Tuesday, July 14, 2015

የወያኔ እና የሃኪንግ ቲም ከፍተኛ ኪሳራ

uly 14, 2015
እራሱን “መንግስት” እያለ የሚጠራው የወያኔ ዘረኛና አምባገነን ቡድን ሃኪንግ ቲም (Hacking Team) ለሚባለውና አምባገነን መንግስታት ዜጎቻቸውን እንዲሰልሉ የሚያስችላቸውን የኮምፒዩተር ስለላ ቴክኖሎጂ እና ስልጠና በመስጠት ለሚታወቀው ኩባንያ ከአንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ (ሃያ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር አካባቢ) የከፈለበት ደረሰኝ ይፋ ሆኗል።
Hacking Team and the Ethiopian dictators
ከዚህ ቀደም ሲቲዝንላብ (CitizenLab) እና አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት (Human Rights Watch) ሃኪንግ ቲም (Hacking Team) ለኢትዮጵያ መንግስት የኢሳት ጋዜጠኞችን ለመሰለል የሚያስችለውን የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂዎች እንደሚያቀርብ ካጋለጡ በኋላ በኩባንያው ላይ አለም ዓቀፍ ጫናዎች በርትተውበት እንደነበር ይታወሳል።
ኩባንያው እንደ ኢትዮጵያ
ላሉ በዜጎቻቸው ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለሚፈጽሙ አምባገነን መንግስታት የኮምፒዩተር ስለላ ቴክኖሎጂዎችን ያቀርብ እንደሆነ ሲጠየቅ “የደንበኞቼን ማንነት ያለማሳወቅ ህጋዊ መብት አለኝ” በማለት ጉዳዩን ሲያደፋፍን ቆይቷል።
ሰሞኑን ታድያ “ለጌታም ጌታ አለው” እንደሚባለው ሆነና ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች የሃኪንግ ቲምን (Hacking Team) ዳታ ማከማቻ ማዕከል ሰብረው በይዘቱ 400GB የሆነ ዳታ መዝብረዋል።
የተመዘበሩት ዳታዎች የኩባንያውን ጥብቅ ሚስጥር፣ የደንበኞቻቸውን ዝርዝር እና ከደንበኞቻቸው ጋር የተለዋወጡዋቸውን የኢሜል መልዕክቶች የያዙ ናቸው።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃኪንግ ቲምን ያመሰገኑበት የኢሜል መልዕክት፣ ቢንያም ተወልደ የተባለው የወያኔ ሰላይ ከኩባንያው ሰዎች ጋር የተለዋወጣቸው በርካታ የኢሜል መልዕክቶች፣ የወያኔ ቡድን ህዝብ በድህነት በሚሰቃይባት ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ለስለላ ተግባሩ የከፈለበት ደረሰኝ እና የመሳሰሉት በሌላ መንገድ ሊገኙ የማይችሉ መረጃዎች አደባባይ መውጣት ጀምረዋል።
ይፋ ከወጡት መዝገቦች መረዳት እንደሚቻለው ወያኔ ይህንን ሁሉ የሃገር ሃብት ዜጎቹን ለመሰለል አባክኖ ሲያበቃ በምላሹ ያገኘው ውጤት እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ነው። ወያኔ ለስለላ ተግባሩ ያሰማራቸው ግለሰቦች ከአንድ ጎሳ ብቻ የወጡ መሆናቸውንም ከሰነዶቹ መረዳት ይቻላል። እውቀት ሳይሆን ዘርን ቅድሚያ ሰጥቶ ሰላዮችን የሚመለምለው ወያኔ የስለላ ቴክኖሎጂዎቹን መጠቀም አቅቶት ሲዳክርም ይስተዋላል።
