Sunday, December 17, 2017

አንድ ሬጂመንት የአጋዚ ኮማንዶ ሰራዊት ወደ ፌደራል ፖሊስ ተዛወረ *የጸጥታ ኃይሎች ዜና (ታህሳስ 7, 2010 ዓ.ም)

በጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ፌደራል ፖሊስን ለማጠናከር በሚል በአጋዚና ልዩ ሃይሎች ጠቅላይ መምሪያ ስር ከሚገኘው የአጋዚ ኮማንዶ አንድ ሬጂመንት ሰራዊት ወደ ፌደራል ፖሊስ እንዲዛወር ተደርጓል።Image may contain: one or more people and outdoor በሃገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሚፈጠሩ ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ በፌደራል ፖሊስ የአቅም ውሱንነት ተፈጥሯል። ይህን ምክንያት በማድረግ ነው በመከላከያ ውስጥ የሚገኝን ሰራዊት ወደ ፌደራል ፖሊስ እንዲዛወር የደህንነቱ መስሪያ ቤት የጠየቀው። የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት 5 ሬጂመንት ሰራዊት ከመከላከያ ወደ ፌደራል ፖሊስ እንዲዛወር ጥያቄ ቢያቀርብም በጄነራል ሳሞራ የሚመራው መከላከያ ወደ ፌደራል ፖሊስ የሚዛወረው አንድ ሬጂመንት የአጋዚ ኮማንዶ ሰራዊት ብቻ እንዲሆን ፈቅዷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወደ ፌደራል ፖሊስ የሚገቡ አዲስ ተመልማዮች ከመቼው ጊዜ በላይ ቁጥሩ ማሽቆልቆሉ ነባር የሰራዊት አባላትን ወደ ፌደራል ፖሊስ እንዲያዛውሩ ተገደዋል። ወደ ፌደራል ፖሊስ የሚዛወሩ የአጋዚ ኮማንዶ የሰራዊት አባላት በአሁን ሰአት ሃዋሳ ቶጋ በሚገኘው የአጋዚ ኮማንዶና ልዩ ሃይሎች ጠቅላይ መምሪያ ካምፕ ውስጥ ልዩ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ። በስልጠናው ከነፍስ ከወፍ እስከ RPG ያሉ መሳሪያዎች በመጠቀም የተኩስ ልምምድ እየተደረገ እንደሚገኝ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በተጨማሪም ህዝባዊ አመጾችን እንዴት መበተን እንደሚቻል የሚያሳይና የከተማ የጸረ ሽምቅ ውጊያ ቴክኒኮችንም ያካተተ ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የአጋዚ ኮማንዶ ሰራዊት በዚህ ያህል ቁጥር ቀጥታ ወደ ፌደራል ፖሊስ እንዲዛወር ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ መረጃውን ያስተላለፉት ወኪሎቻችን ይገልጻሉ። ፌደራል ፖሊስ በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ቀጥታ ቁጥጥር ስር ያለ እንደመሆኑ አቶ ጌታቸው አሰፋ ከመከላከያ የሚመጣበትን ማንኛውውም አደጋ ቀድሞ ለመከላከል እንዲያስችለው እየሰራ እንደሆነ ይታመናል። ፌደራል ፖሊስ ከህግ አግባብ ውጪ የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ተዋጊ ሃይል ሆኖ መወሰዱ በመከላከያ ውስጥ ቅሬታን የፈጠረ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል። የፌደራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኮሚሽነር አሰፋ አቢዩ ወደዚህ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት ለረጅም ጊዜ በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ ሲሰራ እንደነበረ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment