Wednesday, July 1, 2015

አለም አቀፍ ድጋፍ የተቸረው “ልማታዊ” አንባገነናዊነት በኢትዮጵያ

አለም አቀፍ ድጋፍ የተቸረው “ልማታዊ” አንባገነናዊነት በኢትዮጵያ

“የአፍሪቃ ድሃ ባይጠግብም እንኳ ቀምሶ ካደረ ይበቃዋል” አይነት ንቀት የተሞላው የምዕራቡ አለም ምልከታ ከመቼውም ጊዜ በከፋ መልኩ አፍጦና አግጦ እየታየ ነው፡፡ በርሃባችንና በእርስ በእርስ መናቆራችን ለዘመናት ሲነግዱበትም ሲማረሩበትም ቆይተዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ የመጫወቻው ካርድ ተቀይሮ ለአፍሪቃ አንባገነኖች አንድ ቃል ተለጥፎላቸው ካሳላፍነው ታሪክ ምናልባትም በከፋ መልኩ ጉዟችንን ቀጥለናል፤ የኋሊት ይሁን ወደፊት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን የምዕራቡ አለም “ልማታዊ” በሚል ካባ የተከናነበውን የለየለት አንባገነናዊነት ሙሉ ድጋፋቸውን እየሰጡ ለመሆኑ የኦባማን የኢትዮጵያ ጉዞ ጨምሮ በርካታ ምልክቶችን እያየን ነው፡፡ ከምርጫው በፊትም ሆነ ከተጠናቀቀ በኋላ የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካን መንግስት ያሳዩትም ድጋፍ የእዚሁ መገለጫ ነው፡፡
በአፋኝ አገዛዝ ውስጥ ላለ ሕዝብ ዲሞክራሲን፣ ሰብአዊ መብቶችን፣ ፍትሕን እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ድጋፍ ለተራበ ሕዝብ ስንዴና ዘይትን እንደመርዳት ቀላል አይደለም፡፡ እህል ተርፏቸው ወደ ባሕር የሚጨምሩ አገሮች የተራበ ሲያገኙ የተረፋቸውን መወርወራቸው አንድም እርዳታ በመስጠትና ለጋሽ በመሆን የሚገኝው የመንፈስ እርካታና በዋነኝነት ደግሞ የተጠኑ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትርፎችም አሉት፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ላለፉት አስርት አመታት በርካታ የአፍሪቃ አገራት፤ የኛዋ አገር ደግሞ በግናባር ቀደምነትነት የዚህ የእህልና የገንዘብ ድጎማ ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች፡፡ በዚህ የቁስ እርዳታ ማን እንዳተረፈ በጥልቅ መመርመር የግድ ይላል፡፡ በእርግጠኝነት ግን መናገር የሚቻለው አገርንና ሕዝብን ለውርደት የዳረገና ክፉ የታሪክ ጠባሳም መሆኑን ነው፡፡ ዘንድሮ ስንዴና ዘይት የሚላክለት ድሃ ሕዝብ ያለችውን ቅሪት እየሸጠ በርሃና ባሕር አቋርጦ በራሱ ጥረት “ምና አደከማችሁ እኔ እዛው እምጣለሁ” ብሎ ለጋሾቹ ደጃፍ ደርሷል፡፡ ለዚህም በየአመቱ ከኢትዮጰያ፣ ከኤርትራ፣ ከሱዳን እና ከሱማሌ የሚሰደደው ሕዝብ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የምዕራቡ አለም እርዳታውን በመርከብ ከማጓጓዝ ሳይድን አልቀረም፡፡ ስንዴ የሚጭኑ መርከቦች ሽብርን ለመዋጋት በሚል ሽፋን የጦር መሳሪያ በማጓጓዝ ስራ የተጠመዱ ይመስለኛል፡፡
ዛሬ ላይ የቻይና ቢዝነስ ተኮር ወረራ ያስደነበራቸው የምዕራቡ አለም አገራት የአፍሪቃን አንባገነኖች ከነ ወንጀሎቻቸውና ስንክሳራቸው ተቀበለው አብረው ለመዝለቅ የተገደዱበትና መለማመጥ የጀመሩበት ሁኔታ ነው የሚታየው፡፡ “ልማት” እና “ደህንነት” (security) ብቸኛዎቹ የምዕራቡና የአፍሪቃ አንባገነኖች የመወያያና የመደራደሪያ አጀንዳዎች ሆነዋል፡፡ ሰብአዊ መብቶች፣ ዲሞክራሲንና የሕግ የበላይነትን በዋነኝነት ያነሱ የነበሩት አውሮፓዊያን ሳይቀሩ እነዚህን አጀንዳዎች ወደጎን የገፉዋቸው መሆኑን በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ የ2007 ምርጫ ዙሪያ ያሳዩት የዳር ተመልካችነት ሚና እና ከምርጫውም በኋላ የሰጡዋቸው መግለጫዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት ሁሉን ነገር ወደ ጎን ተትው “ሰላም” በሚለው አጀንዳ ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ከ”ልማታዊው” አንባገነናዊ ሥርዓት ጋር ያላቸውን ጥብቁ ቁርኝት አድሰው እንደሚቀጥሉ በግልጽ የሚያሳየውን የአጋርነት መግለጫቸውን አንብበናል፡፡