ቢንያም ተወልደ የሚባለውና ወያኔዎቹን ወክሎ ከሃኪንግ ቲም ኩባንያ ጋር ድርድሮችን ያካሂድ የነበረው ግለሰብ የስለላ ቴክኖሎጂዎቹ የተሰላዮቹን ኢትዮጵያውያን የኮምፒዩተር ቫይረስ መከላከያዎች ማለፍ አቅቷቸው የሃኪንግ ቲም ኩባንያን ሲሳደብና ኮንትራቱን ለማቋረጥ ዛቻ ሲሰነዝር እንደከረመ ከሰነዶቹ መረዳት ይቻላል። ግለሰቡ ከስለላ ኩባንያው ጋር ያደረጋቸው የኢሜል ልውውጦች አብዛኛዎቹ አሳፋሪ ናቸው (ቢንያም ተወልደ እውቀት ብቻ ሳይሆን እንደ አብዛኛዎቹ የወያኔ ሹማምንትና ካድሬዎች ስነ-ምግባርም ይጎድለዋል)። ኋላ ላይ በወያኔዎቹ ሰላዮች ዘንድ ከፍተኛ የእውቀት ማነስ እንዳለ የተረዳው የስለላ ኩባንያ በነጻ ስልጠና ለመስጠት ሃሳብ ባቀረበው መሰረት የተመረጡ የስርዓቱ ታማኞች (ከስማቸው መረዳት እንደሚቻለው ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ናቸው) ወደ ጣልያን ሃገር ተልከው ገረፍ ገረፍ የሶስት ቀን ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። በአጠቃላይ ከተለዋወጡት የኢሜል መልዕክቶች መረዳት እንደሚቻለው ባብዛኛው በስለላ ኩባንያው እና በወያኔ ሰላዮች መካከል ከመደናቆር ያለፈ ውጤታማ የስለላ ተግባር አልነበረም።
የሃኪንግ ቲም ዳታዎች ሲዘረፉ የስለላ ቴክኖሎጂ ፕሮግራሞቻቸውም አብረው በመዘረፋቸው ምክንያት ቀደም ሲል ሃኪንግ ቲም ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች አምባገነን መንግስታት የሸጣቸው የስለላ ቴክኖሎጂ ፕሮግራሞች ባብዛኛው ጥቅም አልባ ሆነዋል። ማይክሮሶፍት እና አዶቤ የተባሉት ዋነኛ የኮምፒዩተር ፕሮግራም አቅራቢዎች ሃኪንግ ም በምን አይነት መንገድ ኮምፒውተሮችን ይደፍር እንደነበር በመረዳታቸው ስሞኑን ፕሮግራሞቻቸው ላይ ጥገና ሲያካሂዱ ከርመዋል። (በዚህ አጋጣሚ በኮምፒዩተሮ ላይ የአዶቤ ፍላሽ ፕሌየር ‘Adobe Flash Player’ ተጭኖ የሚገኝ ከሆነ አሁኑኑ በአዲስ መልክ በተጠገነው ፕሮግራም ይቀይሩት) ፕሮግራሙን እዚህ ያገኙታል
ይህ በዚህ እንዳለ ወያኔ ከስለላ ኩባንያዎቹ ጋር በመተባበር የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በህገወጥ መንገድ ኮምፒዩተሮቻቸውን እና ስልኮቻቸውን በመበርበር ወንጀል ተከሶ ጉዳዩ በአሜሪካን ሃገር በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በፍርድ ቤት መታየት ጀምሯል
ዊኪሊክስ አደራጅቶ የለቀቀውን በወያኔ ሰላዮች እና በሃኪንግ ቲም ኩባንያ መካከል የተደረጉትን የኢሜል መልዕክት ልውውጦች፣ የኩባንያው ሰዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ እርስ በእርስ የተወያዩትን እና ሌሎችንም ሰነዶች ለመመልከት እዚህ ይጫኑ
ይህንን ጽሁፍ በሌላ ቦታ ማተም የተፈቀደ ነው፣ ታድያ የዌብሳይታችንን ስምና አስፈንጣሪንም አብረው ማኖር እንዳይረሱ። (ECADF Ethiopian News)

No comments:

Post a Comment