Tuesday, July 18, 2017

የመከላከያ ሰራዊትና ሚናው (ከአርበኞች ግንቦት 7)

July 18, 2017

ለአንዲት አገር በሁለንተናዊ መልኩ ከሚያስፈልጓት መሰረታዊ ተቋማት መካከል ወሳኙና የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የጸጥታው አካል ነው። አገሪቱ ዳር ድንበራ ተከብሮ፣ ዜጎቿ ያለስጋት በሰላም ወጥተው እንዲገቡ በማድረግ ደረጃ የጸጥታ አካላት የሚወጡት ሚና እጅግ የላቀ እንደ ሆነ አሌ የማይባል ሃቅ ነው።
Relatert bilde
በዚህ የጸጥታ አካል እየተባለ በሚጠራው ተቋም ዋና ዋና ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፖሊስ ሰራዊት እና የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤቶች ይገኙበታል።

በተለይ ከሶስቱ  ተቋማት መካከል መከላከያ ሰራዊት ለአንዲት አገር የሚያበረክተው ሁለንተናዊ አስተዋጽዎ የማይተካ ሚና እንዲኖረው ሆኗል። ይህ ሲባል ግን የፖሊስ ሆነ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤቶችም የሚያበረክቱተን ትሩፋት ዝቅ ለማድረግ ወይም ለማንኳሰስ ታስቦ አይደለም። የዛሬ ርእሰ ጉዳያችን ስለመከላከያ ሰራዊት በመሆኑ ነው።
የመከላከያ ሰራዊት የሚያበረክተውአ ስተዋጽዎ አገሪቷን እንደሚመሯት ወይም እንደሚገዟት አካላት መስረታዊ ባህሪያት ይወሰናል። ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በሚከተሉ አገሮች የመከላከያ ተቋም ለሚወጣው ሚና መሰረቱ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት፣ ህዝባዊ ወገንተኝነት እና የሃገር ጥቅምና ፍላጎትነው።
ይሁን እንጂ በአምባገነን መንግስታት በሚዘወር አገዛዝ የሚገኝ የመከላከያ ሰራዊት ሚና የፈላጭ ቆራጭ ገዢዎችን ወንበር ከማሞቅና መንበረ-ዙፋናቸወን ከመጠበቅ የዘለለ ለሃገሩና ለህዝቡ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ያንያክል ጉልህ ሁኖ አይታይም። እንዲያውም ህዝብን በመጨፍጨፍ፣የመብት ጥያቄዎችን በማደናቀፍ፣የሃገርን ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማዘረፍ በሃገር ላይ ጥቁር አሻራ ጥሎ ያልፋል።በተጨማሪም የአምባገነኖች መጨቆኛ መሳሪያ በመሆን በስም ብቻ የሃገርን ስም ወርሶ ማደናገሪያ ይሆናል።
ሰለዚህ አጠቃላይ ስለ መከላከያ ሰራዊት ይህን ካልን፣ የሃገራችን የመከላከያ ተቋም ለሃገሩ ያበረከተው  አስተዋጽዖ ምን ይመስላል? የሚለውን ለማየት እንሞክራለን።
ሃገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ የተደራጀ እና ዘመኑ የሚጠይቀውን የመከላከያ ተቋም መገንባት ከጀመረች ገና አንድ ክፍለ ዘመን እንኳን አልደፈነችም። ከዚህ ላይ ግን አሁን ያለው በህወሃት የሚዘወረው የመከላከያ ተቋም፣እንደ ተቋም የቆመ ሳይሆን የተቦረቦረ፣ የነቀዘ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል።
ኢትዮጵያን ከዘመነ-መሳፍት የእርስ በርስ መንቆራቆስ መንጥቆ ያወጣት አጼ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ የተደራጀና በወቅቱ የነበረውን የዘመኑን መሳሪያ የታጠቀ ሰራዊት እንደሚያስፈልጋት ልብ ብሎ ነበር።ምክኒያቱም በደረስጌ ማርያም ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ-ነገስት ዘ-ኢትዮጵያ ተብሎ ከመንገሱ በፊት፣በሽፍትነት ዘመኑ በ1845 ዓ.ም ከማሃዲስቶች ጋር ጦርነት ገጥሟል። ከመሃዲስቶች ጋር ያደረገው ጦርነት የቋራው ካሳ የተደራጀና የታጠቀ ሰራዊት ለአንዲት አገር  ምን ያህል የህልውና መሰረት እንደሆነ በጥለቅት የተረዳበት እንደሆነ ይነገራል። በዚህም አጼ ቴዎድሮስ በደሞዝ የሚተዳደር ሰራዊት በመፍጠርና በሃገራችን ብሎም በአፍሪካ ደረጀ የመጀመሪያውን መድፍ በማስራት ፈር ቀዳጅ መሪ ለመሆን ችሏል።
ከዚያም ከጀግናው ቴዎድሮስ በኋላ የመጡት ነገስታት የተጠናቀረ የሰራዊት አቅም እንዲኖራቸው ያቅማቸውን ሰርተው አልፈዋል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመናዊ የመከላከያ ሰራዊት መገንባት የተጀመረው በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ-መንግስት በ1927 ዓ.ም እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል። በንጉሱ ዘመን የነበረውን ሰራዊት እንደተቋም ለመገንባት ብዙ ተለፍቷል። ከዛሬው ህወሃት ከሚዘውረው ሰራዊት ጋር ጨርሶ ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም። የሰራዊቱ አባል የሆኑ ከከፍተኛ መኮንን እስከተራው ወታደር ድረስ ህዝባዊ ወገንተኝንነት የሚሰማቸው፣ ለህዝብ ጥቅም የቆሙና በብቃታቸው የተመሰከረላቸው እንደነበረ ማንም የሚረዳው ሃቅ ነው።
ለዚህ አባባላችን እንደ አስረጅነት ሊቀርብ የሚገባው በታሪክ “የታህሳሱ ግርግር” እየተባለ የሚጠራውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በ1953 ዓ.ም በንጉሱ ላይ የተሞከረውን መፈንቅለ-መንግስት ከጥንስሱ ጀምሮ የመሩት በከፍተኛ ወታደራዊ የመኮንነት መአረግ ተቀምጠው የነበሩ መኮንኖች ነበሩ። እነኝህ መኮንኖች የሃገር ጉዳይ እንጂ በግላቸው ከማንም በላይ በወቅቱ በነበረው የህይወት ከፍታ ላይ የተቀመጡ ነበሩ። ቢሆንም ግን ቅጥያጣው የንጉሳዊው ስርዓት በህዝብ ላይ ያደርስ የነበረውን በደል እንደ ዛሬዎቹ “ጀሮ ዳባ ልበስ” ወይም  “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል ብሂል አልተሸበቡም ነበር። ለህዝብ ሲሉ የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ አደረጉ። ግን ከሸፈ። በዚህም ምክንያት የህይወት መስዋእትነት ከፍለዋል። እነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ፣ ጀነራል ጽጌ ዲቡ፣ ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ፣ ሻለቃ ዮሐንስ ምስክር እና የመሳሰሉት አንጸባራቂና ቀጣይ የሃገሪቷን እጣ ፋንታ አመላካች የሆነ ታሪክ ሰርተው አልፈዋል።
ይሁን እንጂ የመፈቅለ-መንግስቱ ሙከራ ቢከሽፍም፣ ክሽፈቱን ተከትሎ ወታደራዊ አዛዦቹ ቢገደሉም፣“ንጉስ አይከሰስ፣ ሰማይ አይታረስ” ይባል የነበረው ብሂል ፉርሽ ሊያደርገው ችሏል። በዚህም የ53ቱ የመፈንቅለ-መንግስት ለ1966ቱ አብዮት መነሳት መሰረት ጥሎ ማለፉን ሁሉም የታሪክ አዋቂዎች በአንድ ድምጽ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።
የንጉሱ ስርዓት እዲወድቅ ብሎም በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን የሰለሞናዊው ስርወ-መንግስት እዲያከትም ሰራዊቱ ትልቅ ሚና እንደተወጣ አሌ የሚባል አይደለም። ይህ ሲባል ግን ተቋሙ እደተቋም ሙሉ በሙሉ ከህዝብ ጎን የተሰለፈ ነው ማለት አይደለም። ግን አሁን እንዳለው ህወሃት እንደ ሚዘውረው የመከላከያ ሰራዊት ሙሉ በሙሉ ለመንግስት አጎብዳጅ እና ሰጋጅ አልነበረም።
ሰራዊቱ በአብዮቱ ወቅት በቀጥታ የህዝብን ጥያቄ ከህዝብ ጋር ተሰልፈው የወቅቱን መፎክሮች ከፍ አድርጎ በማሳየትና በማስተጋባት የለውጡ አካል ነበር። በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከግቢያቸው ውስጥ ሆነው በሚያሰሙት ተቃውሞ ላይ የሰራዊቱ አባላት ወደ ተማሪዎች እንኳን የሩምታ ተኩስ ከፍተው ተማሪዎችን   ሊጨፈጭፉ ቀርቶ፣አንድም የጸጥታ አካል የዩኒቨርስቲውን በር አልፎ መግባት አይችልም ነበር። የዛሬዎቹ ግን የእውቀት መአድ የሆነውን ክቡር ተቋም በሩን በመገንጠል፣ማአዱን በመርገጥ ከተማሪዎች የመኝታ ክፍል ድረስ ዘልቀው በመግባት የጅምላ ጭፍጨፋዎችን አካሂደዋል። ዛሬም ይህን ድርጊታቸውን እየፈጸሙ ይገኛሉ።
የ66ቱ አብዮት ንጉሱን ከስልጣን ቢያስወግድም ኢትዮጵያን ከዘውዳዊው ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አላሸጋገራትም። “ከድጡ ወደ ማጡ” እንደሚባለው ቁልቁል አሽቀነጠራት እንጂ። ወታደራዊ መንግስት ደርግ የብልጣ-ብልጥነት መንገድን በመከተል፣ አንዴ ለንጉሱ ታማኝ መስሎ በመታየት፣
በሌላ ጊዜ ደግሞ ከህዝቡ ጎን የቆመ በመምስል፣በህዝቡ መስዋዕትነት ላይ አመድ ነስንሶ መስከረም ሁለት 1967 ዓ.ም ንጉሱን ገልበጦ ከዙፋኑ ኮረቻ ላይ ፊጥ አለ። ቢሆንም ግን የዙፋኑ ኮረቻ ሊደላደልለት አልቻለም። ለ17 አመታት በአራቱም አቅጣጫ በጦርነት ተወጥሮ አንድም ቀን ሰላማዊ እንቅልፍ ሳያንቀላፋ እደማሰነ ነበር የከረመው።
ኢትዮጵያ በተዘፈቀችበት መቋጫ ባጣው የዕርስ በዕርስ ጦርነት ምክንያት የሚረግፈው የሰው ህይወት፣የሚወድመው የሃገር ሃብት፣ በእጅጉ ያሳሰባቸው ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ቀውሱ በሰላማዊና በጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሄ እንዲያገኝ በተለያየ አጋጣሚ ቢወተውቱም ውትወታቸውም ሆነ ጩኸታቸው ጀሮ አላገኝም። ማንም ከቁብ የቆጠረው አልነበረም።
ኢትጵያን ይገዛት የነበረው ወታደራዊው መንግስት የመታበይ አባዜ የተጠናወተው ስለለነበረ ሁሉንም ነገር በጡንቻው ጭጭ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ በመሆኑ ከምድር ጦር እስከ አየር ሃይል፣ ከአየር ሃየል እስከ ባህር ሃይል የነበሩ ከፍተኛ መኮንኖች ሌላ ምርጫ ለማየት አማተሩ። እናም በታሪክ “የግንቦት ስምንቱ መፈንቅለ መንግስት” እየተባለ የሚጠራውን መፈንቅለ-መንግስት ግንቦተት 8/1981 ዓ.ም አደረጉ። ነገር ግን መፈንቅለ መንግስቱ እንደ “ታህሳሱ” ሁሉ ይሄኛውም ከሸፈ።
የመፈንቅለ መንግስቱን መክሸፍ ተከትሎ አገራችን ኢትዮጵያ እስከ ዛሬም ድረስ ልተካቸው ያልቻለቻቸውን ምርጥ የጦር መሃንዲሶቿን በአንድ ጀበር አጥታለች። ካጣቻቸው የጦር መሃንዲሶቿ መካከል፦ሜ/ጀ ፋንታ በላይ፣ ሜ/ጀ አምሃ ደስታ፣ ሜ/ጀ መርዕድ ንጉሴ፣ ሜ/ጀ ደምሴ ቡልቶ፣ ብ/ጀ ሰሎሞን በጋሻርው፣ ብ/ጄ ተስፋዬ ትርፌ፣ ብ/ጄ ንጉሴ ዘርጋውና በአጠቃላይ ወደ 30 የሚሆኑ ከፍተኛ የጦር መኮንኖቿ በአንድ ጀምበር ላይመለሱ አሸልበዋል። መኮንኖቹም ለሃገራቸውና ለህዝባቸው ፍትህ፣እኩልነት፣ ሰላምና ዴሞክራስን ለማምጣት ሲሉ ሰማእትነትን ተቀብለዋል። ይህን ተከትሎ የደርግ ስርዓትም ፍጻሜ መንግስቱ መቃረቡን የጦር ሜዳ ተንታኝ ሳያስፈልግ ሁሉም  ሰው በቀላሉ መገንዘብ ቻለ። እናም ስርዓቱ የቁልቁለት መንገዱን ተያይዞት ተንሸራቶ ተንሸራቶ በመጨረሻም 1983 ዓ.ም ወርዶ በመፈጥፈጥ ላይመለስ እስከ ወዳኛው ሄዷል። የስርአቱ ቁንጮ የሆነው ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማሪያምም ሃገር ጥሎ ሊሄድ ችሏል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ለሌላ የቀን ጅብ ለሆነ ስርዓት ልትዳረግ ችላለች።
ከዚያ በኋላ ዘረኛው እና ፋሺሺታዊው ቡድን “ህ.ወ.ሃ.ት” መንበረ ዙፋኑን ተቆጣጥሮ ሃገሪቷን እንዳሻው እያደረጋት ይገኛል።
ህወሃት ስልጣነ ወንበሩ ላይ ፊጥ ካለ በኋላ በቀጥታ በጠላትነት የፈረጀውን የኢትዮጵያ የቀድሞ ጦር ሰራዊት መናድና ማፍረስ ነው የጀመረው። “ደርግ የነካው ሰይጣን የነካው” በሚል ብሂል የአየር ሃይሉን፣የምድር ሃይሉን፣ የባህር ሃይሉን፣ የፖሊስ ሰራዊቱን እና የደህንነት መስሪያ ቤቱን በአጠቃላየይ የሲቪል ተቋማትን ሳይቀር አፈራርሷቸዋል።
በአብዛኛዎቹ አለም አገሮች የስልጣን ለውጥ ሲመጣ ሁሉንም ነገር ንደው ከዜሮ ሲጀምሩ አይታዩም።ካለው ላይ እየጨመሩ፣ህዝባቸውና አስተዳደራዊ ዘይቤያቸው በሚፈልገው መንገድ እየቃኙ ይሄዳሉ እንጂ። ህወሃት ግን ማፍረስ፣ ንዶ ማስቀረት ነው የተያያዘው። የመገንባት ሳይሆን የማፍረስ አባዜ የተጣባው ስረዓት  እንደሆነ በሚገባ አስመስክሯል።
በ1969 ዓ.ም በጀነራል ዚያድ ባሬ የሚመራው የሱማሊያ ጦር ኢትዮጵያን ለመውረ ሞከረ። በዚያን  ወቅት በጀግንት አገራቸውን በመከላከል ብሎም መልሶ በማጥቃ የዚያድ ባሬን “ታላቋን ሱማሌ” የመመስረት ህልም ቅዠት ያደረጉትን የቀደሞ የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት አባላትን ሳይቀር ገድሏል፤ አስሯል። ዘብጥያ ያልከተታቸውን ደግሞ በማዋረድ እንዲባረሩ ሆነዋል። ለሃገራቸው ሲሉ የአካል መስዋእትነት የከፈሉትን የጦር ጉዳተኞች ሳይቀር ጎዳና ላይ በመበተን ለስቃይ ህይወት እንዲዳረጉ ሆነዋል።  ኢትዮጵያ ዳግም
“ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ።” ተብሎ እንዲ-ተረትባት ሆኗል።
በቅንነት ሃገራቸውን ያገለገሉት በኋላም ዘረኛውና ፋሺስቱ ህወሃት ሃገሪቱን ሲቆጣጠር በግፍ የተባረሩት  የሰራዊቱ አባላት በየሄዱበት የአንጋፋውን ድምጻዊ የሙሃሙድ አህመድን  ዜማ እንዲህ በማለት ነበር ሲያንጎራጉሩ የነበረው
