መጋቢት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት ከታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጠው በቦሌ አየር ማረፊያ በሚስጢር ስም የተመዘገቡና ባለቤታቸው ተለይቶ ያልተመዘገቡ ድርጅቶች ካለፉት 10 አመታት ጀምሮ የኮንትራት ጊዜያቸውን ሳያድሱ እና
የቤት ኪራይ ክፍያቸውን ለመንግስት ገቢ ሳያደርጉ በመነገድ ላይ ናቸው።
በእነዚህ ድርጅቶች ጀርባ የከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እጅ እንዳለበትም ምንጮች ጠቁመዋል።
የኤርፖርቶች ድርጅት ፣ተከራዮችንና ሌሎች የሚመለከታቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚል ምክንያት በየካቲት 1999 ዓም ላይ ኤሮኔቲካል ያልሆኑ የገቢ ምንጮችን ለማስተዳደር የሚል መመሪያ ያወጣ ሲሆን፣ በመመሪያው መሰረት
ተከራዮቹ በየአምስት አመቱ በግልጽ ጨረታ እንደገና መወዳደር ይጠበቅባቸው ነበር።
ይሁን እንጅ ከእነዚህ መካከል፣8ት ባለቤታቸው የማይታወቅ በኮድ ስም የተመዘገቡ ድርጅቶችን ጨምሮ 15 የንግድ ድርጅቶች የኮንትራት ጊዜያቸውን ሳያድሱ ፣ የሚከፍሉት ወርሃዊ ክፍያ የት እንደገባ ሳይታወቅ ገንዘቡ በባለስልጣናት መበላቱን ምንጮች ጠቁመዋል።
ድርጅቶቹ በ1995 ዓም የኮንትራት ውል የፈረሙ ቢሆንም ፣ በ1999 ዓም በወጣው መመሪያ መሰረት እንደገና አለመመዝገባቸውን፣ ድርጅቶቹን ደፍሮ እንዲመዘገቡ የሚያደርግ አካል መጥፋቱን ምንጮች አክለዋል።
በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 02 የተመዘገበው ድርጅት፣ የህትመት ውጤቶችን ለመሸጥ በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ክፍያ 54 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ክፍል ተከራይቶ የሚገኝ ሲሆን፣ በአመት 437 ሺ 400 ብር ሂሳብ የአስር አመት
ጠቅላላ ክፍያ 4 ሚሊዮን 374 ሺ ብር ፤ በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 07 Cultural Cusin በሚል የይዞታ አይነት የተመዘገበው ድርጅት በአመት በካሬሜትር 5 ሺ 220 ብር ሂሳብ 54 ካሬ ሜትር ቦታ ቢወስድም የ10 አመታት የኪራይ
ክፍያ 2 ሚሊዮን 818 ሺ 800 ብር የት እንደገባ አይታወቅም።
በተርሚናል ቁጥር 2 ለሻንጣ ማሸጊያ በሚል በኮድ ቁጥር AACS 22 የተመዘገበ ድርጅት ለ12 ካሬ ሜትር በአመት በካሬ ሜትር 4 ሺ 100 ሂሳብ በአስር አመት 492 ሺ ብር ለመክፈል ቢዋዋልም ክፍያው የት እንደገባ አልታወቀም።
በተርሚናል 2 በኮድ ቁጥር AARS 12 ለካውንተር ሰርቪስ አገልግሎት ተመዝግቦ የሚገኘው ድርጅት 141.31 ካሬ ሜትር ቦታ ወስዶ በካሬሜትር በአመት 4 ፣ 100 ብር በ10 አመታት በአጠቃላይ 5 ሚሊዮን 793 ሺ 710 ብር ክፍያ እንዲሁም በዚሁ
ተርሚናል በኮድ ቁጥር AACS 09 የተመዘገበው የወርቅና ጌጣጌጦች ሱቅ ለያዘው 31.10 ካሬ ሜትር ቦታ በአመት በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ሂሳብ በአስር አመት 2 ሚሊዮን 519 ሺ 100 ብር ክፍያ የት እንደገባ አልታወቀም
በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 21 ለአበባ መሸጫነት የተከራየው በ25.9 ካሬ ሜትር የሰፈረው ቦታ በአመት በካሬ ሜትር 4 ሺ 100 ብር የሚከፈልበት ቢሆንም የ10 አመታት አመታዊ ክፍያው 1 ሚሊዮን 61 ሺ 900 ብር እንዲሁም በኮድ
ቁጥር AACS 06 የይዞታዉ መጠን 31.10 ካሬ ሜትር ለብር ጌጣጌጥ/Silver Shop/ የሚውለው መደብር በአመት በካሬሜትር 8 ሺ 100.00 ብር ተከራይቶ በአስር አመታት ውስጥ 2 ሚሊዮን 519 ሺ 100 ብር ክፍያ የት እንደገባ አይታወቅም።
በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 16 ለሱፐር ማርኬት የተከራየው በ 33.4 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሰፈረው መደብር በአመት 8 ሺ 100 ብር የሚከፈልበት ቢሆንም አመታዊው ክፍያው 2 ሚሊዮን 700 ሺ ብር ከ40 ሳንቲም እንዲሁ የት እንደገባአይታወቅም።
እነዚህን ድርጅቶች በባለቤትነት የሚያስተዳድሩዋቸው ሰዎች በግልጽ ባይታወቁም ምንጮች : ” በህግ የማይጠየቁ የተወሰኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘመዶችና ቤተሰቦች ናቸው” ይላሉ።
በስማቸው ተመዝገበው የሚገኙት የንግድ ድርጅቶችም በአዲሱ መመሪያ መሰረት ውል ሳይገቡ በመነገድ ላይ ሲሆኑ የሚከፍሉት ክፍያ ከወቅቱ ጋር የማይመጣጠንና ተቆጣጣሪ የሌለባቸው መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
በአዲሱ ውል መሰረት ውል ሳይዋዋሉ ለ5 አመታት ያክል በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በመነገድ ላይ ካሉት ድርጅቶች መካከል ለንደን ካፌና ሳተላይት ሬስቶራንት 109.9 ካሬ ቦታ በአመት ብር 138 ሺ 474 አላፋራጅ ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፣
የይዞታ መጠን 631 ካሬ ሜትር፣ አመታዊ ክፍያ በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ላሊበላ ወርቅ ቤት፣ 31.10 ካሬ ሜትር፣ አመታዊ የክፍያ መጠን በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ሲቲ ቢዝነስ ኮምፒዩተር ፣ 104 ካሬ ሜትር አመታዊ የክፍያ መጠን በካሬ ሜትር 8 ሺ 100
ብር ድሬ ኢንዱስትሪ ሃ/የተወሰነ የግል ማህበር 54 ካሬ ሜትር አመታዊ የክፍያ መጠን በሄክታር 8 ሺ 100 ህይወት ለማ ትሬዲንግ 31.10 ካሬ ሜትር የክፍያ መጠን በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ሲማት ትሬዲንግ 31.10 ካሬ ሜትር የክፍያ መጠኑ ባከሬ ሜትር
8 ሺ 100 ብር ይገኙበታል።
በአጠቃላይ አዲስ በወጣው መመሪያ መሰረት ህጋዊ ውል ሳይፈርሙ በመስራት ላይ የሚገኙት ደርጅቶች የ10 አመታት የኪራይ ዋጋ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ኤርፖርቶች ድርጅት እስካሁን እርምጃ ለመውሰድ አለመድፈሩን ምንጮች ገልጸዋል።
ጉዳዩ በተደጋጋሚ ለድርጅቱ ቢቀርብም ምላሽ መጥፋቱን ምንጮች አክለው ይገልጻሉ። በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ኤርፖርት ኢንተርፕራይዝን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
No comments:
Post a Comment