እድምታው በወያኔ ጎራ
– ለወትሮው ጭቃ በመትፋት የሚታወቀው የወያኔ ሹማምንት እና ካድሬዎች አንደበት የመኮማተር አዝማሚያ ታይቶበታል። በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ኢትዮጵያውያን አፈናው እና ጫናው በዛብን ሲሉ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” በማለት የሚታወቁት ወያኔዎች የጦርነትን አስከፊነት መስበክ ጀምረዋል።
– ኢትዮጵያን እንደ ሃገር፣ የኢትዮጵያን ታሪክ እንደታሪክ እውቅና ለመስጠት እጅግ የሚጠየፉት ወያኔዎች “እምዬ ኢትዮጵያ” ማለት አብዝተዋል።
– ኤርትራን ከእናት ሃገርዋ ኢትዮጵያ ለመገንጠል፣ ኢትዮጵያን ባህር በር አልባ ለማድረግ ከሻብያ ጋር ተቀናጅተው ኢትዮጵያን ሲወጉ የኖሩት ወያኔዎች ኤርትራ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ናት በፍጹም ከኤርትራ ጋር አትነካኩ ሲሉ እየተደመጡ ነው። የወያኔዎቹ ቁንጮ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ከኤርትራ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ሲጠየቅ “ግንኙነታችን እንደ መርፌና ክር ነው” ማለቱን ራዕዩን የወረሱት ወያኔዎች የአርበኞች ግንቦት 7 ምት አስረስቷቸዋል። ሌላኛው የወያኔዎች ቁንጮ ስበሃት ነጋ “ኤርትራ ጥቃት ቢሰነዘርባት ወያኔ ከኤርትራ ጎን ተሰልፎ ይዋጋል” ማለቱን የአርበኞች ግንቦት 7 ጠንካራ ጡጫ አስረስቷቸዋል።
– ቀደም ሲል ከኤርትራ ባለስልጣኖች ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር እንደሚፈልግ ያሳወቀው አሻንጉሊቱ ሃይለማርያም ደሳለኝ አርበኞች ግንቦት 7 ጥቃት በሰነዘረ ማግስት “ኤርትራ አሸግራናለች የኢትዮጵያን ህዝብ አስፈቅደን ጦርነት እንገጥማለን” ብሏል።
– በተለያየ ጊዜ አርበኞች ስለሚፈጽሟቸው ጥቃቶች እውቅና ላለመስጠት ሲል ትንፍሽ የማይለው ወያኔ፣ “አንድ ጊዜ በአካባቢው በመሬት ይገባኛል የተነሳ የነበረ ግጭት ነው” ሲል በሌላ ጊዜ ደግሞ “የሻብያ ተላላኪዎችን ደመሰስኩ” በማለት በተዘዋዋሪም ቢሆን ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር በመፋለም ላይ እንደሚገኙ አምኗል።
የተቃዋሚ ጭንብል በለበሱት ጎራ የአርበኞች ግንቦት 7 ጥቃት የመሰንዘር እድምታ
– ላለፉት በርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች ውጤት ማስመዝገብ ሲጀምሩ ውዥምብር በመንዛት፣ የሃሰት ከፋፋይ ዜናዎችን በማሰራጨትና የትግሉን ግለት ለማቀዝቀዝ ሙከራ በማድረግ የሚታወቁ ግለሰቦች የአርበኞች ግቦት 7ን ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘር ተከትሎ ባልተቀናጀ መልኩ አደባባይ እየወጡና እራሳቸውን እያጋለጡ ይገኛሉ።