“ለዋልኩት ውለታ ይኸ ነው ወይ ውርሴ
ልፋቴ ድካሜ ይኸው ነው ውርሴ
እንግዲህ ምንበል ይህ ከሆነ ቅርሴ
አሃ∙∙∙ዝምታ ነው መልሴ”
በዚህም አላበቁም የድምጻዊ  ኬነዲ መንገሻን ዜማም ደገሙ።
“ብድርስ ይሄው ነው ወይ
ውለታስ ይሄው ነው ወይ
ሰው አልወጣልኝም እኔስ አወይ∙∙∙አወይ”
“ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንደሚባለው ሁሉ፣ ህወሃት በሻእቢያ ታዝሎ የአራት-ኪሎ ቤተ-መንግስትን ከተቆጣጠረ በኋላ የሃገሪቱን ሁለተናዊ ገቢር *በሱ ጥብቆ ልክ ሰፍቶ እንኩ ልበሱት አለን።ህወሃት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ደረጃ ትልቅ ስምና ዝና ተጎናጽፎ የነበረውን የቀድሞ ጦር ተቋም እንዳልነበረ አደረጎ ካፈረሰ በኋላ በ1987 ዓ.ም በራሱ አምሳል የጠፈጠፈውን መከላከያ ሰራዊት ገነባሁ ብሎ በአደባባይ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ከበሮ ሲደልቅ ተስተውሏል። አሽሟጣጮችም “ድንቄም መገንባት እቴ” ሲሉ ተሳልቀዋል።
ህወሃት ገነባሁት ያለውን የመከላከያ ተቋም ከአናቱ ላይ ወጥተው እንዲያሽከረክሩት፣ብሎም ወደ ገደል እንዲዶሉት ምንም አይነት መሰረታዊ የውትድርና ሳይንስ እውቀት በሌላቸው የጫካ ታጋዮች እንዲደናበር ተፈርዶበታል። እነኝህ የዘረኝነት አባዜ የተጠናወታቸው፣ በአንዴ ከተራ ሽምቅ ተዋጊነት እስከ ጀነራልነት መአረግ ተቆጥሮና ተሰፍሮ የታደላቸው ወታደራዊ አዛዥ ተብየዎች በስራቸው የሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊት በዘርና በጎሳ ከፋፍለው እርሱ በእሱ የማይተማመን ተጠራጣሪ ሰራዊት አድርገውታል።
ይህ ገነባነው ያሉት ሰራዊት ሃገራዊ ግዳጆችን በብቃት የማይወጣና የሞራል መንፈሱም ዝቅተኛ እንደሆነ በተግባር ታይቷል።
እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1999 ዓ.ም ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊ የያኔው የኢስላማዊ ፍርድቤቶች ህብረት ወይም Islamic court የአሁን አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ የሽብር አደጋ ደቅኗል በሚል ሰበብ ወደ ሱማያ ሰራዊቱ እንዲገባ ተደርጓል። አቶ መለስም በፓርላማ ቀርቦ ወደ ሱማሊያ የዘመተው ሃይል የኢስላማዊ ፍ/ቤቶችን ህብረትን በአጭር ጊዜ ደምስሶ እንደሚመለስ መጀመሪያ ሰራዊት ሲያዘምት ላላማከረው  ህዝብ ቃል ገባ። ግን አልሆነም። ዛሬ መለስ የለም። ቃሉን ቅርጥፍጥፍ አድርጎ በልቶ መቃብር ወርዷል። ለአጭር ጊዜ የተባለው ዘመቻ 10 ዓመታትን አስቆጥሯል። ጦርነቱ አሁንም እንደ ቀጠለነው። የወያኔ የሲቪል ባለስልጣናት ሆኑ ወታደራዊ ሹማምንቶች በተዘዋዋሪም ቢሆን አላዋቂነታቸውን በአደባባይ ነግረዉናል። ለህዝብ ቃል ሲገቡ መረጃን በመንተራስ ሳይሆን ካፋቸው የመጣላቸውን እንደ ወርደ ወይም በዘፈቀደ እንደሚናገሩ በተደጋጋሚ አሳይተውናል። ጦርነት ሲያውጁ የጠላትን ደካማና ጠንካራ ጎኖችን ሳያጠኑ በጭፍን ብቻ ወደ ጦርነት የድሃን ልጆችን በመማገድ ሲያስፈጁ በተደጋጋሚ አስተውለናል። አሁንም አላቆመም። አንድ የጦር መሃንዲስ የሚመራውን ሰራዊት ወደ ጦርነት ከማስገባቱ በፊት ስለጠላት በቂ መረጃዎችን ማሰባሰብ ይኖርበታል። ጠላት የታጠቀውን የጦር መሳሪያ፣የያዘውን ቦታ፣ የሰራዊቱን ቁጥር፣ የአይር ንብረቱ ከጠላት በስተጀርባ ማን አለ? ወዘተ ሳይቀር ቀድሞ ማጥናት ግድ ይለዋል። በሶማሊያው ጦርነት ከ10,000 በላይ የመከላከያ ሰራዊት እንደ ቅጠል ረግፏል። ዛሬም በሱማሊያ ውስጥ በጦርነት እንዳክራለን።  