Tuesday, April 14, 2015

የመንግስት ቤቶችን ለመንግስት ባለስልጣናት ብቻ የሚያደርግ መመሪያ ስራ ላይ ዋለ



የመንግስት ቤቶችን ለመንግስት ባለስልጣናት ብቻ የሚያደርግ መመሪያ ስራ ላይ ዋለ

ሚያዝያ ፭(አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከዚህ ቀደም የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት በመባል ይጠራ የነበረውና በአሁኑ ወቅት የመንግስት ቤቶች አጀንሲ የሚባለው በምዝገባ ለዜጎች መኖሪያ ቤቶች በኪራይ የሚሰጥበትን የቆየ አሰራር በመተው ለባለስልጣናት ብቻ ለመስጠት የሚያስችል አዲስ መመሪያ አውጥቶ በሥራ ላይ አውሎአል።
አጀንሲው ከዚህ ቀደም ለበርካታ ዓመታት ወረፋ በመጠበቅ ከዛሬ ነገ የኪራይ ቤት እናገኛለን ብለው ተስፋ ያደረጉ በሺ የሚገመቱ ደንበኞቹን ተስፋ የሚያስቆርጥ መመሪያ በቅርቡ አውጥቶ በስራ ላይ ማዋሉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
በዚሁ መመሪያ መሠረት ኤጀንሲው በኪራይና ያለኪራይ ቤት የሚሰጠው ለፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች ተሿሚዎች፣ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት፣ ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ለአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር በክልል ደረጃ ላሉ ተሿሚዎች፣ ከሃላፊነታቸው
ለሚነሱ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ በጡረታ ለሚገለሉ የመከላከያ ጄኔራሎች፣ ከውጭ ሀገር ለተመለሱ አምባሳደሮች እንዲሁም የፌዴራል መንግስት የመምሪያ ወይንም የስራ ሒደት ባለቤቶች እንደሚሆን መመሪያው ያዛል፡፡
ይህ መመሪያ በባለስልጣናትና በዜጎች መካከል ልዩነትን በመፍጠር ዜጎች በኪራይ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብታቸውን የሚያሳጣ ነው ተብሎአል፡፡ ኤጀንሲው የቀድሞ የግል ተከራዮችንም ቀስ በቀስ የኪራይ ውል በማቋረጥ ቤቶቹን ለተፈቀደላቸው ባለስልጣናት
ለማስተላለፍ ማቀዱም መረጃው የደረሳቸው ተከራዮችን አስደንግጧል፡፡ ኤጀንሲው በአሁኑ ሰዓት ይህን መመሪያ ቁጥር 4/2007 በተለያዩ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በማስተዋወቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን የግል ተከራዮችን ቤት ይሰጠን ጥያቄ ማየት አቁሟል፡፡
በሙስናና በመልካም አስተዳደር የከፋ ችግር ያለበት ይህው ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት በአዲስአበባና በድሬዳዋ ከተሞች ከ12 ሺ 200 በላይ ቤቶችን በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment