Wednesday, April 18, 2018

በዜጎች ላይ የሚደርስ እልቂትና መፈናቀል ይቁም፤ ለዘላቂ መፍትሄ እንታገል!!! (አርበኞች ግንቦት 7 )

ሚያዝያ 9 ቀን 2010 ዓም በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተወረወረ ቦንብ እና በጭፍን በተተኮሱ ጥይቶች ሳቢያ የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ወደ 70 በሚጠጉ ዜጎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳቶች ደርሰዋል። የከተማዋና አካባቢ ነዋሪዎች በሆኑ የቦረናና የገሪ ብሄረሰብ ተወላጆች መካከል የተከሰተ ግጭትን መነሻ በማድረግ ይህንን ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈፀሙት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያስታጠቃቸው ወታደሮች መሆናቸው የከተማው መስተዳደር የሥራ ኃላፊ መግለፃቸው ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።
ሁለት ወራት እንኳን ባልሞላው ጊዜ ውስጥ በዚሁ ከተማ የኮማንድ ፓስት አባላት ነን የሚሉ የአገዛዙ ወታደሮች በዜጎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽመው በርካቶች ሕይወታቸው ሲያልፍ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ጎረቤት አገር ኬኒያ መሰደዳቸው ይታወቃል። ወደ ጎረቤት አገር የተሰደዱ ወገኖቻችን ወደ ቀያቸው አልተመለሱም። ያ ቁስል ሳይሽር ይኸኛው መደገሙ ሁኔታውን እጅግ አሳዛኝ ያደርገዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሊ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥታት በምስራቅና በደቡብ የአገራችን ክፍሎች ለሚፈጠሩ ማኅበራዊ ግጭቶች መፍትሄ በመስጠት ፋንታ የችግሩ አካል እየሆኑ መታየታቸው የዜጎች ሰላም እና የሀገር አንድነት አደጋ ላይ መውደቃቸው አመላካች ነው። በእነዚህ ተከታታይ ግጭቶች ሳቢያ ኢትዮጵያዊያን በከፍተኛ ቁጥር ለሞት፣ ለአካልና ስነልቦና ጉዳቶች እና ለጅምላ መፈናቀል እየዳረጉ በመሆናቸው ችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ የሚሻ ነው።
ይህ የማያባራ የኢትዮጵያዊያን ሰቆቃ የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ውጤት እንደሆነ ንቅናቄዓችን ይገነዘባል።
በሌላ በኩል ደግሞ በጉጂ ዞን በጉጂ እና በጌዲዮ ተወላጆች መካከል የተቀሰቀሰ ግጭት ለበርካታ ዜጎች ህልፈት፤ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀልና ለበርካታ መንደሮች በእሳት መጋየት ምክንያት ሆኗል። ግጭቱ ከዕለት ዕለት አድማሱን እያሰፋ መሆኑ አርበኞች ግንቦት 7ን ያሳስበዋል። እዚህም የኦሮሚያ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥቶች ግጭቶችን ማብረድ አልተቻላቸውም። እዚህም የኮማንድ ፓስት አባላት ግጭቱን ሲያባብሱ እንጂ ሲያረግቡ አልታዩም።
ተመሳሳይ ችግሮች በአማራና በትግራይ እና በትግራይና በአፋር ክልላዊ መንግሥቶች መካከልም ይታያል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፈጠረው የመታፈን ስሜት ግጭቶችን እያሰፋ መሆኑ ዘወትር የሚስተዋል ክስተት እየሆነ ነው። ማኅበራዊ ግጭቶች በተለመደው ባህላዊ መንገድ ብቻ መፈታት የማይችሉ፤ መዋቅራዊ መፍትሄ የሚሹ ሀገራዊ አጀንዳዎች ሆነዋል።
አርበኞች ግንቦት 7 የዜጎች ደህንነት በማናቸውም ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ ያምናል። የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው አካልም ከዚህ የሚያስቀድመው ጉዳይ ሊኖር አይገባም ብሎ ያምናል።
ህወሓት/ኢህአዴግ በህገወጥ መንገድ ለሁለተኛ ግዜ በአገራችን ላይ ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፀጥታን በማስፈን ፈንታ የሕዝብን ሰላም እያደፈረሰ መሆኑ አርበኞች ግንቦት 7 ይገነዘባል፤ የኮማንድ ፓስት አባላት በተለያዩ ስፍራዎች ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት የአገዛዙ እድሜ ለማራዘም የሚያደርጉትን ጥረት አጥብቆ ያወግዛል፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለዚህ መሠረታዊ ችግር ስር ነቀል መዋቅራዊ መላ እንዲሹለትም ይመክራል።
አርበኞች ግንቦት 7 በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ሳቢያ ሕይወታቸው ላጡ ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል፤ በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት ለአካልና ስነልቦናዊ ቀውስ ለተዳረጉ እና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን አጋርነቱን ይገልፃል። በዚህ ወንጀል እጃቸው ያለበት ሁሉ በህግ ፊት እንዲቀርቡና እስከዛሬ በወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ላለው ሰቆቃ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያስታውቃል።
በአገራችን ለሚከሰቱ ማኅበራዊ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት የሚቻለው ስር ነቀል የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ ሲደረግ ብቻ እንደሆነ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። በዚህም ምክንያት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ትኩረቱን የፓለቲካ ሥርዓቱን ለመለወጥ በሚያስችለው ትግል ላይ እንዲያደርግ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!

No comments:

Post a Comment