቦች አሁን ኢትዮጵያዊ ጥሪው፤ አንድነት በኢትዮጵያዊነታችን እንድንሰባሰብ ነው። የምንሰባሰበው ለወገናችን ለመድረስ፣ ሀገራችንን ነፃ ለማውጣት ነው። የምንሰባሰበው በኢትዮጵያዊያን የነፃነት ንቅናቄ እንዋቀራለን። ይህ የትግሉ ማዕከል ይሆናል። ይህ የነፃነት ንቅናቄ፣ የትግሉን ራዕይና ተልዕኮ በግልፅ አንጥሮ በማውጣት፤ በአደባባይ ሕዝባዊ ንቅናቄውን ይመራል። ይህ ማዕከል፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ በየቦታውና ባመቸው መንገድ፤ የትግሉን ሂደት እያስረዳ ባደባባይ በግልፅ ትግሉን ያካሂዳል። አንድ ማዕከል፣ አንድ ትግል! አንድ ሕዝብ! አንድ ሀገር! ይህ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጠየቀው። አንድ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ለማቋቋም። ይህ የኢትዮጵያዊያን የነፃነት ንቅናቄ፤ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት እየከፈለ፤ የትግሉ ሂደት ግፊት በሚፈጥረው የሽክርክሪት ዕድገት መሠረት፤ ወደፊት ይገፋል። ስለዚህ ማስተባበሩ፣ መተባበሩ፣ እና መጥራትና መጠራቱ የኛ የያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ግዴታ ነው። ኢትዮጵያዊነታችን አሁን ተጠይቋል። መልስ እንሥጥ! እኔ በeske.meche@yahoo.com እገኛለሁ።
ኢትዮጵያዊያን እንቆጠር! 

No comments:

Post a Comment