Saturday, October 7, 2017

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ)

ውድ አድማጮቻችን በዛሬው የአርበኞች ማስታወሻ መሰናዷችን አንድ አርበኛ ታጋይን እንዘክራለን። ይህ አርበኛ ታጋይ ከወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ በኢትዮጲያ የ70ዎቹ ፖለቲካ ውስጥ በንቃት ሲሳተፍ የነበረና በጎልምስና ጊዜውም ቢሆን በሃሳብ፣ በገንዘብና በጉልበት ከወያኔ ጋር የሚደረገውን የነጻነት ትግል ሲያግዝ የነበረ ነው። በተለይም ደግሞ ይህን አርበኛ ልዩ የሚያደርገው በርካታ ኢትዮጲያዊያን እንደ ምድረ ገነት በሚያዩዋት ሃገረ አሜሪካ ሲያትል በተባለ ከተማ ይኖር የነበረና ተደራራቢ የቤተሰብና የስራ ሃላፊነቱን በትጋት ከመወጣት ባሻገር በኢትዮጲያ ህዝብ አርበኞች ግንባር በኋላም በአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ውስጥ በመቀላቀል ትግሉን በተለያየ መንገድ ሲያግዝ የነበረ ጠንካራ ኢትዮጲያዊ ስለነበርም ነው። ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት 7 በሚያደርጋቸው የህዝባዊ እምቢተኝነቶችም ሆኑ ሌሎች ተሳትፎዎች ላይ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ካደረገና ከልጆቹ ጉሮሮ እየቀነሰ ትግሉን በገንዘብም ሲረዳ ከቆየ በኋላ ይህ ሁሉ ጥረቱ ለልቡ ደስታ ለህሊናው እርካታ አልሰጥ ብሎት ዱር ቤቴ ብሎ የአርበኞች ግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይልን ኤርትራ በረሃ ወርዶ ተቀላቀለ። መሬት ላይ ያለውንም ትግል እንደ ማንኛውም አርበኛ ታጋይ የበሉትን በልቼ የጠጡትን ጠትቼ በዱር በገደሉ ከጓዶቼ ጋር ጠላታችንን ወያኔን እንዋጋለን በማለት ወደ በረሃ ቆርጠው ከወረዱ እንደ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ወይንም ገብርዬ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ገበየሁ አባጎራው፣ ኤፍሬም ማዴቦ፣ አበበ ቦጋለ፣ ነአምን ዘለቀ፣ ዕዝራ ዘለቀ፣ ሽባባው ዋዩና ከመሳሰሉት ጥቂት ብርቅዬ የኢትዮጲያ ዳያስፖራዎች ተርታ ስሙ በታሪክ ማህደር ውስጥ ተመዝግቧል። ይህ ሰው ተስፋ ላቀው አስረስ ወይንም በትግል ስሙ አርበኛ ታጋይ ተከዜ ይባላል። 
አርበኛ ታጋይ ተከዜ እጅግ በጣም መልካም ስነምግባር የነበረው፣ በንቅናቄው አመራር አባላትም ሆነ በትግል ጓዶቹ ዘንድ የተወደደና የተከበረ ታጋይ ነበር። በበረሃ ቆይታው ውስጥ በማሰልጠኛ ካምፕም ውስጥ ሆነ ከዚያ ውጪ በሚከናወኑ ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ቀድሞ የሚገኝ፣ ከሚናገረው በላይ የሚሰራ፣ በዕድሜው ከአብዛኛዎቹ ወጣት ታጋዮች የገፋ ቢሆንም አንድም ቀን ቢሆን የድካምና የመሰልቸት ስሜት ሳይታይበት የታገለ ጀግና ነበር። የሚገርም ትህትናን የተላበሰ፣ በታጋዬች መካከል ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች የሽምግልናና የማስታረቅ ሚናን ይጫወት የነበረ፣ የሰራዊቱን የአካልና የስነ ልቦና ደህንነት ለመጠበቅ በጤና መኮንንነት ያገለገለና በተምሮ ማስተማር ሂደት ውስጥ በርካታ አርበኞችን መሰረታዊ የማንበብና የመጻፍ ትምህርትን ይሰጥ የነበረ አርበኛ ብቻ ሳይሆን ወንድምም አባትም የነበረ ትክክለኛ አገር ወዳድና ለኢትዮጵያ ህዝብም አጥብቆ የሚቆረቆር የዳያስፖራው አምባሳደር ነበር።Image may contain: 1 person, outdoor
ለረዥም ጊዜ ከአሜሪካን የሕይወት ልምዱ ያገኘውን በነጻነትና በድፍረት ሃሳብን የመግለጽ ባህል በሚገባ የተላበሰው አርበኛ ታጋይ ተከዜ ይህንን የግልጽነትና የቀጥተኛነት ባህርይ በትግል ሜዳም ሆኖ ሲያስተላልፍ የነበረ የሰራዊቱ ድምጽ ነበር ማለት ይቻላል። የታገለለትና የተሰዋለትም ይህንን የነጻነትና የዲሞክራሲ ባህል በኢትዮጲያ ውስጥ ለመተግበር ንቅናቄአችን ያስቀመጠውን ራዕይ ለማስፈጸም ሲል ነውና ይህንን የሱን ትግል ከዳር የማድረስ ታሪካዊ ሃላፊነት በትከሻችን ላይ ጥሎብን ሄዷል።።
ብላቴን ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን “የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ” በሚለው ትራጄዲው ውስጥ ንጉሱ በምሬት እንዲህ አሉ ይለናል
ምንድነን እኮ ምንድነን?
አመንኩሽ ማለት የማንችል
ፍቅራችን የሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ግፋችን የሚያስከአብረን
እኮ ምንድነን? ይላሉ አጼ ቴዎድሮስ
አርበኛ ታጋይ ተከዜ ግን እንደንጉሰ ነገስቱ ታማኝ ባለሟልና የቀኝ እጅ ገብርዬ ለእናት ሀገሩ ኢትዮጲያ ያለውን ፍቅርና ቀናኢነት አንድም ቀን እንኳ ሳያፍርባትና ሳይደብቅ በአንደበቱም ሆነ በስራው ይገልጥ የነበረ ሰው እንደነበር የምናስታውሰው በሱ ከኛ ድንገት ተለይቶ መሰዋት የፈጠረብንን ክፉኛ የመንፈስ ስብራት እያስታመምን ነው። ምክንያቱም ተከዜን ያጣው ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት 7 ብቻ ሳይሆን ኢትዮጲያና የኢትዮጲያ ህዝብም ነውና። 
ብዙዎች ዘመኑ በፈጠረውና ወያኔ ባባባሰው የዘረኝነት መርዝ ተለክፈው ከኢትዮጲያዊነት ማንነታቸው ኮስሰውና አንሰው እንዳበደ ውሻ እየተቅበዘበዙ የገዛ ወገናቸውን እየነከሱና እየለከፉ ባለበት ባሁኑ ሰዓት አርበኛ ታጋይ ተከዜ አንዲትም ቀን እንኳ የትልቋን ኢትዮጲያ ምስል ከአዕምሮው ሳያጠፋ እስትንፋሱ እስከሚያልፍባት ደቂቃ ድረስ ሀገሬ፣ ሀገሬ እንዳለ የተሰዋ ልዩ ኢትዮጲያዊ ነበር።ይህንንም በሚጽፋቸው ጽሁፎቹ፣ በሚገጥማቸው ግጥሞቹና በሚናገራቸው ንግግሮቹ ሁሉ በግልጽ የሚታዩ ነበሩ። የትግል ጓዶቹም ለዚህ ሕያው ምስክሮች ናቸው።

ጀግና ማለት ሌላ ሳይሆን ሀገር የጀግና ያለህ ስትል ራሱን ለመስዕዋትነት የሚያቀርብ ነው ይላሉ። በመሆኑም እናታችን ኢትዮጲያ የቀን ጅብ ሆኖ እየጋጣት ካለው የወያኔ/ሕወሃት እኹይ ሃይል ራሷን ለማዳን የወንድ ያለህ ባለችበት ሰዓት አለሁልሽ ካሏት ጥቂት ጀግኖች ልጆቿ መካከል ተከዜ አንዱ ነበር። ይህንንም ጀግና እንደሰውም፣ እንደ ድርጅታችን አባልም፣ ብሎም እንደኢትዮጲያዊ በቅርብ ለማወቅ በመቻላችን ደግሞ ኩራታችንና ብራችን ወሰን የለውም።
አርበኛ ታጋይ ተከዜ ከመሰዋቱ በፊት ብዙ ግዴታዎችን ከአጋር የትግል ጓዶቹ ጋር በጽናት የተወጣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጇ ነውና በህይወት ባይኖርም ከልባችን ውስጥ ተቀምጦ ዘላለም በክብር ይኖራል።
እኛም የቀረነው የትግል ጓዶቹ ይህንን ሁሉ መከራና ስቃይ የሚያስከፍለንን የወያኔ/ሕወሃትን ወራዳ ሰው በላ አገዛዝ እስከ መጨረሻው ኣንደምንፋለመው በተሰዋው ወንድማችን ስም ቃል እንገባለን።
ወንድማችን ተስፋ ላቀው አስረስ / ተከዜ / ነብስህን በገነት ያኑርልን። ሁሌም በነፃነት ፈላጊው የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ ነህና አንረሳህም። የጀመርከውን የትግል ዓላማህንም እንደምናሳካልህ ቃል እንገባልሃለን።
ለቤተቦቹም መፅናናትን እንመኛለን።

No comments:

Post a Comment