በኦሮሚያና በአማራ ክልል የሚደረጉ ተቃውሞዎችን ተከትሎ ይህን ተቃውሞዎች ይደግፋሉ የሚባሉ የኦህዴድና የብአዴን ባለስልጣናትን ከሃላፊነታቸው የማንሳትና የተወሰኑትን ደግሞ ወደ እስር ቤት ለማስገባት የሚያስችል ስራዎች በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት በከፍተኛ ሚስጥር እየተከናወነ እንደሆነ ከደህንነት የተገኘ መረጃ ያመለክታል። የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ለህወሃት ታማኝ አይደሉም ተብለው የሚጠረጠሩ በብአዴን እና በኦህዴድ ውስጥ ከመካከለኛ አመራር ጀምሮ ያሉ ግለሰቦች ስማቸው በዝርዝር ተቀምጦ በስውር ክትትል እየተደረገባቸው ይገኛል። በነዚህ የብአዴን እና የኦህዴድ ባለስልጣናትን ላይ በአሁን ሰአት እርምጃዎች የሚወሰዱ ከሆነ ሃገሪቱ ውስጥ ከተፈጠረው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ ለሌላ ውስብስብ ችግሮች ልንጋለጥ እንችላለን በማለት እንደየሁኔታው ለወደፊቱ በተጠረጠሩ የብአዴን እና የኦህዴድ ባለስልጣናት ላይ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የደህንንነቱ መስሪያ ቤት ውሳኔ አሳልፏል። ብአዴን እና ኦህዴድ፤ የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ሽብርተኛ ብሎ በሚጠራቸው ቡድኖች በተለይ የአርበኞች ግንቦት 7 እና ኦነግ መጠቀሚያ ሆነዋል የሚል የትንተና ሪፖርት በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ቀርቧል። በዚህም ምክንያት ብአዴን እና ኦህዴድ እራሳቸውን ማጽዳት ይኖርባቸዋል በሚል በብአዴን እና በኦህዴድ ውስጥ ያሉ ከመካከለኛ አመራሮች ጀምሮ ያሉ ባለስልጣናትን ያካተተ ስም ዝርዝር በቀጣይ ለሚወሰድ እርምጃ ተዘጋጅቶ መቀመጡን ከደህንነት የተገኘው መረጃ ያስረዳል። የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ የሚነሱ ተቃውሞዎች የብአዴን እና ኦህዴድ እጅ አለበት ሲል ይከሳል። በደህንነቱ መስሪያ ቤት የሚቀርቡ ሪፖርቶችም የሚያስረዱት በብአዴን እና ኦህዴድ ውስጥ ያሉ አመራሮች ከተቋውሞ ጋር በተያያዘ እጃቸው እንዳለበት ነው። በተቃራኒው በብአዴን እና በኦህዴድ ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት፤ የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ወኪሎቹን በመጠቀም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የእርስ በርስ ግጭቶች እንዲነሱ ይሰራል ሲሉ ይከሳሉ። የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት በክልሎቹ የስልጣን ጠገግ ውስጥ እንደፈለገ በመግባት ከህግ ውጪ ያሻውን እየፈጸመ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት ክልሎቹ የደህንነት መስሪያ ቤቱን ፍላጎት ማሟላት ሳይችሉ ሲቀሩ ደህንነቱ እርምጃዎችን እንደሚወሰድባቸውና የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት እራሱን የቻለ ስውር መንግስት እንደሆነ ይገልጻሉ። የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት የክልሎችን የጸጥታ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር የሚያችለውን አሰራር ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment