የወያኔው ጦር በጨለንቆ በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ ባደረሰው የጅምላ ጭፍጨፋና እንዲሁም በምዕራብ ሃረርጌ ሃዊ ጉዲና እና ዳሮ ወረዳዎች ውስጥ በኢትዮጵያ ሶማሊ ወገኖች ላይ በደረሰው እልቂት ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት7 የተሰማውን ከፍተኛ ሃዘን ለመግለጽ ይወዳል። ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ህይወት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠውና ለዜጎች የህይወት ዋስትናና ነጻነት እውን መሆን ሌት ተቀን የሚታገለው ድርጅታችን፣ እንዲህ አይነት የጅምላ ጭፍጨፋ መርዶዎችን ሰምቶ በዝምታ ለማለፍ የሚያስችለው ትዕግስት የለውም።
የአለም ህዝብ አገራችንን በድህነቷ ይወቃት እንጅ፣ ድህነት ያልበታተነው የህዝብ አንድነትና ፍቅር ያላት አገር መሆኗንም ጠንቅቆ ያውቃል። ይህ በዘመናት የተገነባው ፍቅርና አንድነት የውዷ አገራችን ልዩ መለያ እሴቷ ነው። ይሁን እንጅ ይህ እንቁ እሴት ካለፉት 26 ዓመታት ወዲህ፣ በተለይም ደግሞ በቅርቡ እየተራከሰና ዋጋ እያጣ በመምጣቱ በአገራችን ህልውና፣ በህዝባችን ሰላምና ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ይዞ መጥቷል። ይህ የአንድነትና የፍቅር ማተባችን እየተበጠሰ ያለው በማንኛውም የውጭ ሃይል ወይም በየትኛውም ድርጅት ሳይሆን፣ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ በሚገኘው የወያኔ ቡድን መሆኑ ስጋታችንን አባብሶታል። በየትኛውም አገር የመንግስት ታሪክ የመንግስት የመጨረሻውና ቀላሉ ስራ የዜጎችን ደህንነትና ህልውና ማስጠበቅ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ለዘመናት የተገነባ ፍቅርና አንድነት ባለባቸው አገሮች የሚገዙ መንግስታት፣ የዜጎቻቸውን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ ካለባቸው ሃላፊነቶች ሁሉ እጅግ ቀላሉ መሆኑን ከታሪክ መማር ይቻላል። ዜጎች ለዘመናት የገነቡትን ፍቅርና አንድነት ከትውልድ ትውልድ እያሸጋገሩ ህልውናቸውንና ደህንነታቸውን አስጠብቀው እንዲጓዙ፣ ፍትሃዊ አስተዳደር መመስረት ግድ ነው። እንደ ጣሊያን የመሳሰሉ የውጭ ወራሪዎች አገራችንን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ያልቻሉት ይህን ዘመን የማይሽረውን የአንድነትና የፍቅር ማተብ ለመበጠስ ባለመቻላቸው መሆኑ የሚታወቅ ነው። ወያኔ ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ይነሳብኛል በሚል ፍርሃት፣ ህዝባችንን እርስ በርስ በማጋጨት በየቦታው የዜጎች እልቂት እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑ ፣ በአለም የመንግስታት ታሪክ ልዩ ያደርገዋል። ይህ ህዝብን እርስ በርስ እያጨፋጨፉ ለመግዛት የሚደረግ ሙከራ፣ ዛሬ ሆድን ሞልቶ ለማደር የጠቀመ ቢመስልም፣ የሁዋላ ሁዋላ ግን “መሬት ተከፍታ በዋጠችኝ” የሚያስብል አደጋ በገዢዎች ላይ ይዞ መምጣቱ የማይቀር መሆኑን ከሊቢያው መሪ ጋዳፊ እና ከየመኑ አህመድ ሳላህ የቅርብ ጊዜ ታሪክ መማር ይቻላል።
በሃዊ ጉዲናና ዳሮ ወረዳዎችም ይሁን በጨለንቆ፣ ከዚያ በፊትም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተካሄዱ እና አሁንም በመካሄድ ላይ ያሉ ጭፍጨፋዎችና ግጭቶች በህዝብ መካከል የሚካሄዱ ሳይሆኑ ወያኔ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ሲል የሚለኩሳቸውና የሚያራግባቸው መሆኑን ህዝባችን የሚያውቀው ሃቅ ቢሆንም፣ ዛሬም ይህን ሃቅ ልናስታውስ እንወዳለን። ወያኔ በስልጣን ላይ እንዲቀጥል እስከፈቀድንለት ድረስ በዘመናት የተገነባው የፍቅርና የአንድነት ማተባችን ተበጣጥሶ አሁን ከሚታዬውም በላይ እጅግ አስከፊ ወደሆነ የእርስ በርስ ጦርነት እንደሚከተን የታወቀ ነው። ስለዚህ ይህን የአገር ጠላት ከስር መሰረቱ ነቅሎ በመጣል የአንድነታችንንና የፍቅር ማተባችንን መልሶ በማሰር የዜጎቻችንን ህልውና እና ደህንነት ማስጠበቅ ከእያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ የሚጠበቅ ነው። ወያኔ እያንዳንዷን ቀን በስልጣን ላይ በቆዬ ቁጥር በህዝባችን ላይ የሚደርሰው አደጋም በተመሳሳይ መንገድ እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ ዳር ቆመን የምንመለከትብት ጊዜ እንዳበቃ ማወቅ አለብን።
አርበኞች ግንቦት7 ወያኔ በህዝባችን ላይ ያደረሰውን እልቂት ሲያወግዝ፣ የእልቂቶች ሁሉ ምንጭ የሆነውን የወያኔ አገዛዝ እንድናስወገድ የተለመደ ጥሪውን በማቅረብ ነው።
ድል ለኢዮጵያ ሕዝብ!!!
አርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ለዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ
No comments:
Post a Comment