June 18, 2015
ኢትዮጵያ አንድ ተጨማሪ ወጣት ልጇን አጣች። ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓም ማታ የደብረ ማርቆሱ የሰማያዊ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ወጣት ሳሙኤል አወቀ ኢሰብዓዊ በሆነ ድብደባ ሕይወቱ አልፏል። ይህ ወጣት በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ በጽናት ታግሏል። ለኢትዮጵያ ይበጃል ብሎ ባመነበት መንገድ ተጉዞ ለትግሉ ሕይወቱን ሰጥቷል። ሳሙኤል በሕይወቱ ላይ ያንዣበበውን አደጋ በትክክል ያውቅ ነበር፤ ለህልፈት የዳረገው አደጋ በመድረሱ በፊት ተደጋጋሚ ጥቃቶች ደርሰውበታል፤ ሆኖም ግን ግንባሩን አላጠፈም። በሕይወቱ ላይ ያንዣንበበውን አደጋ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ በመገመቱ “ከታሠሩኩም ህሊናዬ አይታሰርም፤ ከገደሉኝም ትግሌን አደራ። በተለይ የኔ ትውልድ አደራ!”የሚል ኗሪውን እረፍት የሚነሳ ተማጽኖ በጽሁፍ አስቀምጦ የመጨረሻውን ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ለዚህ የሙት አደራ ምላሻችን ምንድነው?
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በወጣት ሳሙኤል አወቀ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል፤ ለቤተሰቦቹም መጽናናትን ይመኛል።
ዛሬን እየኖርን ያለነው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከሀቅ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠናል። እንዴት ነው የሳሙኤል አወቀ እና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰማዕታት አደራ መወጣት የምንችለው? እንዴት ነው ይህንን የህወሓት ፋሽስታዊ ዘረኛ ሥርዓት ማስወገድና በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነበት፤ የአገር አንድነት የተረጋገጠበት ሥርዓት መገንባት የምንችለው? እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለዚህ ትግል የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ምንድነው? ማንን ነው የምንጠብቀው?
አርበኞች ግንቦት 7 መፍትሔው ሁለገብ ትግል ነው ብሎ ያምናል። ሁለገብ ትግል ደግሞ ሕዝባዊ አመጽንና ሕዝባዊ እምቢተኝነትን አቀናጅቶና አስማምቶ ማራመድን ይጠይቃል። በሁለገብ ትግል እያንዳንዱ ለውጥ ፈላጊ የሚያበረክተው ነገር አለ። ሁለገብ ትግልን የሆነ አካል የሆነ ቦታ እስኪጀምረው መጠበቅ አይገባም፤ እያንዳንዳንችን እንደሁኔታው በየአካባቢያችን ልንጀምረው የምንችለው የትግል ስትራቴጄ ነው። ሁለገብ ትግል በየአካባቢያችን በምስጢር በመደራጀት “እኔም ኃላፊነት አለብኝ” እንድንል የሚያደርግ አሳታፊ የሆነ የትግል ስትራቴጂ ነው። ሁለገብ ትግል ጥቂቶችን ሳይሆን በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሚያሳትፍ ሕዝባዊ ትግል ነው።
በየጊዜው በህወሓት ፋሽስቶች ለሚደርስብን በደል ምላሽ መስጠት የሚኖርብን በየአካባቢያችን በምስጢር በመደራጀት ለአምባገነን አገዛዝ ያለን ጥላቻ ስንገልጽ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከራሱ ይጀምር፤ ለህወሓት አምባገነን አገዛዝ ላለመንበርከክ ቃል ይግባ፤ ከሚመስለው ጋር ይቧደን፤ የትግሉን አቅም ይገንባ፤ በአቅሙ መጠን አምባገነኑን ሥርዓት ይገዳደር። ትግሉ እሆነ ቦታ እስኪጀመር መጠበቁን ትተን በሁሉም ከተሞችና በሁሉም የገጠር መንደሮች በአቅማችን መጠን ትግሉን እናፋፍም። እያንዳንችን ለነፃነታችን ኃላፊነት አለብን። የሰማዕታት አደራ የእያንዳንዳችን አዕምሮ እረፍት ሊነሳ ይገባል። ይህንን ስናደርግ ነው ለሰማዕታቱ አደራ ምላሽ ሰጠን ማለት የምንችለው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
No comments:
Post a Comment