“እንደጀመሩ የጨረሱ” መሪ
http://www.goolgule.com/bright-future-for-nigeria-goodluck…/
http://www.goolgule.com/bright-future-for-nigeria-goodluck…/
በናይጄሪያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ የፖለቲካ አካሄድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያመጣል የተባለው የሰሞኑ ምርጫ ውጤት ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት የመንፈስ ልዕልና አጎናጽፏቸዋል፡፡ በበርካታ ችግሮች ለተወጠረችው ናይጄሪያ “ብሩህ ጊዜ” ያመጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ፕሬዚዳንት ጉድላክ ዮናታን በምክትልነት ናይጄሪያን እያገለገሉ በነበሩበት ጊዜ በወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዑማሩ ሙሳ ሕይወታቸው በማለፉ ወዲያው የፕሬዚዳንትነት መንበሩን ተረከቡ፡፡ ዑማሩ ሙሳን ተክተው ጥቂት እንዳገለገሉ በወቅቱ በተካሄደ ምርጫ ሙሐማዱ ቡሃሪን አሸንፈው ናይጄሪያን ለአምስት ዓመታት መርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ የዛሬ አምስት ዓመት ባሸነፏቸው መልሰው ተሸንፈው ሥልጣናቸውን በሰላም አስረክበው በናይጄሪያ የምርጫ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ተግባር በመፈጸም ስማቸውን ከመቃብር በላይ ህያው አድርገዋል – ፕሬዚዳንት ጉድላክ ዮናታን!!
ፕሬዚዳንት ዮናታን በሥልጣን በቆዩባቸው ዓመታት በርካታ ተግባራትን እንዳላከናወኑ እንዲያውም ላሁኑ ሽንፈታቸው እነዚሁ ጉዳዮች እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡ የቦኮ ሃራም፣ የሙስና፣ የኢኮኖሚ አለማደግ፣ ወዘተ አንኳር ጉዳዮች ዮናታንን እንዳይመረጡ እንዳስደረጓቸው በስፋት ከሚነገሩት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በምርጫው ዘመቻ ወቅት ውጤቱ ምንም ይሁን ግልጽና ፍትሐዊ ምርጫ በናይጄሪያ እንደሚደረግ ቃል የገቡት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጉድላክ ቃላቸውን ጠብቀዋል፤ የተናገሩትን ፈጽመዋል፤ የጀመሩትን ጨርሰዋል፡፡ የመራጩ ሕዝብ ድምጽ ሙሉ በሙሉ ተቆጥሮ ከመጠናቀቁ በፊት መሸነፋቸውን ባመኑበት ጊዜ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተቀናቃኛቸውን ጄ/ል ሙሐማዱ ቡሃሪን “እንኳን ደስ አልዎት” በማለት አመስግነዋቸዋል፡፡ ለናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በሕዝብ በመመረጣቸውም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ የሕዝብን ድምጽ እንደሚያከብሩ የሰጡትን ቃል በመፈጸም በአገራቸው ታሪክ የማይረሳና የማይሻር አሻራቸውን አትመዋል፡፡ ደም መፋሰስን ገትተዋል፤ ውድመትን፣ ጥላቻን፣ መራርነትን፣ ወዘተ አክሽፈዋል፤ የማያቋርጠውን የሥልጣንና የአምባገነንነትን አዙሪት ሰብረዋል፤ በዚህ ተምሳሌነታቸው እንደ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ እምነት ለሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ብቻ ሳይሆን ለኖቤልም ብቁ ተሸላሚ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡
ጉድላክ ዮናታን በአገሪቱ ሚዲያ ባስተላለፉት “ሽንፈትን የመቀበል” መግለጫ ላይ “ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ ቃል ገብቼ ነበር፤ ቃሌን ጠብቄአለሁ፤ ከዚህ በተጨማሪም ናይጄሪያውያን በዴሞክራሲ ሒደት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምህዳሩን አስፍቼአለሁ፤ ይህ ለአገሬ ትቼ የማልፈው አንዱ ውርስ (ሌጋሲ) ነው፤ ወደፊት እንዲቀጥልም እመኛለሁ” ብለዋል፡፡ ምርጫው ሰላማዊና የተሳካ አንዲሆን የአገሪቱ የደኅንነት ኃይል ላከናወነው ሥራ አድናቆታቸውን ችረዋል፤ የፓርቲ ሰዎቻቸውን እና ዴሞክራሲያዊ መብቱን በተግባር የተጠቀመውን የናይጄሪያን ሕዝብ አመስግነዋል፤ በመጨረሻም ለጄኔራል ሙሃማዱ ቡሃሪ መልካሙን ሁሉ በመመኘት አገራቸውን ፈጣሪ እንዲባርካት በመማጸን ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡
በአገራችን ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው ምርጫ አኳያ የናይጄሪያው አስቀድሞ መከሰቱ፤ ውጤቱ ያልተጠበቀ መሆኑ እንዲሁም የሥልጣን ሽግግሩ “በመተካካት” ሳይሆን በሕዝብ ምርጫ መከናወኑ የበርካታዎችን ቀልብ የሳበ ሆኗል፡፡ በተለይም በናይጄሪያ ታሪክ በሥልጣን ላይ ያለ ፕሬዚዳንት በምርጫ ተሸንፎ ከሥልጣን ሲለቅ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ገዢዎቿ ካልተፈነቀሉ ወይም ካልሞቱ ወይም ካልተሰደዱ መሪ ለመለወጥ ታድላ የማታውቀው አገራቸው ለዚህ ዕድል የምትበቃበት ዘመን መቼ እንደሚሆን የሚጠይቁና የሚወያዩ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከሚወዳደሩበት አካባቢ ለጎልጉል የተላከው መልዕክት እንዲህ ይላል፤ “በመጪው ምርጫ ብዙ አንጠብቅም፤ ሃይለማርያምም “ውርስ ተቀባይና አስፈጻሚ” እንደመሆናቸው ብዙ ይከውናሉ ብለን አንጠብቅም፤ ቢያንስ ግን እርሳቸው በሚወዳደሩበት ቦታ ፍትሓዊ የምርጫ ውድድር እንዲኖር በማድረግ ለፓርቲያቸው ሳይሆን ከፓርቲቸው በላይ ለሆነው ሃይማኖታቸውና ለሚያመልኩት አምላክ ታማኝ ቢሆኑ ይበቃናል”፡፡
ጉድላክ ዮናታን በወሰዱት እርምጃ “ከአፍሪካ መልካም ነገር አይወጣም” ለሚሉት ምዕራባውያን የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆነዋል፤ በርካታዎችን አስገርመዋል፤ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች “የጀመሩትን መጨረስ” ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አሳይተዋል፤ በተለይ “ምርጫ” ለማድረግ ደፋ ቀና ለሚሉ ምን ዓይነት መንገድ መከተል እንደሚገባቸው ሽንፈትን በመቀበል እንዴት አሸናፊ መሆን እንደሚቻል መስክረዋል፤ ለአገራቸው መጪው ዘመን “ብሩህ” እንዲሆን ታላቅ ተስፋ ፈንጥቀዋል፡፡ መልካም ዕድል (ጉድላክ) ዮናታን!
***********************************
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
***********************************
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
No comments:
Post a Comment