ሐሙስ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በመላው ኢትዮጵያ - ሁላችንም እንነሳ - ግርማ ካሳ
(ይሄን መልእክት እና ሌሎች ተመሳሳይ መልእክቶችን ያሰራጩ። ሕዝቡ መረጃ እንዲደርሰውና የእንቅስቃሴው አካል እንዲሆን የድርሻዎትን ይወጡ)
ሐሙስ በመላው አገሪቷ፣ በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ አምቦ፣ ወለጋ፣ ደብር ብርሃን፣ ደሴ አርባ ምንጭ አዋሳ ...የሥራ ማቆም አድማዎችን ያካተቱ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ። ታክሲዎች አይንቀሳቀሱም። ሰራተኞች፣ ተማሪዎች ፣ አስተማሪዎች ሐሙስ ቀን ወደ ስራችሁ እና ወደ ትምህርት ቤታችሁ እንዳትሄዱ። ሐሙስ የጸሎት ቀን ነው። ሐሙስ ድምጻችንን የምናሰማበት ቀን ነው።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኢትዮጵያዉያንን ልብ የሰበሩ በርካታ ክስተቶች ተፈጽመዋል። በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ ወገኖቻችን ላይ አሰቃቂ እልቂት ተፈጽሟል። በደቡብ አፍሪካ በሌሎች የአፍሪክ አገሮች ግፊትና ጫና ፣ የጃኮብ ዙማ መንግስት ስደተኞችን ለመጠበቅ በርካታ የጥበቃ ሃይል እያሰማራ ነው። ችግሮቹ አሁን አፍጥው ያሉ ቢሆንም፣ በአንጻራዊነት ነገሮች ትንሽ ጋብ ያሉ ይመስላል። እንደ ናይጄሪያ መንግስት ያሉ ምስጋና ይግባቸዉና።
በሊቢያ ግን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው እልቂት በሌሎችም እንዳይደገም ትልቅ ርብርብ ያስፈልጋል። እጅግ በጣም በርካታ ኢትዮጵያዉያን በሊቢያ አሁንም ተደብቀው ነው ያሉት። የነርሱ ሁኔታ እጅግ በጣም ፣ በጣም አሳሳቢ ነው። ሁላችንም በየእምነት ቦታችን በጸሎት ወደ እግዚአብሄር መቅረብ አለብን። ከጭራቆቹ ጌታ ወገኖቻችን እንዲታደግ እንጸልይ። እግዚኦ እንበል።
በደቡብ አፍሪካም አሁን ጋብ ቢልም ገና የጠራ ነገር የለም። በጎሮቤት አገር ኬንያ፣ ስደተኞች ይወጡ የሚል ነገር አለ። ነገሮች ትንሽ በስደተኞች ላይ እየጠነከረ መጥቷል። የግድ ኢትዮጵያዉያን በአሁኑ ወቅት መሰባሰብና መያያዝ አለብን።
ወያኔ ሕዝቡ ሐዘኑን እንዲገልጽ፣ በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ፣ በአፍሪካ ሕብረት ፊት ለፊት ተቃዉሞዉን እንዲያሰማ ማስተባበር ነበረበት። ሆኖም ነገሮችን መደባበቅና በወገኖቻችን ላይ የደረሰዉን ግፍ አሳንሶ ማሳየቱን ነው የመረጠው። የአለም ትላልቅ የሜዲያ ተቋማት፣ እንደ አሜሪካ ያሉ መንግስታት ፣ አይሰስ የገደለው ኢትዮጵያዉያን ክርስቲያኖችን ነው ካሉ በኋላ፣ ከበርካታ ወገኖች ከፍተኛ ዉግዘት ሲደርስበት፣ ወያኔ፣ ትላንት «ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አላጣራሁም» ያለዉን ለዉጦ «አሁን ስላጣራው» በሚል የሞቶት ኢትዮጵያዉያን መሆናቸውን አምኗል። ለመለስ ዜናዊ አሥራ አምስት ቀናት በላይ የሐዘን ቀን ያወጀው ወያኔ፣ ለኢትዮጵያዊኑ ወገኖቻችን ግን 3 ቀን ብቻ የሐዘን ቀን ነው ያወጀው።
ከዝንብ ማር አይጠበቅም እንደሚባለው፣ ብዙም አራት ኪሎ ከተቀመጡት መጠበቁ ፋይዳ የለዉም። ማወቅ ያለብንን ሁላችንም አዉቀናል። እኛ ኢትዮጵያውያን፣ የሚያስብልን፣ የሚያገለግለን፣ የሚያከብረን፣ ለመብታችን የቆመ መንግስት የለንም።
ስለዚህ ኢትዮጵያዉያን ማድረግ ያለብንን በራሳችን ነው ማድረግ ያለብን። የፊታችን ሐሙስም በአገር ቤት መንግስት ያልጠራው፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉትም ለዚህ ነው። የተጠሩት እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ናቸው። ኢትዮጵያዉያን በየእምነታችን፣ በየፖለቲካ ድርጅቶቻችን፣ በየሲቪክ ማህበራችን፣ በየእድራችን፣ ለወገኖቻችን አጋርነት እናሳይ። ቢያንስ ለዜጎቻችን የሚያስብና የሚቆረቆር መንግስት ባይኖርም፣ በጭንቅ ያሉ ስደተኞች የሚወዳቸው ሕዝብ ግን እንዳለ እናሳያቸው።
ወገኖቼ አዎ በጣም አዝነናል። ዉስጣችን ትልቅ ቁስል አለ። ግን አይዞን። ከዚህ በኋላ የባሰ ነገር እንዳይፈጠር ነው መስራት ያለብን። አሁን እምባዎቻችን ጠርገን ፣ ፊታችንን ወደ ፈጣሪ አዙረን፣ መተባበር ነው ያለብን። ኢትዮጵያ ልጆቿ ከርሷ የሚሸሹ ሳይሆን የተሰደዱ የሚመለሱባትና ሌሎች ወደ እርሷ የሚሸሹ ለማድረግ ሁላችንም መነሳት አለብን። ከአሁን በኋላ ዝምታ ይብቃ!!!
No comments:
Post a Comment