የህወሃት ጄነራሎች በሰራዊቱ ደም ላይ ቅምጥል ኑሯቸውን ይኖራሉ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ይገነባሉ።
በእርግጥ ከአልሸባብ ጋር የሚደረገው ጦርነት ቢቀጥል ለወያኔ ባልስልጣናትም ሆነ ለጦር ሹማምንት እሰየው የሚያስብል እንጂ የሚከፋቸው አይሆንም። በዚህም ሳቢያ ጦርነቱ እንዲቀጥል አጥብቀው እየሰሩ ይገኛሉ። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራፕ ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት አሜሪካ አልሻባብን ለመደመሰስ እየተከተለችው ያለው ስልት ትርጉም አልባ መሆኑን፣ እናም አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ሱማሊያ ታዘምታለች፤ መባሉን ተከትሎ የህወሃት መራሹ መከላከያ ሰራዊት በአዛዞቹ ትእዛዝ ያልምንም ጦርነት በቁጥጥራቸው ስር የነበሩትን ግዛቶች እንዲለቁ ተደርገዋል። በዚህም ቦታዎቹን አልሸባብ እንዲይዛቸው አስችለዋል። የአልሻባብ ጋር የሚደረገው ጦርነት ለወያኔ ሹማምንት ገንዘብ ማጋበሻ መሆኑ የአደባባይ ሃቅ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል።
አልሸባብ ከምድረ-ገጽ ቢጠፋ ወያኔዎች ከምዕራቡ ዓለም የሚያገኙት የኢኮኖሚም ሆነ የዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ይነጥፋል። በአሁኑ ወቅት ወያኔ በሰላም አስከባሪ ስም በሱማሊያ፣ በዳርፉርና በደቡብ ሱዳን አያሌ ሰራዊት  አሰማርቷል። ለእያንዳዱ ሰራዊት በነፍስ ወከፍ በየወሩ 1200 ዶላር በላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይከፍላል። ይሁን እንጂ ለእያንዳንዱ ሰራዊት  የሚከፍለው ከ200 ዶላር ያነሰ ነው። ቀሪው በየወሩ የሚገኘው በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የወታደራዊ አዛዞቹን ካዝና ያሞቃል። በተጨማሪም ከነፍስ ካሳ፣ ከመሳሪያዎች፣ ከተሽከርካሪዎች፣ ከአውሮፕላን ኪራይ በአጠቃላይ ከተያዩ የወታደራዊ እቃዎች የሚገኙ የዶላር ክፍያዎች ሁሉ ቀጥታ ወደ ወታደራዊ አዛዦች የግል ኪስ ይሰገሰጋል። በወያኔዎች ዘንድ የአልሻባብ መኖር የገንዘብ ፍላጎታቸው ማርኪያ መሰረት ስለሆነ የአልሸባብን መጥፋት በጽኑ ይቃወሙታል። ይበልጥ በእጅ አዙር መሳሪያ ለአልሻባብ መሳሪያ እየቸበቸቡ ይከብሩበታል። በዚህም ሂደት ምስኪኑ የመከላከያ ሰራዊት በማያውቀው ጦርነት ጭዳ እንዲሆን ይገደዳል።
የመከላከያ ሰራዊትና ሚናው በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ፅሁፍ በዚህ አላበቃም ሁለተኛው ክፍል ሳምንት ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment