በዚህ በዛሬው የአርበኞች ማስታወሻ መርሃ ግብራችን ውስጥ አንድ ጀግና አርበኛን እናስተዋውቃችኋለን።
በ3 ሺህ ዘመን ታሪኳ ውስጥ ማህጸኗ መቼም ቢሆን የቁርጥ ቀን ልጆች ከመጸነስ፣ ከመሸከምና ከመውለድ አቋርጣ የማታውቀው እናታችን ኢትዮጲያ ዛሬም እንዲሁ ጀግና ወልዳልናለች። ይህ ጀግና አርበኛ የተፈጠረበትን፣የመጣበትን ዋና ተልዕኮ ፈጽሞ፣ ሩጭውንም ጨርሶ ወደማይቀረው አለም በክብርና በነጻነት ሄዷል።
የኢትዮጲያ ማህጸን ወልዳው የጀግኖች መፍለቂያ የሆነችው የወልቃይት ጸገዴ ምድር ያሳደገችው ይህ አርበኛ ብርሃኑ ጀግኔ ይባላል። የአርበኛ ታጋይ ብርሃኑ ጀግኔ ሕይወቱና ሞቱ ከወልቃይት ምድር፣ ከወልቃይት ዉሃ፣ ከወልቃይት አየር፣ ከወልቃይት ታሪክና ባጠቃላይ ከዚህ አካባቢ ማንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነበር። በተለይም ደግሞ የወልቃይት ጸገዴ ሕዝብ ሕወሃት በሚባል ሀገር በቀል ክፉ መንፈስ ከደረሰበት የ40 አመት ግፍ፣ መከራ፣ ስደት፣ሞትና የዘር ማጽዳት ወንጀል ጋር በተያያዘ ሲወሳ የብርሃኑ ጀግኔ ስም መነሳቱ የግድ ነው። የሕይወቱም የሞቱም ቃል ኪዳን ከወልቃይት ጠገዴ ጋር ላይፋቱ ተጣምረዋልና።
እንደሚታወቀው የወልቃይት ጸገዴ ህዝብ ከ1972 ዓ-ም ጀምሮ ተስፋፊዉ የህዉሃት ቡድን ባቀነባበረዉ ሴራና ተንኮል ተተብትቦ ታስሮ ሁሉንም መራራ ነገር መቅመስ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም መራራ ነገር ጨልጦ እንዲጠጣ የተፈረደበት ህዝብ ነዉ።
ህዉሃቶች የታላቋ ትግራይን የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግ እና ከሱዳን ጋር ለሚኖራቸዉ ግኑኝነት በደረቅ ወደብነት የሚያገለግል በር ለማግኘት ሲሉ፤ አቋም ይዘዉና በስትራቴጅ ነድፈዉ የወልቃይት ጸገዴን ህዝብ በማስገደድ የተለያየ ሴራና ተንኮል በመፍተል የአካባቢዉን መሬት ተቆጣጥረን ወደ ትግራይ ማካለል ወሳኝነት አለዉ ብለዉ በማመናቸዉ
ይህንም ምኞታችዉን ተግባራዊ ለማድረግ ተከዜን ተሻግረዉ መሪቱን መርገጥ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በአርማጭሆና በመተማ በተለይም በወልቃይት ጸገዴ ህዝብ ላይ በጣም ዘግናኝ የሆነ የዘር ማጽዳት ወንጀል የፈጸሙበት አካባቢ ነዉ።
በርግጥ የህዉሃቶች በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የአገዛዝ ስልጣኑን ከጨበጡ በኋላ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል በዘመኑ ወደር የማይገኝለት በዘር ላይ ያነጻጸሩ አስከፊ ወንጀሎችን መፈጸማቸዉ ለማንም የተሰወረ አይደለም።
በዚህም መነሻ ምክኒያት የወልቃይት ተወላጅ የሆነዉ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ታጋይ ብርሃኑ ጀግኔ ከልጅነቱ ጀምሮ የቡድኑን አሳፋሪና ፍጹም ስብእና የሌለዉን ተግባር እያየና እየሰማ ስላደገ፤ ህዉሃት ለኢትዮጵያ ህዝብ የማይጠቅምና የማይበጅ መሆኑን በጥልቀት ስላወቀ ፤በ1997ዓ/ም እና ከዝያም በፊት አገዛዙን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመተካት በሰላማዊ መንገድ ከፍተኛ ትግል አድርጓል።
አርበኛ ታጋይ ብርሃኑ ጀግኔ በጎንደር ከተማ በደብረ ሰላም ካቶሊክ ትምህርት ቤት ለረዥም ዓመታት በመምህርነት ሞያ ያገለገለ በስነ-ምግባሩ የተወደደና የተከበረ ሰዉ እንደነበር የሚይዉቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል።
ነገር ግን ከአግዛዙ ሹመኞች ጋር በነበረዉ የፖለቲካ ልዩነት ምክኒያት የጎንደርን ከተማ ለቆ ወደ ጎንደር ምእራብ አርማጭሆ አብራ ጅራ ከተማ በመሄድ ከመምህርነቱ በትጓዳኝ ተምሮ በያዘዉ የፋርማሲስት ሙያ የመድሃኒት መሸጫ መደብር በመክፈት እንዲሁም የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችን የእንስሳት እርባታና የእርሻ ስራን አጣምሮ በመስራት ኑሮዉን ይመራ ነበር ።
ሆኖም ግን የህዉሃት ቡድን በሃገሪቱ ዜጎች ላይ በእብሪት ከጊዜ ወደ ጊዜ ግድያና አፈናን አባብሶ የመሬት ወረራዉን አጠናክሮ በመቀጠሉና የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን በመሸጡ እንዲሁም የወልቃይት ጸገዴ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ዘወትር በቁጭት የሃገሩ መዋረድ የሚያሳስበው አርበኛ ታጋይ ብርሃኑ ጀግኔ አገዛዙን በሰላማዊ ትግል መቀየር እንደማይቻል ሲያረጋግጥ የሚኖርበት አካባቢ ህብረተሰብ ትግሉን ወደ ህዝባዊ እንቢተኝነት እንድቀይረው በማድረግና ከፊት ሁኖ በመምራት በቁርጠኝነት ታግሏል።
እርበኛ ታጋይ ብርሃኑ ጀግኔ በምእራብ አርማጭሆ ከሚገኙ መሰል ጓደኞቹ ጋር በመሆን የከተማና የገጠር ነዋሪዎችን በመቅስቅስና በማስተባበር ከአገዛዙ ፈቃድ ዉጭ ጥር 16 2007 ዓ ም በአብራ ጅራ ከተማ አገዛዙን የሚያወግዝ ህዝባዊ ስብሰባ እንዲደረግ ከፍተኛ ትግል አድርጟል።
በዚህም ህዝባዊ ስብሰባ በድፍረት የአገዛዙን እስከፊነትና ወራሪነቱን በዝርዝር በመግለጽ ትግሉ ወደ ህዝባዊ እንቢተኝነት እንዲሸጋገር ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሯል ።
አርበኛ ታጋይ ብርሃኑ ጀግኔ በወቅቱ ለተሰብሳቢዉ ከተናገረዉ ንግግር ዉስጥ ለመጥቀስ ያክል ከእንግዲህ ወያኔ በእርኩስ መንፈስ ታድሞ በሃገራችን የስልጣን እድሜዉን የሚያራዝም ከሆነ ለኔ ሳልሞት ነፍስና ስጋየ ሳይለያይ በቁሜ ሞቸ በዚች ምድር ላይ በገሃነም ዉስጥ እየኖርኩ ያለሁ መሆኔን ነዉ የማዉቀዉ-
ስለዚህ ወገኖቸ በህይዎት እያለን በወያኔ ግፍ እኛ መኖር ባንችልም ለመጭዉ ትዉልድ ስንል ነፍስና ስጋን የሚያለያየዉን የጽድቁን ሞት ሞተን ልጆቻችንን ከቁም ሞት እናድናቸዉ ነበር ያለዉ ።
ከስብሰባዉ በኋላም በራሪ ጽሁፍ በማዘጋጀት በአብራጅራና በዙሪያዉ ባሉ ከተሞች ወረቀቶች እንድበተኑና እንድለጠፉ በማድረግ ህዝቡ ስለ አገዛዙ ድብቅ ሴራ አዉቆ ለትግሉ እንድሰለፍ ከፍተኛ ስራ ሰርቷል።
ከዚህ በኋላ ነበር የወያኔ አፋኝ የቡድን አባላት ከአድስ አበባ ወደ አብራ ጅራ ተንቀሳቅሰዉ አርበኛ ታጋይ ብርሃኑ ጀግኔን በጥር 21 ቀን 2007 ዓ ም አፍኖ ለመዉሰድ ሙከራ ያደረጉት። ነገር ግን ታፍኖ እንደተወሰደ አንድ ስዓት በማይሞላ ጊዜ ዉስጥ የአብራ ጅራ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ በጊዚያዊነት ታስሮ እንድቆይ በተደረገበት ፖሊስ ጣቢያ ዘልቆ በመግባት ክታጠቁ ፖሊሶች በሃይል በማስለቀቅ ከእስር ቤት አስወጥቶታል ።
ከእስር ቤቱም እንዲወጣ ተሰበስቦ ለሚጠብቀዉ ህዝብ ምስጋናዉን ከአቅረበ በኋላ- ቀጥሎ የተናገረዉ – ከዚህ የተሰባስባችሁት ወግኖቸ አንድ ሆናችሁ በመተባበራችሁ እኔን በአጭር ስዓት ዉስጥ ከገዳዮቹ እስር ነጻ አዉጥታችሁኛል ።ልክ እንደዛሬዉ ቀን ወደፊት አንድ መሆን ከቻልን በቁርጠኝነት ከተባበርን ሃገራችን ነጻ እንዳትወጣ የሚከለክለን ምንም አይነት ሃይል አይኖርም በማለት ነበር ሃሳቡን የገለጸዉ።
በዚሁ እለት ነበር ጥር 21 ቀን 2007 ዓ ም ሌሊት ልጁንና እናቱን እንድሁም ቤተሰቡን ተለይቶ ቤት ንብረቱን ትቶ አካባቢዉን ለቆ አገዛዙን በሙሉ አቅሙ ለመታገል የካቲት 19 2007 ዓ ም ከአርበኞች ግንቦት 7 ድርጅት ጋር የተቀላቀለዉ።
አርበኛ ታግይ ብርሃኑ ጀግኔ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጠና ከሰለጠነ በኋላ የአርበኞች ግንቦት 7 የትምህርትና ስልጠና መምሪያ የፖለቲካ ሃላፊ በመሆን ብዛት ያላቸዉን ወጣቶች የአርበኝነት የትግል ስንቅ እንዲታጠቁ አድርጓል።
በመጨረሻም አርበኛ ታጋይ ብርሃኑ ጀግኔ የወያኔን አገዛዝ ለማስወገድ በሚደረገዉ የትጥቅ ትግል ተጋድሎ ታላቅ የጀግንነት ጀብዱ ፈጽሞ በተወለደበት በወልቃይት ምድር ለኢትዮጽያ ሃገሩ ሲል ክቡር ህይወቱን አሳልፎ ሰጥቶ በመስዋእትነት ተለይቶናል።
አርበኛ ታጋይ ብርሃኑ ጀግኔን እግዚአብሔር ነፍሱን በገነት ያስቀምጥልን
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ድል ለአርበኞች ግንቦት 7
No comments:
Post a Comment