– ኤልያስ ክፍሌ (የኢትዮጵያን ሪቪው ድረገጽ አዘጋጅ) አንዱ ነው። ኤልያስ ክፍሌ ወያኔን እየተፋለሙ ባሉ አርበኞች ላይ በርካታ የሃሰት ዘገባዎችን በማሰራጨት የሚታወቅ ቢሆንም ሰሞኑን አርበኞች ግንቦት 7 በወያኔ ላይ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ የሚናገራቸው ነገሮች “ይህ ሰው አበደ?” የሚያስብሉ ናቸው። ከብዙ እጅ እግር ከሌላቸው ጸረ አርበኞች ግንቦት 7ና ጸረ ኢሳት ቴሌቪዥን ንግግሮቹ ለመጥቀስ ያህል “የኤርትራ መንግስት ከኳታር እና ከሳውዲ አረቢያ በእርዳታ ከሚያገኘው ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ውስጥ ግማሹን ለአርበኞች ግንቦት 7 እና ለኢሳት ይሰጣል” በማለት ተላብሶ የኖረውን የተቃዋሚ ጭምብል ገፎ ወጥቷል።
– ሌላኛው የአርበኞች ግንቦት 7 በወያኔ ላይ ጥቃት መሰንዘር ሽብር የለቀቀበትና የተቃዋሚ ጭምብል አጥልቆ የኖረው የቀድሞ ተወዛዋዥና የአሁኑ ጋዜጠኛ አበበ በለው ይባላል። በሰሜን የአርበኞች እንቅስቃሴ እያየለ ሲመጣ ነው አበበ በለው መተራመስ የጀመረው። የኢሳት ጋዜጠኞች ወደ ኤርትራ ተጉዘው የአርበኞቹን እንቅስቃሴ በስፋት እየዘገቡ በነበረበት ወቅት ሁኔታው ያላስደሰተው አበበ በለው ከረጂም አመታት በፊት በምግባረ ብልሹነት ከአርበኞች ግንባር የተወገዱ ግለሰቦችን በማፈላለግ የቻለውን ያህል በትግል ሜዳ እየተዋደቁ በሚገኙ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ላይ ጭቃ ሲለጥፍ ሰንብቷል። አበበ በለው ይባስ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ እራሱን ባደባባይ ማጋለጥ የጀመረው ግን አርበኞች ግንቦት 7 በወያኔ ላይ ጥቃት መክፈቱን ይፋ ባደረገ ሰሞን ነው። አበበ በለው እንዲህ አለ “ወያኔ እና ሻብያ በፍጹም አልተጣሉም… ለማረጋገጫም ወያኔ በየዓመቱ ለኤርትራ መንግስት 250 ሚሊዮን ዶላር በስጦታ መልክ ያበረክታል” አበበ በለው ይህንን ከተናገረ በኋላ በቃለ-ምልልሱ ወቅት የተቀዳው ድምጽ ድረገጾች ላይ ሲለጠፍ “ወያኔ በየዓመቱ ለኤርትራ መንግስት 250 ሚሊዮን ዶላር በስጦታ መልክ ያበረክታል” የምትለው ሃረግ ተቆርጣ እንድትወጣ ተደርጋለች።
የአርበኞች ግንቦት 7 ማጥቃት በሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጎራ የፈጠረው እድምታ
– በተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብዙ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሰብስበው ለአርበኞች ግንቦት 7 ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ አበርክተዋል።
– በሃገር ቤትም ሆነ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አርበኞቹን በርቱልን ከጎናችሁ ነን እያሉ ነው።
– አርበኞች ግንቦት 7 በወያኔ ላይ ጥቃት መሰንዘር በጀመረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአርበኛውን ጎራ በስፋት በመቀላቀል ላይ እንደሚገኙ አርበኞቹ እየገለጹ ነው።
– የማህበራዊ ድረገጾችን የሚጠቀሙ ለውጥ አራማጅ ኢትዮጵያውያን እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ ዜናዎችንና መልዕክቶችን በማሰራጨት በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥረዋል፣ የመረጃ ክፍተት እንዳይኖርም የላቀ አስተዋጸኦ በማበርከት ላይ ናቸው።
No comments:
Post a Comment