በአገዛዝ ሥርዓቱና በአለም አቀፉ ማኅበረሰብ መካከል፤ የአፍሪቃ ኅብረቱንም ጨምሮ በኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ቀደም ብሎ የተደረሰበት አንድ አይነት ስምምነት እንዳለ የሚያሳየው የምርጫ ቦርድና ገዢውን ቡድን ጨምሮ ሁሉም መፈክራቸው “ምርጫዉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተጠናቋል” የሚል ነበር:: ይህ መሪ መፈክር ተደጋግሞ በሁሉም ሚዲያዎችም እነቪኦኤን ጨምሮ እስክንደነቁር ድረስ ሲነገርን ቆይቷል፡፡ ይህ ሆን ተብሎ ቅድመ ሥራ የተሰራበት ነገር ስለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም፡፡ አንደኛ ሰላም ባለበት አገር ልክ ምርጫውን ተከትሎ አንዳች የመተላለቅ ዳመና እንዳንጃበበ ተደርጎ የተሰራው ዘገባ ሁሉ ሕዝቡ ስጋት ውስጥ እንዲገባና እንዲሸበር አድርጎታል፡፡ ይህ ተንኮል ያልገባውና ቀላል ግምት የማይሰጠው ሕዝብም ሊመጣ ይችላል ከተባለው አደጋ እንኳን ወያኔ አንዳች ኃይል ያለው ሰይጣንም ቢያስጥለው አይጠላም፡፡ ይህም ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነገር ነው፡፡ የሌለን ነገር እንዳለ አድርጎ ፈጥሮ ሕዝብን ማስጨነቅና ማስሸበር የተፈለገበት ዋነኛ አላማም የገዢውን ኃይል ብቸኛ የሰላም አስከባሪ አካል አድርጎ ሕዝብ እንዲያየውና ወያኔ ከሌለ ያልቅልናል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ እንዲፈጠር አድርጓል:: ይህ ደግሞ ከአመታት በፊት ቀድሞ የተወሰነና የምዕራቡንም አለም ቅቡልነት ያገኘውን የገዢውን ቡድን በስልጣን የመቆየት እቅድና ሕዝብ ባይዋጥለትም ሳያንገራግር እንዲቀበል ለማደረግ ቀላሉና ብቸኛው መንገድ ነበር፡፡ ስለሆነም “ነጻና ፍትሐዊነት” በምንም መልኩ የዚህ ምርጫ መሪ መፈክር አልነበሩም፡፡ ወያኔም ይህን ለማሟላት ዝግጁ አይደለም፡፡ ስለዚህ ምርጫውን ተከትሎ አንዳች የመተላለቅ አደጋ እንዳንጃበበ አድርጎ የማቅረቡ ፋይዳ ለወያኔም ሆነ ለምዕራቡ አለም ብቸኛው የማደናገሪያ ካርድና የመውጫ ቀዳዳ ነበር፡፡
ድምጽ በሚሰጥበት ዕለት እንኳን በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ ዕጩዎችና ደጋፊዎቻቸው ሲጉላሉ፣ ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩና አልፎም በአንዳንድ ቦታዎች ሲገደሉ የበርካታ ሚዲያዎች፣ የአፍሪቃ ሕብረት ታዛቢዎችና አለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ አንድ አይነት ነጠላ ዜማ ነበር የሚያዜሙት፤ “የምርጫው ሂደት ሰላማዊ ነው፡፡ … በሰላምም ተጠናቋል፣ ወዘተ…”፡፡ ይህ ከላይ እንዳልኩት አንድም የአገዛዝ ሥርአቱን ብቃትና ጥንካሬ ለማጉላት ያለው ብቸኛ መንገድ ስለሆነ በሌላ መልኩም ቀድሞ የተዶለተበትንና አለም አቀፍ ቅቡልነት ያገኘውን በምርጫ ስም የአንባገነን ሥርዓቱን የአገዛዝ ዘመን የማደስ ስልት ለመሸፈን የተደረገ የትብብር ዘመቻ ነው፡፡
ምርጫ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሚረጋገጡባቸው መንገዶቹ አንዱ ነው፡፡ ልማት ደግሞ የአንድ አገር ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መበቶች በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጡ የሚያስችል ሌላው መንገድ ነው፡፡ ልማትና ዲሞክራሲ ተጣጥመው በሚሄዱበት ስፍራ ሁሉ ማህበራዊ ፍትሕም ይሰፍናል፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምም ይኖራል፡፡ ለዚህም ነው በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ውስጥ በሁለት ማዕቀፍ የተቀመጡት መብትና ነጻነቶች፤ የሲቪልና የፖለቲካ እንዲሁም የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባሕላዊ መበቶች ሳይነጣጠሉ መተርጎምና መከብር እንዳለባቸው የተደነገገው:: ይሁንና ለድሃ አገራት ስንዴና ዘይት እየረዳ ስለ ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች መከበር ካንገት በላይም ቢሆን ይሟገት የነበረው የምዕራቡ አለም ‘ድሃ በል’ በሆነው የገበያ መርህና በግሎባላይዜሽን ስም የዝርፊያ ጋሪውን አስቀድሞ ዜማውን በመቀየር ከ”ልማታዊ” አንባገነኖች ጋር ተስማምቶ የእጃዙር ቅኝ ግዛት መረቡን አፍሪቃ ላይ ጥሏል፡፡ እኛንም ከገዢዎቻችሁ የተራረፈውን ቀምሳችሁ ማደር ከቻላችሁ ዲሞክራሲንና ሰብአዊ መብቶችን ቀስ ብላችሁ በመቶ አመት ሂደት ትቀዳጃላችሁና ተረጋጉ እያሉን ነው፡፡ ለጊዜው አለማችን እኛው በፈጠርናቸው ሽብርተኞች ተወጥራለችና እጃቸው ከመውደቋ በፊት እነሱን ለማጥፋት እንተባበር እያሉን ነው፡፡ እንግዲህ የሚበጀንን እንምረጥ::
በቸር እንሰንብት!
ከያሬድ ኃይለማርያም
ሰኔ 16፣ 2007 ዓ.ም. ከብራስልስ
yhailema@gmail.com


No comments:

Post a Comment