በህወሓት ስር የሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦች መካከል ሰፍኖ የቆየው አለመተማመን ከጫፍ ደርሶ የጠብመንጃ አፈሙዝ ሊያዟዙራቸው መቃረቡ ታወቀ፡፡
የሰራዊቱ አዛዦች እርስበርስ በጥርጣሬ አይን ስለሚተያዩ አንዱ ሌላውን በመሰለልና በማሰለል ስራ ላይ ተጠምደው የባጁ ሲሆን አሁን ደግሞ በቅርቡ አለመተማመን የወለደው አዲስ መመሪያ በኤታማጆር ሹሙ ሳሞራ የኑስ አማካኝነት ወርዶ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ መመሪያው በመከላከያ ሰራዊቱ የእዝ እርከን ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ በዋና አዛዦች ስር ሦስት ምክትል አዛዦች እንዲቀመጡ በማድረግ የአወቃቀር ለውጥ እንዲኖር ያስገደደ ነው፡፡
በዋና አዛዡ ስር አዲስ የተዋቀሩት ሦስቱ የምክትል አዛዥ ቦታዎች ምክትል አዛዥና የሎጅስቲክ ኃላፊ፣ ምክትል አዛዥና የአስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ እንዲሁም በተጨማሪ ምክትል አዛዥና የዘመቻ ኃላፊ ናቸው፡፡ መዋቅሩ የተዘረጋው የህወሓት አገዛዝ ከትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ውጭ በሆኑ የሰራዊቱ አዛዦች ላይ ቅንጣት ታክል እንኳን እምነት ስለሌለው ለቁጥጥር እንዲያመቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ይህ በመከላከያ ውስጥ ከታች እስከ ላይ ሙሉ በሙሉ እየተተገበረ የሚገኘው በአንድ ኃላፊ ስር ሦስት ምክትል ኃላፊዎችን በማስቀመጥ ከህወሓት አባላት ውጭ የሆኑ ባለስልጣናትን የመቆጣጠሪያ ዘዴ ከዚህ በፊትም የህወሓት-ኢህአዴግ አገዛዝ አሻንጉሊት ጠ/ሚንስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ላይ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ አሻንጉሊቱ ጠ/ሚኒስተር ኃ/ማርያም ደሳለኝ በስሩ ሦስት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች እንደተሾሙበት ይታወቃል፡፡
የሰራዊቱ ገዥ የህወሓት ጀነራሎች ከትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ውጭ በሆኑ ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖች ላይ ጆሮ ጠቢ በመመደብ የሚሰልሏቸው ሲሆን በህወሓቶችም መካከል እያደር አለመተማመን በማቆጥቆጡ ጭምር የጀነራል ሳሞራ የኑስ ቀኝ እጅ የሆኑ የቅርብ ሰዎች በመከላከያ ውስጥ ያሉ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን እንዲይዙ እየተደረግ ይገኛል፡፡
እረዘም ላሉ ዓመታት የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሆኖ የቆየው ሜጀር ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በሌተናል ጀነራልነት የማዕረግ ዕድገት ማሽበልበያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስም ዘወር እንዲል ተደርጓል፡፡ በምትኩ ከሳሞራ ቡችላዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ሜጀር ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ የምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ በመሆን ተሹሟል፡፡
በመከላከያ አዛዦች መካከል ሰፍኖ የሚገኘው አለመተማመን ስር ሰዶ በመንሰራፋት በህወሓት ሰዎችም መካከል ጭምር በመከሰቱ ሳሞራ የኑስና ቡችሎቹ በሚጠራጠሩት የምስራቅ ዕዝ አዛዥ አብርሃ ወ/ማርያም ላይ በምክትል አዛዥና የሎጅስቲክ ኃላፊ ስም ብርጋዴር ጀነራል የማነ ሙሉን በሰላይነትና በተቆጣጣሪነት መድበውታል፡፡ በተጨማሪም ሜጀር ጀነራል አብረሃ ወ/ማርያምን በከፍተኛ ሹመት ስም ወደ መከላከያ መምሪያ በማዛወር በምክትል አዛዥነትና የሎጅስቲክ ሃላፊ ስም ሰላይና ተቆጣጣሪ ሆኖ የተመደበውን ብርጋዴር ጀነራል የማነ ሙሉን የምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ የማድረግ እቅድ እንዳለ የመከላከያ ውስጥ አዋቂዎች ለአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ዜና ምጮች ገልፀዋል፡፡
No comments:
Post a Comment